EwnetMedia 2022

EwnetMedia 2022

EwnetMedia

መሥዋዕትና ሥርዓቱ— በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ!

==================================

በኦሮሞዎች ዘንድ ‹‹መሥዋዕት›› የሚለውን ጽንሰ አሳብ የሚተረጉመው ‹‹አርሣ›› የሚለው ቃል ነው፤ ይኸም በቀጥታ ሲተረጎም ‹‹ማጤስ›› እንደማለት ነው፡፡ በተለይ የአፋን ኦሮሞው ቃል አንድ የሚያስታውሰን ነገር አለ፤ ደም በማፍሰስ፣ ስብ በማጤስ ይፈጸም የነበረውን የኦሪቱን ሥርዓተ መሥዋዕት፡፡

እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር እንዲያቀርቡ የታዘዙአቸው አምስት ዓይነት መሥዋዕቶች ናቸው፡- የሚቃጠል መሥዋዕት፣ የእህል ቁርባን፣ የደኅንነት መሥዋዕት፣ የኃጢአት መሥዋዕትና የበደል መሥዋዕት ናቸው (ዘሌዋ.ምዕ.1-5)፡፡[1]

በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድም የሚዘወተሩ ተመሳሳይ የመሥዋዕት ዓይነቶችና ተያያዥ ሥርዓቶች ስለሚስተዋሉ እነዚህን በተለያዩ መገለጫዎች፣ በአጭሩ ለመመልከት እንሞክር፡-

(ሀ)ኢሬሣ—የኦሮሞዎች መሠዊያ፡- ኢሬሣ (Irreessa)[2] መሥዋዕት የሚቀርብበት ቁስ/ቦታ ሲኾን የሚዘጋጀውም ከተለያዩ መዓዛ ካላቸው እንጨቶች (abbayii/ቀለዋ/፣ ulumaayii/ልምጭ/፣ kusaayee /ከሰይ/ ሌላም ቅጠላቸው የለመለመና ያማረ ለጋ የኾኑትን) ቆርጠው በሐረግ አንድ ላይ በማሰር ነው፡፡[3] አንዳንዴም የተከበረ ድንጋይ በማቆም ሊኾን ይችላል፡፡ መሥዋዕት ኹሉ የሚቀርበው ወደዚህ ኢሬሣ የታረደውን እንስሳ ደም በመርጨት፣ ሥጋውን ከየብልቱ (የቀኝ ክፍል) ቆራርጦ በማስቀመጥ፣ እንዲሁም ከሁሉም ዓይነት እህል እየቆነጠሩ (በትንሹ እያነሱ) በማቅረብ ነው፡፡

ኢሬሣ የሚቀመጠው በዋናነት ለሥርዓተ አምልኮ በተለየ የጸሎት ቤት ወይም ተራራ ጥግ፣ ጥላ ባለው ትልቅ ዛፍ ሥር ወይም ከወንዝና ከምንጭ አጠገብ ነው፡፡ አልፎ አልፎ በእያንዳንዱ የእምነቱ ተከታይም ቤት ሊኖር ይችላል፤ ግን በሰዋራ ቦታ (‹‹ዲንቃ›› በሚሉት ጓዳ) መኾን አለበት፡፡ የኢሬሣው መቀመጫ የትም ቢኾን ማንም ሊደርስበት የማይችል ቦታ መኾኑ ግን አያጠያይቅም፤ ይህ የኢሬሣው ቦታ ለእነርሱ ‹‹ቅድስተ ቅዱሳን›› ዓይነት መኾኑ ይመስላል፡፡

በእርግጥም፥ የማኅበረሰቡ አዛውንት ኢሬሣ ለምን በተደበቀ ቦታ (ማጀትና ጨለማ ውስጥ) እንደሚቀመጥ የሚያብራሩት በተለያዩ አገላለጾች ቢኾንም ‹‹የምንሰዋለት መንፈስ መገለጫ ነዋ›› የሚል የጋራ መንፈስ አላቸው፡፡ እነርሱ እንደሚሉት አያና (መንፈሱ) እዚያ መጥቶ ‹‹ይበላዋል›› ወይም ‹‹ያሸተዋል››፡፡ ይህ ሁሉ ሲኾን ግን ለማንም አይታይም፤ (ለምሳሌ፥ በዘንዶ አምሳል) ለሰው የታየ እንደኾነ ግን ተቆጥቷልና በተለየ ሥርዓት ቶሎ ይቅርታ ሊጠየቅ ይገባዋል እንጂ ለመግደል መሞከር ፈጽሞ አይታሰብም!

(ለ) ꬊጋ (Dhiiga)፡- ይህ ‹‹ደም›› ማለት ሲኾን ዋነኛው የማኅበረሰቡ መሥዋዕት ክፍል ነው፡፡ ከሌሎች የእንስሳት ሥጋ ብልቶችና የእህል ዓይነቶች ጋር ኾኖ በኢሬሣ (መሠውያው) ላይ ይቀርባል፡፡ በቅዱስ መጽሐፍም፡- ‹‹የሥጋ ኹሉ ሕይወት ደሙ ነው፤ ደሙም ከሕይወቱ የተነሣ ያስተሰርያልና በመሠዊያው ላይ ለነፍሳችሁ ማስተሰርያ ይኾን ዘንድ እኔ ለእናንተ ሰጠሁት (ዘሌዋ.17፡11)፤ ‹‹...በኦሪት ሕግ ሁሉ በደም ይነጻ ነበር፤ ደም ሳይረጭ ግን አይሰረይም ነበር›› (ዕብ.9፡22) የሚሉ ተመሳሳይ ጭብጦች ይገኛሉ፡፡

በሌላ መልኩ፥ እንኳንስ ኾን ተብሎ ለመሥዋዕት የታረደው ቀርቶ ለሌላ ጉዳይ የሚታረድ እንስሳ ደም እንኳ ልዩ ዋጋ ይሰጠዋል፤ በተለየ ዕቃ ተደቅኖ በቤት መቃንና ጉበን እንዲሁም መሃል ምሰሶ ላይ እንዲረጭ ይደረጋል፡፡ ይህን መሰሉ ሥርዓት ከኦሪቱ ሞተ በኩር ለመዳን ይረጭ ከነበረው የእስራኤላውያን የፋሲካ በግ ደም ጋር ቁርኝት ያለው ይመስላል (ዘጸ.12፡1-14)፡፡ በእርግጥም አብዛኞቹ የማኅበረሰቡ አባላት ለምን ደም በመቃን፣ በጉበንና መሃል ምሰሶ ላይ እንደሚቀቡ ሲጠየቁ ‹‹ቆደሳቲ›› ከማለት ያለፈ ምላሽ አይሰጡም፤ ‹‹ሥርዓቱ ነው›› እንደማለት፡፡ እነርሱ የሥርዓቱን መነሻ እና ምክንያት አያውቁትም እንጂ ‹‹ሥርዓቱ›› ለመኾኑ (አስቀድሞ የኖረና ሊሻር የሚገባው እንዳልኾነ) ግን ጠንቅቀው ያውቃሉ፤ አስረግጠውም ያስረዳሉ፡፡ ባላምበራስ ጀቤሣ ግን ኦሮሞዎች ደጋግና ርኩሳን መናፍስት መኖራቸውን እንደሚያምኑ ከጠቀሱ በኋላ በተለይ ለምን ደም የቤታቸውን መሃል ምሶሶ፣ የበራቸውን ግራና ቀኝ መቃን ላይ እንዲሁም ግምባራቸውንና ማንቁርታቸውን እንደሚያስነኩ ከአንዳንድ አዛውንት አገኘሁት ያሉትን ምላሽ (ምክንያት) እንዲህ ጽፈውታል፡-[4]

‹‹በምሰሶ ላይ የሚቀባው ደም ተጻራሪ መናፍስትን ከቤት ለማስወጣት (በቤት ውስጥ እንዳይኖሩ ለማድረግ)፣ በበር መቃን ላይ የሚቀባው ከውጭ ወደ ቤት እንዳይገቡ እንዲከላከል እንዲሁም ግምባርና ማንቁርትን ደም ማስነካት ''adda na jabeessi, lubbuu na dheeressi'' (ግምባሬን አጠንክር፣ እድሜዬን አስረዝም) በማለት ርኩሳን መናፍስትን የማራቅ ዓላማ አለው፡፡››

በእርግጥ ኦሮሞዎች የራሳቸውን ግንባር ብቻም ሳይኾን የከብቶቻቸውንም ግንባር ደም ያስነካሉ፡፡ በአንጻሩ ታዲያ ተክለ ጻድቅ መኵሪያ ይህንኑ የኦሮሞዎችን ድርጊት ‹‹ባዕድ አምልኮ›› በማለት ድርሳነ ራጉኤልንና ድርሳነ ኡራኤልን ጠቅሰው፡- ‹‹አጼ ልብነ ድንግል እንደ ኦሮሞች ሥርዓት የፈረሶቻቸውን ግንባር የቦረንቲቻ ደም እየቀቡ፣...አምልኮ ባዕድ አድርገው ነበርና....እግዚአብሔር ግራኝ መሐመድን አስነሳባቸው›› ሲሉ ጽፈዋል፡፡[5]

(ሐ) Ixaana (ዕጣን)፡- የዕጣን መሥዋዕት በብሉይም ሆነ በሐዲስ የታወቀ ሥርዓት ነው፡፡ ‹‹በቀማሚ ብልሃት እንደ ተሠራ የተቀመመ ንጹህና ቅዱስ ዕጣን አድርገው...›› (ዘፀ.30፡35)፤ ‹‹...ከተወቀጠውም ልቅምና ደቃቅ ዕጣን እጁን ሙሉ ይወስዳል...በእግዚአብሔርም ፊት ዕጣኑን በእሳቱ ላይ ያደርጋል›› እንዲል (ዘሌዋ.16፡12-13)፡፡ በኦሮሞም ሥርዓተ አምልኮ ውስጥ የዕጣን መሥዋዕት ዋነኛውና መደበኛው መሥዋዕት ነው፡፡

በኦሪት፥ ከሊቀ ካህናቱ በቀር፣ ዛሬም በቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛውን የክህነት ደረጃ ያለው ካልኾነ በቀር ዕጣኑን በጥናው ላይ እንደማያስቀምጥ ኹሉ በኦሮሞም ዘንድ የቃሉ ባለቤት (የመንፈሱ ማኅደር) እንጂ ማንኛውም ሰው በማጤሻው ገል (የሸክላ ማዕጠንት) ላይ ሊያስቀምጥ አይፈቀድለትም፡፡ 

(መ) የእህልና መጠጥ ቁርባን [Daddarbaa (ደደርባ) እና Dhibaayyuu (ዲባዩ)]፡- ‹‹ደደርባ›› በቁሙ ሲፈታ፥ ‹‹መወርወር›› ማለት ሲኾን (ለሚበሉ ምግቦች የሚነገር) ‹‹ዲባዩ›› ደግሞ ‹‹ማፍሰስ/ጠብ ማድረግ›› የሚለውን ትርጉም ይይዛል (ለሚጠጡ ነገሮች የሚነገር)፡፡ እነዚህ ሥርዓቶች ለመሥዋዕት የቀረቡትን እህሎች ከየዓይነቱ ትንሽ ትንሽ በመቆንጠር አልያም የተሰዋውን (የታረደውን) ከብት ብልት ከየዓይነቱ በመውሰድ በመሰዊያው ላይ መበተን (ማስቀመጥ) እንዲሁም ከየመጠጦቹ በትንሹ ማፍሰስ ነው፡፡ በማኅበረሰቡ እምነት መሠረት በዚህ መልኩ የሚሠዋለት መንፈስ በስውር መጥቶ ይመገበዋል፡፡ ይህ ኹኔታ በቀጥታ ከኦሪቱ መስዋዕት ጋር የተገናኘ ነው፡- ‹‹የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ይገፍፈዋል፤ በየብልቱም ይቆርጠዋል፡፡... የተቆረጡትንም ብልቶች...በእንጨቱ ላይ ይረበርቡታል...›› እንዲል (ዘሌዋ.1፡6-8)፡፡

ኾን ተብሎ ለመናፍስት የሚኾን መሥዋዕት ተዘጋጅቶ ይቅርና የኦሮሞ ማኅበረሰብ በዘወትር ኑሮውም ቢኾን አድባሩን፣ ቆሌውን ሳይለማመን ለእነርሱ የሚኾነውንም ትንሽ ነገር አስቀድሞ ቆርሶ ሳይወረውር፣ ቆንጥሮ ሳይበትን፣ ከሚጠጣውም ጨልፎ (ቀንሶ) ሳይደፋ ፈጽሞ ለራሱ አይቀምስም! ቡና ሲፈላ እንኳን ሴቷ የጀበናውን ክዳን ከፍታ ቃጀባ (''qaajabaa'') ይበሉ ትላለች፤ ‹‹ይመርቁ›› እንደማለት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ታዲያ አባወራው ''qaajabaa...Rabbi situ jabaa...'' (ብርቱው አምላክ ስማን...) ብሎ ተገቢውን ‹‹ቡራኬ›› ከሰጠ በኋላ እንደተለመደው ቆንጥሮ ይወረውራል፤ ከቡናውም በሲኒ ተቀንሶ ይደፋል፡፡ ይህንን ለምን እንደሚያደርጉ ሲጠየቁ ምላሹን በአንድ ሥነ-ቃላቸው ያጠቃልሉታል፡- ''kan nyaate nama hin nyaatu'' (‹‹የበላ ሰውን አይበላም››)፤ ባታበላው ይበላሃልና የሚል መልእክት አለው፡፡


(ሠ) Haqa (ሐቃ)፡- ‹‹ሐቃ›› በቁሙ እውነት፣ ፍትሕ ማለት ሲኾን በዚህ አገባቡ ግን ‹‹ታርዶ ለአሞራ የሚጣል›› እንስሳን ይወክላል፡፡ የመናፍስት መሥዋዕት ኾኖ የሚቀርበው እንስሳው፥ የከሳ፣ የመነመነ፣ ለማየት የማያስደስት ቁመና ያለው ሲኾን መሰል ከሲታ ገጽታ ያላቸው እንስሳት ተመርጠው የሚሰውቱትም መሥዋዕቱ በአሞራ እንጂ በሰዎች ስለማይበላ ሊኾን ይችላል፡፡

ይህ መሥዋዕት የሚቀርበው ቤተዘመድ ከኾኑ (አንድ ‹‹የዘር ሐረግ›› ካላቸው) የማኅበረሰቡ አባላት መካከል ሰው የሞተ እንደኾነ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹አያና አባ›› (የአባታቸው መንፈስ) ተቆጥቶናል ብለው ስለሚያምኑ ‹‹የይቅርታ መጠየቂያ›› መሥዋዕት መኾኑ ነው፡፡

የመሥዋዕቱ ሥርዓትም እንደሚከተለው ነው፡- አስቀድሞ ቤተዘመድ (በአያና አባ ጥላ ሥር ያሉ) ኹሉ ተሰብስበው ለአያና አባው ያመለክቱና ትክክለኛውን የመሥዋዕት ማቅረቢያ ቀንና ቦታ ያስወስናሉ፡፡ በዕለቱ ማልደው በተጠቀሰው ቦታ ተሰብስበው የተዘጋጀውን እንስሳ (በግ) ያርዳሉ፡፡ የታረደውን በግ ጨጓራ ቀድደው በዚያ ውስጥ እጆቻቸውን እያጮለቁ እርስ በርስ ይጨባበጣሉ፤ ‹‹አቤቱ እንዲህ ታረቀን›› እንደማለት ነው፡፡ ከዚያም የታረደውን በግ በሜዳማ (ግላጭ) ሥፍራ ያስቀምጡና እነርሱ ተሰባስበው ራቅ ባለ ሰዋራ ሥፍራ ላይ በጸጥታ (ድምጽ ባለማሰማት) ይጠባበቃሉ፡፡ በዕለቱ ከሕፃናት እስከ አዋቂ ድረስ ማንም ቢኾን እህል ውኃ መቅመስ አይችልም፤ ገና ‹‹ዋቃ አልታረቃቸውምና››፡፡ ዋቃ እንደታረቃቸው የሚያውቁት ታርዶ የተጣለውን በግ ከሰማይ አሞራ መጥቶ የበላላቸው እንደኾነ ብቻ ነው፡፡ እድላቸው ኾኖ ይህ ከተሳካላቸው ‹‹ታርቋቸዋልና›› እልልታው ይቀልጣል፣ ሌላ እንስሳ ታርዶ ይበላል፣ የአያና አባው ማወደሻ ዘፈን (እነርሱ ‹‹ዳላጋ›› ይሉታል) ይደምቃል፡፡

ይህ ሥርዓት (በተለይ የዋቃን እርቅ በሰማይ አሞራ መረዳት) ከኦሪቱ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በእሳት መውረድ ማረጋገጥ ጋር ያመሳስለዋል፡- ‹‹...የእግዚአብሔርም ክብር ለሕዝቡ ኹሉ ተገለጠ፡፡ እሳትም ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጣ፤ በመሠዊያውም ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፣ ስቡንም በላ፤ ሕዝቡም ኹሉ አይተው ተደነቁ፤ በግምባራቸውም ወደቁ›› (ዘሌዋ.9፥23-24)፤ ‹‹እሳትም ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወረደች፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት፣ እንጨቱንም፣ ድንጋዮቹንም በላች...›› (1ነገ.18፥38)፤ ‹‹ሰሎሞንም ይህን ጸሎት በፈጸመ ጊዜ እሳት ከሰማይ ወርዶ የሚቃጠለውን ቁርባንና መሥዋዕቱን ኹሉ በላ...›› (2ዜና.7፥1) እንዲል፡፡


(ረ) ወረጆ (Warajoo)፡- በኦሮሞዎች ዘንድ ‹‹Warajoo›› የሚባለው የአንድን ሰው በደልና ሊመጣበት የሚችለውን መጥፎ ነገር ይሸከም ዘንድ የሚመረጥ እንስሳ ነው፡፡ እንስሳው እንደሰው አቅም ታይቶ ከብት፣ በግ፣ ፍየል አልያም ዶሮ ሊኾን ይችላል፡፡

እንስሳው እንደተለየ ባለ ወረጆው እጁን በእንስሳው ላይ ጭኖ ይጸልያል (ዘሌዋ.1፥4) ወይም እፍ ይልበታል (ይተነፍስበታል)፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ያ እንስሳ ይለቀቃል፡፡ ምንም እንኳ ኾን ተብሎ ለአውሬ ባይሰጥም የሰውየውን ጦስ ተሸክሟልና ቢሞት ወይም በአውሬ ቢበላ ባለ ወረጆው ሰው ‹‹እንኳን ደስ ያለህ›› ይባላል፤ ወረጆው ‹‹ጦሱን ይዞ ሄዷልና!››፡፡ ከዚህ በኋላ (በእነርሱ እምነት) ይህ ሰው አስቀድሞ የሰራው በደል ጠፍቶለታል፤ ወደፊትም ክፉ ነገር አያገኘውም፡፡ ምናልባት ይህ እንስሳ በቤት ውስጥ የሚታረድበት ኹኔታ ከተፈጠረ እንኳ እጁን የጫነበት (የተነፈሰበት) ባለወረጆው እንዲበላ አይፈቀድለትም፤ ይህ ‹‹ከራቀው በደል ጋር መልሶ እንደመጋባት›› ነውና፡፡

በብሉይ ኪዳንም ኃጥአትን ለሠሩ ሰዎች ለማስተሰርያ የሚፈጸም ሥርዓት ነበር፡- አውራ በግ፣ ጠቦት ወይም ወይፈን ወደ ቤተ መቅደስ ይቀርባል፡፡ ካህኑም የሰዎችን ኃጥአት ባቀረበው እንስሳ ላይ እጁን በመጫን ወደ እንስሳው ያስተላልፈዋል፡፡ ከዚያም እንስሳው ወደ በረሃ ተወስዶ ይለቀቃል፡፡ ይህ ‹‹በደልን ማስተላለፍ›› ይባል ነበር፡፡ ኀጥአተኛውም በእንስሳው ላይ እጁን በመጫን ራሱን ከእንስሳው ጋር ያስተካክል (ኀጥአቱንም ያሸክመው) እንደነበር ተጽፏል፡፡ ስለ ኀጥአት ስርየት ይቀርብ የነበረውን የኦሪቱን ‹‹ተቅበዝባዥ ፍየል›› ኹኔታ በተመለከተ እንዲህ ተጽፏል፡- ‹‹አሮንም ሁለቱን እጆቹን በደኅነኛው ፍየል ራስ ላይ ይጭናል፤ በላዩም የእስራኤልን ልጆች በደል ኹሉ፣ መተላለፋቸውንም ኹሉ፣ ኀጥአታቸውንም ኹሉ ያስተሰርያል፤ በፍየሉም ራስ ላይ ያሸክመዋል፤ በተዘጋጀው ሰውም እጅ ወደ ምድረ በዳ ይሰድደዋል፡፡ ፍየሉም ኀጥአታቸውን ሁሉ ወደ በረሃ ይሸከማል፤...›› (ዘሌዋ.16፥21-22)፡፡

በሐዲስ ኪዳን ደግሞ፥ ጌታ ክርስቶስ ‹‹እርሱ ግን በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕመማችንንም ተሸከመ፤...›› የሚል ትንቢት የተነገረለት (ኢሳ.53፥4)፤ ‹‹...እርሱ ስለ ኀጥአታችን በሥጋው ኀጥአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ... እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበርና...›› የተባለውም (1ጴጥ.2፥24) በኦሪቱ የኀጥአት ማስተሠርያ መሥዋዕት (በግ) አምሳል መኾኑን ልብ ይሏል፡፡ 

~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~

#አንብቡ! #ገንቢ_አስተያየቶችንም_ከበሳል_ትችቶች_ጋር_ስጡ! #ስድብ_በባህል_ነውር_በሃይማኖት_ደግሞ_ኃጢአት_ነውና_እንተወዉ! #እውነት https://www.facebook.com/ewnetmediapage የሚለውን ገጻችንን #Like በማድረግ ቤተሰቦቻችን ሁኑ!  ለሌሎችም #Share በማድረግ ጽሑፎችን እንዲያነቡ፣ እንዲቀላቀሉንም ጋብዙ!

#በቴሌግራም ቻናላችንም ይከታተሉን https://t.me/ewnetmedia

#አውነትን_በመግለጥና_ሐሰትን_በማጋለጥ_የሀገርን_ሰላምና_የሕዝብን_አንድነት_ለመጠበቅ_እንትጋ!


[1] የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃት፤ 1992 ዓ.ም፣ ገጽ.30፡፡

[2] በመጫ ኦሮሞ ‹‹ኢሬሣ››፣ በቱለማ ኦሮሞ ደግሞ ‹‹ኢሬቻ›› የሚባሉት አንድ ዓይነት ናቸው፡፡ በዚህ ዐውዱ ግን የተለያየ ጭብጥ ይዘው እናገኛቸዋለን፡- ‹‹ኢሬቻ›› በተለይ በዓመት ሁለት ጊዜ (መስከረም ውስጥ በሐይቅ ላይ፣ ግንቦት አከባቢ ደግሞ በተራራ ላይ) የሚከበር በዓል በመኾኑ ኹለቱ ሊምታቱ አይገባቸውም፡፡          


[3] Ilaalcha Oromoo (2009); ጀቤሣ ኤጄታ (ባላምበራስ)፤ የኦሮሞ ብሔር ባህልና አጭር ታሪክ (ገጽ.93)፡፡

[4] ጀቤሣ ኤጄታ (ባላምበራስ)፤ የኦሮሞ ብሔር ባህልና አጭር ታሪክ (ገጽ.99)፡፡


[5] የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ከአጼ ልብነ ድንግል እስከ አጼ ቴዎድሮስ፣ 1953 ዓ.ም፣ ገጽ.37፡፡



Report Page