EwnetMedia 2022
EwnetMedia
የዋቄፈና እምነት መሪዎች:- ማንነት፣ የመምረጫ መሥፈርትና የሥራ ድርሻ!
==================================
(ሀ)አባ ሙዳ (Abbaa Muudaa) ወይም Qaalluu (ቃሉ)፡- ቃሉ የዋቄፈና እምነት መሪ (ከፍተኛው የክህነት ባለቤት) ሲኾን የመጀመሪያው ቃሉ ከሰማይ የወረደ ሰው እንደኾነ ይታመናል፡፡[1] እግዚአብሔር ከሰው ልጆች ጋር የሚገናኘው በቃሉ አማካይነት (ድልድይነት) እንደኾነም ይታሰባል፡፡[2] አባ ሙዳ፣ ቃሉ፣ እሬሳ ገዳ የሚባሉት ስሞች ለአንድ የዋቄፈና እምነት መሪ የተሰጡ ስያሜዎች (ተሿሚ ግለሰብ የሚያመለክቱ) ሲኾኑ መጠሪያው እንደየአካባቢው የሚለያይ ነው፡፡[3] አባ ሙዳነት አንዴ ከተሰጠ በኋላ ኃላፊነቱ እስከ ዕድሜ ልክ አይሻርም፤ [እንደ ብሉይ ኪዳኑ ክህነት] ከዘር ዘርም የሚተላለፍ ነው፡፡[4] በዋቄፈና እምነት ውስጥ የሴቷም ሢመት እንዲሁ ነው፡- ማንኛዋም ሴት ቃሊቲ (የሃይማኖት መሪ) ከኾነች እስከ ዕድሜ ልኳ ድረስ መሪ የመኾን መብት አላት፡፡[5] እናም፥ አባ ሙዳ ወይም ቃሉ ‹‹የኦሮሞ ሌዋውያን ናቸው›› ማለት ይቻላል (ሌዋውያኑ ወንዶች ብቻ ከመኾናቸው በቀር)፡፡

ኦሮሞዎች የቃሉ መንፈስ ማደርያ እንዲኾን የተመረጠውን ሰው በሌላም አጠራር፥ ‹‹አያንቱ›› (በቁሙ ሲፈታ ዕድለኛ ማለት ነው) ወይም ‹‹ሉባ›› (ካህን) ብለው ይጠሩታል፡፡ እነዚህ ስለ መጻእያት ትንቢት በመናገር፣ እንደ ሐሳበ ዘመን ሊቃውንት በማገልገል፣ እንዲሁም በሕዝቡና በዋቃ መካከል ድልድይ በመኾን (መረጃ በማስተላለፍና በአማላጅነት) እንደሚያገለግሉ የሚታመኑ ናቸው፡፡ እንዲያውም፥ ‹‹ቃሉ በክርስትናው እምነት ውስጥ እንዳለው እንደ ‹ጳጳስ› እና በእስልምናው ውስጥ እንዳለው እንደ ‹ኢማም› ዓይነት ተመሳሳይ ደረጃ ያለው፣ የሃይማኖትና የመንፈሳዊ ክብረ በዓላት አዋቂ የኾነ፣ ከአያና ውስጥ ከአንዱ ጋር ልዩና የጠበቀ ግንኙነት ያለው፣ በተወሰነ ወቅትም ይኸው አያና የሚሠፍርበት (የሚነግሥበት) ሰው ነው›› በማለት የገለጹ አሉ፡፡[6]
በርካታ የማኅበረሰቡ ባህልና ሥርዓተ አምልኮዎች የሚተገበሩት፣ እስከ ዛሬም ድረስ ተጠብቀው የሚገኙት በቃሉ ተቋማት ዘንድ ነው፡፡ የሥርዓቱ ፈጻሚዎችም የቃሉ ማደርያዎች (አያንቱ) ናቸው፡፡ ስለዚህም ቃሉ ለኦሮሞ ብዙ ነገር ናቸው፡- እንደ ነቢያት ትንቢት ይናገሩላቸዋል፣ እንደ ሊቃውንት ዘመኑን ይቆጥሩላቸዋል (መቁጠር ብቻም ሳይኾን እንደ ጠንቋዮችም በጎና ክፉ ቀናትን ይለዩላቸዋል)፣ እንደ ካህናት መሥዋዕት ያቀርቡላቸዋል፣ እንደ ቅዱሳንም ከዋቃ ጋር ያስታርቋቸዋል (ያማልዷቸዋል)፡፡
(ለ) Caamsituu (ጫምሲቱ)፡- እነዚህ ደግሞ በማኅበረሰቡ ዘንድ እንደ ‹‹ልዩ ጸሎተኞች›› የሚታመኑ ሲሆን፥ በተለያዩ ምክንያቶች ዝናብ እንዳይዘንብ ሲፈለግ ልዩ ተሰጥዖ ያላቸው (ዝናብ እንዳይዘንብ የሚያደርጉ) ሰዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ፡- በመከር ወቅት እህል እንዳያበላሽ፣ በሠርግና ቀብር ቀናት ሕዝቡ እንዳይረበሽ ሲባል፣ ወዘተ ሊኾን ይችላል፡፡ እነዚህ caamsituu (ጫምሲቱ) ይባላሉ፤ በቁሙ ሲተረጎም ‹‹ዝናብ የሚያባራ›› እንደማለት ነው፡፡ በእርግጥ እነዚህ ጫምሲቱዎች ምን ዓይነት ‹‹ጸሎት›› እንደሚጸልዩና ምን ዓይነት ድርጊቶች እንደሚያከናውኑ ግልጽ ባይኾንም ድርጊቱ ግን በቅዱስ መጽሐፍ ላይ ከምናውቀው የነቢዩ ኤልያስ ተግባር ጋር ተመሳሳይነት ያለው እንደኾነ እንረዳለን (1ነገ.17፡1-7፤ ያዕ.5፡17-18)፡፡
(ሐ) Ayyaana Abbaa (አያና አባ)፡- ኦሮሞዎች በዓይን የማይታዩ ክፉና ደግ መናፍስት እንዳሉ ያምናሉ፡- ክፉ መናፍስት የሚባሉት ቀሳፊዎች ሲኾኑ ስማቸው ''seexana'' (በየቦታው የሚዘዋወርና ከኹሉ የባሰ ኃይለኛ)፣ ''golfaa'' (በየመንደሩ የሚኖር)፣ እና ''dachee'' (በደንና በቆላ ቀመስ /አፋፍ/ የሚኖር) ነው፡፡ ደጋግ መናፍስት ጠባቂ መናፍስት (ውቃቢ) ሲኾኑ በዋናነት ''ayyaana abbaa'' (የአባት አምላክ) እና ''giiftii/aayyolee'' (እመቤት) ይባላሉ፡፡[7]
ማኅበረሰቡ ለሁለቱም መናፍስት መሥዋዕት ያቀርባል፡- ክፉዎቹ ተመግበው በያሉበት እንዲያርፉ (እንዳይተናኮሉ)፣ ደጋጎቹ ደግሞ ለማደርያነት በሚመርጧቸው ሰዎች አማካይነት በዋቃ ቶኪቻ እና በሰዎች መካከል እንዲያማልዱ ለመለማመን ሲባል፡፡ ‹‹በተለይ ተገቢው መሥዋዕት በተገቢው ጊዜ የቀረበ እንደኾነ›› ይላሉ የማኅበረሰቡ አዛውንት፥[8] ‹‹ወዲያ ወዲህ እየተክለፈለፉ አደጋ እንዳያደርሱብን አለቃቸው ይቆጣጠራቸዋል፤ አለበለዚያ ለእነርሱ አሳልፎ ይሰጠናል፡፡››
(መ) ለ ‹‹አያንቱነት›› (የእምነት መሪነት) የሚያበቁ ኹኔታዎች፡-
(መ-1) በዋቃ መመረጥ፡- በማኅበረሰቡ እምነት እነዚህ ሰዎች አያንቱ (ዕድለኛ) መባላቸው ተገቢ ነው፤ ይህ ያለ ዋቃ (እግዚአብሔር) ምርጫ የሚገኝ አይደለምና፡፡ በመሠረቱ ይህ ሁኔታ ለክህነት ከመመረጥ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ክህነት መመረጥን (መታደልን) እንደሚጠይቅ ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናልና፡- ‹‹እናንተ...የተመረጠ ትውልድ፣ የመንግሥትና የክህነት ወገን፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ ለርስቱም የተለየ ወገን ናችሁ›› እንዲል (1ጴጥ.2፡9)፡፡ ‹‹ዕድለኛ›› መሰኘትም ለሁሉም ያልተሰጠውን የመመረጥ ክብር ማግኘት መቻል ነው፤ ‹‹በውኑ ሁሉ ሐዋርያት ይሆናሉን?...›› እንደተባለ (1ቆሮ.12፡29)፡፡ ሁሉም ካህናት መሆን ቢችሉማ ኖሮ ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ በምን ቅድመ ሁኔታ መመረጥ እንዳለባቸው ባልተናገረ ነበር (1ጢሞ.3:2-13፤ ቲቶ.1:5-9)፡፡
(መ-2) ከሕዝቡ የብቃት ምስክርነት፡- ከሰማያዊው ዋቃ በተጨማሪ ቃሉ (አያንቱ) ለመኾን የሕዝብ ምስክርነት ያስፈልጋል፡- ‹‹ቃሉ…በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው ንጹህና ምስጉን፣ ባህላዊውን ነውር እግድ (taboos) የሚጠነቀቅ፣ ‹‹safuu›› (ሳፉ) የሚሰኙ የሥነ ምግባር እሴቶችን (values) የሚጠብቅ፣ በየወቅቱ ያሉትን የእምነት ክብረ በዓላት የሚያከብር (የሚያስከብር)፣ በሚያደርጋቸውም ክንዋኔዎች ኹሉ እውነትን የሚከተል፣ ከኀጥአትም የራቀ መኾን አለበት›› እንዲል፡፡[9] የኦሪት ካህናትም ‹‹ነውር ያለባቸው›› እንዳይኾኑ የሚመረጡበትን ቅድመ ሁኔታ እግዚአብሔር በዝርዝር ለሙሴ ነግሮታል (ዘሌዋ.21፡16-23)፡፡
(መ-3) ግርዛት፡- ኦሮሞም እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ኹሉ የግርዛት ባህል አለው፡፡ እዚህ ላይ ለማንሳት የተፈለገው ግን በማኅበረሰቡ ዘንድ ብቻ የሚታወቀውን የግዝረት አፈጻጸም ነው፡፡ ለምሳሌ፡- በማኅበረሰቡ የገዳ ሥርዓት ውስጥ በሃይማኖታዊ መሪነት የሚሾሙት ሰዎች የተለያዩ ደረጃዎች ያላቸው ሲኾን ከመጀመርያው ደረጃ (ገዳ አያና) ወደ ሉባ ለመሸጋገር በ40 ዓመታቸው መገረዝ ዋናው ቅድመ ሁኔታ ነበር፡፡[10] ስለዚህም ሉባ ለመኾን በዕድሜ 40 ዓመት መሙላት የግድ ከመኾኑም በላይ በጠባይ፣ በዕውቀትና ስለ ትጋቱ (ችሎታው) በሕዝቡ ዘንድ የተመሰከረለት ሊኾን ይገባዋል፡፡ ተገርዘው ‹‹ሉባ›› የተባሉት ኹሉ በእጩነት ለመቅረብ መብት ቢኖራቸውም በአንድ ሉባ አስተዳደር ሥልጣን የሚይዙት ግን ከእነርሱ መካከል የሚመረጡት 12 ብቻ ናቸው፡፡[11]
(ሠ) ለቃሉዎች የተከለከሉ ተግባራት፡-[12]
- በተሰበረ ወይም በተሰነጠቀ ወንበር ላይ አይቀመጡም፤
- ጸጉራቸውን፣ ጺማቸውንም[13] አይላጩም፤
- አያርሱም፣ አይቆፍሩም፤
- ከሰው ጋር ዘወትር አይገናኙም፤
- ከገዳ መሪዎች ጋር በመንገድ አይተላለፉም፤
- በበዓላት ቀን ካልኾነ በስተቀር ከብት አያርዱም፤
- ከቤታቸው ውጪ የተዘጋጀውን ምግብ አይበሉም፤
- ከገብስ የተዘጋጀ ምግብ ውጭ አይበሉም፤
- ብቻቸውን አይሔዱም፣ ወንዝም አይሻገሩም፡፡
(ረ) የእምነት መሪዎች የሥራ ድርሻ:- አባ ሙዳ (ቃሉ) የሃይማኖት አባት እንጂ የአስተዳደር መሪ አይደለምና በፖለቲካ ውስጥ እንዲገቡ ፈጽሞ አይፈቀድለትም፡፡[14] ይልቁንም የሚከተሉትን ዋና ዋና ተግባራት እንዲፈጽም ይጠበቃል፡-[15]
- ምርጫ ላይ ለሚነሱት አለመግባባቶች መፍትሔ መስጠት፤
- በአካባቢዎች ያሉት የሃይማኖት መሪዎችን መርዳትና መምራት፤
- ሕግና ልማዶች እንዲከበሩ ማስተባበር፤
- የተፈጥሮ ሕጎች (ሰፉ) እንዳይጣሱ መጠበቅ፤
- በሐመቺሣ ዕለት ለሕጻናት ስም ማውጣት፣ መመረቅ፤
- የፈውስ ጸሎት ማድረግ፤
- የበደሉ ክሰው፣ የተበደሉ ተክሰው እንዲታረቁ ማድረግ፤
- የፈጣሪን ሕግጋት ማስተማር፤
- ለስምንት ዓመት ብቻ ሥልጣን ለሚረከቡት አባ ገዳዎች ሥርዓተ መንግሥት መፈጸም፤
- ለእነዚህ የገዳ መሪዎች ሃይማኖታዊ ቡራኬ፣ ምርቃትና እውቅና መስጠት፤
- አዲሱን የገዳ አመራር Qumbii (ቁምቢ) የሚባል መራራ ፍሬ (‹‹ቅዱስ ምግብ››) እንዲበላ አድርጎ እግዚአብሔርን እንዳያሳዝን፣ ፍርድ እንዳያዛባ፣ ሕዝብ እንዳይበድል ቃለ መሐላ ማስፈጸም፡፡ ሉባው ሥርዓተ መንግሥት የሚፈጽምበት ይህ ቁምቢ እንደ ‹‹ቅዱስ ቁርባን›› የሚታይ ነው፤ መሪዎቹን ‹‹እውነት ያናግራቸዋል›› ተብሎም ይታመናል፡፡[16]
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
#አንብቡ! #ገንቢ_አስተያየቶችንም_ከበሳል_ትችቶች_ጋር_ስጡ! #ስድብ_በባህል_ነውር_በሃይማኖት_ደግሞ_ኃጢአት_ነውና_እንተወዉ! #እውነት https://www.facebook.com/ewnetmediapage የሚለውን ገጻችንን #Like በማድረግ ቤተሰቦቻችን ሁኑ! ለሌሎችም #Share በማድረግ ጽሑፎችን እንዲያነቡ፣ እንዲቀላቀሉንም ጋብዙ!
#በቴሌግራም ቻናላችንም ይከታተሉን https://t.me/ewnetmedia
#አውነትን_በመግለጥና_ሐሰትን_በማጋለጥ_የሀገርን_ሰላምና_የሕዝብን_አንድነት_ለመጠበቅ_እንትጋ!
[1] Sirna Gadaa; Biiroo Aadaafi Tuurizimii Oromiyaa; 1999: 108, 112.
[2] Sirna Gadaa; Biiroo Aadaafi Tuurizimii Oromiyaa; 1999: 108.
[3] ታቦር ዋሚ፤ የውገና ድርሰቶችና የታሪክ እውነቶች፤ 2006 ዓ.ም፣ ገጽ.219፡፡
[4] Seenaa Oromoo Hanga Jaarraa 16ffaa, 1998:47፤ Sirna Gadaa; 1999: 122፤ ታቦር ዋሚ፤ 2006 ዓ.ም፣ ገጽ.219፡፡
[5] ታቦር ዋሚ፤ የውገና ድርሰቶችና የታሪክ እውነቶች፤ 2006 ዓ.ም፣ ገጽ.242፡፡
[6] ባኃሮ ቢያንሣ፤ ኦሮምያ፤ 1985 ዓ.ም፣ ገጽ.30፡፡
[7] ጀቤሣ ኤጄታ (ባላምበራስ)፤ የኦሮሞ ብሔር ባህልና አጭር ታሪክ (ገጽ.190)፡፡
[8] ቃለ መጠይቅ (ወ/ሮ ሀንገራሼ)፡፡
[9] ባኃሮ ቢያንሣ፤ ኦሮምያ፤ 1985 ዓ.ም፣ ገጽ.ገጽ.30-31፡፡
[10] ጀቤሣ ኤጄታ (ባላምበራስ)፤ የኦሮሞ ብሔር…(ገጽ.39)፡፡
[11] ዝኒ ከማሁ (ገጽ.47)፡፡
[12] ታቦር ዋሚ፤ የውገና ድርሰቶችና የታሪክ እውነቶች፤ 2006 ዓ.ም፣ ገጽ.198፡፡
[13] እሸቱ ኢረና፤ የኦሮሞ ታሪክ፤ 2001 ዓ.ም፣ ገጽ.166፡፡
[14] ታቦር ዋሚ፤ የውገና ድርሰቶችና የታሪክ እውነቶች፤ 2006 ዓ.ም፣ ገጽ.251፡፡
[15] ታቦር ዋሚ፤ የውገና ድርሰቶችና የታሪክ እውነቶች፤ 2006 ዓ.ም፣ ገጽ.199፡፡
[16] Sirna Gadaa; Biiroo Aadaafi Tuurizimii Oromiyaa; 1999: 118.
