EwnetMedia 2022
EwnetMedia
‹‹ኦርቶዶክስን በኦሮሙማ የማጥመቅ ሴራ››?
==================================
ፖለቲካ እና ታሪክ በሌላው ክፍለ ዓለም ‹‹ሳይንስ›› ቢኾኑም፥ በሀገራችን ኢትዮጵያ ግን የሴራ፣ የመጠላለፍና የእርስ በርስ መጠፋፋት ስልቶች ከተደረጉ ውለው አድረዋል፡፡ የፖለቲካውን ሴራና የታሪኩን ትርክት የሚያወሳስቡት በአብዛኛው ‹‹ተምረዋል›› የሚባሉት አካላት ሲኾኑ በእነርሱ መዘዝ በየቀኑ የሚገደሉት ግን ሕጻናት፣ ሴቶች፣ አረጋውያንና ለፍቶ አዳሪ ንጹሐን ዜጎች ናቸው፡፡ ሰሞኑን በምዕራብ ወለጋ፣ ጊምቢ ወረዳ፣ ቶሌ ቀበሌ ውስጥ የረገፉት ነፍሳትም የዚሁ ሴራ ተጠቂዎች ናቸው፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ብቻ በመተከል፣ በትግራይ፣ በማይካድራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጅግጅጋ፣ በባሌ፣ በአርሲ፣ በሐረርጌና ሌሎችም የሀገራችን ክፍል ዘግናኝ ጭፍጨፋዎች ተካሂደዋል፡፡ ገዳዮቹና አስገዳዮቹ ማንም ይኹኑ፥ የሟቾችም ማንነትና ሃይማኖት ምንም ይኹን፥ እየተቀጠፈ ያለው የሰው ሕይወት ነውና ሐዘኑ ልብ ይሰብራል፡፡ ከሞቱና አሟሟቱ በላይ እጅግ የሚያሳዝነው ግን ሐዘናችንን እንኳ በጋራ ማድረግ አለመቻላችን ነው፤ ለሟቾቹ ለማዘን እንደ ቅድመ ኹኔታ የምንወስደው የሬሳውን ብሔር ማንነት ነውና! የዚህ ኹሉ እብደታችን መንሥኤው ታሪክን እና ፖለቲካን የተማርንበት፣ የተረዳንበትና ለመተግበር የሞከርንበት ስህተታችን ነው!
እንደ እውነቱ፥ ሰዎች ሲገደሉ በግልጽ እያየንና እየሰማን ስለኾነ ቢያንስ እናዝናለን፣ እናለቅሳለንም፡፡ በዚሁ የተሳሳተ የታሪክ ትርክትና የፖለቲካ ሴራ ተቋማት ሲፈርሱ፣ ሃይማኖት ክፉኛ ስትፈተን ግን እምብዛም ያስተዋልን አይመስልም፡፡ በተለይ፥ ኦርቶዶክሳዊት እምነት እንድትጠፋ፣ ቤተ ክርስቲያኗ በምድረ ኢትዮጵያ እንዳትኖር ያልተመከረ ምክር፣ ያልተሸረበ ሴራ፣ ያልተጻፈ ድርሳን፣ ያልተናገረ ልሳን የለም ማለት ይቻላል፡፡
ኹሉም ኢትዮጵያዊ የሐሰት ትርክቱ ጥቃት ሰለባ ቢኾንም፥ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በኦሮሚያ ክልል የደረሰባትና እየደረሰባት ያለው ግፍ ግን ከኹሉ ይብሳል፡፡ በኦሮሞ ወጣቶችና በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ላይ የተሠራው ሴራ ከልክ ያለፈ ነው፡፡ ሁለቱ በተናጠል የተደረገባቸውን ጥፋትና ማሸማቀቅ ትተን ኦሮሞነትንና ኦርቶዶክሳዊነትን በማጣላት የፖለቲካ ትርፍ ለማጋበስ የተኬደበትን ርቀት ግን ታሪክ አይዘነጋውም! ጽንፈኛ የኦሮሞ ፖለቲከኞች፣ ‹‹ዶክተር›› እና ‹‹ፕሮፌሰር›› የሚሉ ማዕርጋትን ደርበው ካልተማረው ዜጋ በታች የሚያስቡ ‹‹ምሁራን››፣ ሐሰትን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በማራገብ የዕለት እንጀራቸውን የሚጋግሩ የማኅበረሰብ ‹‹አንቂዎች›› ኹሉ ከአክራሪ እስልምናው ጋር በመተባበር ዘምተውባታል፡፡ ኦርቶዶክስ እና ኦርቶዶክሳውያን ከኦሮሚያ ክልል ጨርሰው እንዲጠፉ ያልወጡት ተራራ፣ ያልወረዱት ቁልቁለት የለም!
ሁለቱ ማንነቶች (ኦሮሞነትና ኦርቶዶክሳዊነት) ፈጽሞ የአንድ ሰው ገንዘቦች ሊኾኑ እንደማይችሉ አብዝተው ለፈፉ፤ ጻፉ፡፡ ‹‹ኦሮሞ ኾኖ ኦርቶዶክስ የለም›› የሚለውን ተረት ደጋግመው በትውልድ አእምሮ ቀረጹ፡፡ ‹‹ኦርቶዶክስ የአማራ ሃይማኖት ናት›› ብለው ከአንድ ሕዝብ ጋር ሊጨፈልቋት ሞከሩ፡፡ ኦርቶዶክስ መኾን ኦሮሞነትን ክዶ አማራነትን አምኖ መጠመቅ እንደኾነ በሕዝብ ሚዲያ ላይ ጭምር ሳይፈሩና ሳያፍሩ ተናገሩ፡፡ ሌላው ቀርቶ፥ የክርስትና ስም የሚሰጠው ‹‹ኦሮሞዎችን አማራ ለማድረግ ነው›› እስከማለት ተዳፈሩ፡፡ ኦርቶዶክስ ከአማርኛ ውጪ ያሉትን ቋንቋዎች ትጸየፋለች፤ የኦሮሞን ባህል ታጠፋለች፤ የአንድ ጎሣ የበላይነትን ትሰብካለች… እያሉ ደሰኮሩ፡፡ ‹‹የምኒልክ ሃይማኖት›› ብለውም ከንጉሡ ጋር ሊቀብሯት ጥረት አደረጉ፡፡ ‹‹የአሓዳዊ ሥርዓት አቀንቃኝ›› የሚልም ፕሮፖጋንዳም ከፈቱባት፡፡
ይህ ኹሉ በዝምታና በትዕግሥት ሲታለፍ ጽላቱን ጭምር ‹‹የኦሮሞ ብቻ›› አድርገው ለመቅረጽ እንቅስቃሴ ጀመሩ፤ የኦሮምኛ ስምም አወጡለት፡፡ ቄሱም፣ ጳጳሱም፣ ሰባኪውም፣ ዘማሪውም፣ ቤተ ክህነቱም፣ ማኅበሩም፣ ቅዳሴውም፣…ኹሉ በአፋን ኦሮሞ ማገልገል ብቻ ሳይኾን እነርሱ በሚያምኑበት የጎሣ ፖለቲካ ልክ እየጠበቡ እንዲንቀሳቀሱ አቅጣጫ አስቀመጡ፡፡ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ጭምር ‹‹አፋን ኦሮሞ መቻል ብቻ ሳይኾን በደም ኦሮሞ መኾን የግድ ነው›› ወደሚል ጽንፍ አሳደጉት፡፡ ‹‹የኦሮሞ ጳጳስ››፣ ‹‹የኦሮሞ ማኅበር››፣ ‹‹የኦሮሚያ ቤተ ክህነት››፣ ‹‹የኦሮሚያ ሲኖዶስ››፣ ‹‹የኦሮሞ ቤተ ክርስቲያን››፣ ወዘተ. የሚሉትን አስበው መተግበር ጀመሩ፡፡ ‹‹በኦሮሚያ ክልል ኦሮሞ ያልኾነ ካህን ማገልገል አይችልም›› በሚል ማሳደድና መግደል አዘወተሩ፡፡ ‹‹በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚገኙ አድባራትና ገዳማት ገቢ ለኦሮሚያ አብያተ ክርስቲያናት ብቻ መዋል አለባቸው›› በሚል የቁልቢ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤልን የመሳሰሉ ገዳማትን ገቢዎች ለብቻ መቆጣጠር ፈለጉ፡፡
አብዛኞቹ የእውነት ሚዲያ ትኩረቶች ‹‹ለምን ኦሮሚያ ላይ ኾኑ?›› ብለው ለሚጠይቁትም ምላሹ ይኸው ነው፤ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የምትገኘው ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አደጋ ላይ የመኾኗ ሐቅ! ኦርቶዶክስ፥ በትግራይ፣ በደቡብና በሌሎች የሀገራችን ክፍሎች ፈተና አልገጠማትም ማለት ግን አይደለም፤ እውነት ሚዲያ በዚህ ረገድ የድርሻዋን ከተወጣች ሌሎች አካላት ደግሞ በእነዚያ ላይ ትኩረት አድርገው ይሰራሉ በሚል እምነት እንጂ! በተረፈ፥ የእውነት ሚዲያ እያንዳንዷ እርምጃ ለኦርቶዶክስና ኦርቶዶክሳውያን ጥብቅና መቆም ብቻ ነው፤ ሌላ ዓላማ የላትም! ‹‹ጊንጊልቻ›› በሚል ርእስ የታተመው የዕቅበተ እምነት መጽሐፍም በአብዛኛው የዚሁ ሚዲያ ጽሑፎች ስብስብ መኾኑ መረሳት የለበትም፡፡
‹‹ታዲያ አንዳንድ ጽሑፎቻችሁ ለምን ‹የኦሮሙማ ፖለቲካ› አስተሳሰብን ይመስላሉ?›› የሚሉት አንባቢያን ስጋታቸው ይገባናል፤ ‹‹እባብ ያየ በልጥ በረየ›› ነውና ከወቅቱ የፖለቲካ ሴራ ጋር ቢያገናኙት አይፈረድባቸውም፡፡ እውነታው ግን ወዲህ ነው… ((እንመለስበታለን!))
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
#አንብቡ! #ገንቢ_አስተያየቶችንም_ከበሳል_ትችቶች_ጋር_ስጡ! #ስድብ_በባህል_ነውር_በሃይማኖት_ደግሞ_ኃጢአት_ነውና_እንተወዉ! #እውነት https://www.facebook.com/ewnetmediapage የሚለውን ገጻችንን #Like በማድረግ ቤተሰቦቻችን ሁኑ! ለሌሎችም #Share በማድረግ ጽሑፎችን እንዲያነቡ፣ እንዲቀላቀሉንም ጋብዙ!
#በቴሌግራም ቻናላችንም ይከታተሉን https://t.me/ewnetmedia
#አውነትን_በመግለጥና_ሐሰትን_በማጋለጥ_የሀገርን_ሰላምና_የሕዝብን_አንድነት_ለመጠበቅ_እንትጋ!
