EwnetMedia 2022

EwnetMedia 2022

EwnetMedia

መካነ ጸሎት ወመሥዋዕት [‹‹ቅዱሳት መካናት››] በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ!

==================================

በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ በልዩ ኹኔታ የሚከበሩ፣ ‹‹የተቀደሱ ቦታዎች›› ተብለው የሚታወቁ አሉ፡፡ እነዚኽ በጥቅሉ፥ ‹‹Ardaa-Jilaa/አርዳ ጅላ›› (‹‹መንፈሳዊ›› ጉዞ የሚደረግባቸው የተከበሩ ቦታዎች) ተብለው ይታወቃሉ፡፡ ለምሳሌ፡- በሃይማኖታዊ ማእከልነት ጭምር የሚታወቁና ለክብረ በዓላት ጉዞ የሚደረግባቸው መዳ ዋላቡ (ባሌ)፣ ሆራ አርሳዲ (ቢሾፍቱ)፣ኦዳ ነቤ፣ ወዘተ. ተጠቃሽ ናቸው፡፡[1]

በማኅበረሰቡ ዘንድ ትላልቅ ዛፎች፣ ሰፋፊ ሐይቆች፣ ረጃጅም ተራሮች፣ ወዘተ. የእግዚአብሔር መንፈስ የሚገለጥባቸው ክቡራት ፍጥረታት ናቸው ተብሎ ይታመናል፡፡[2] በዚሁ አግባብ፥ ኦሮሞዎች ለጸሎትና መሥዋዕት ማቅረቢያ ‹‹የተለዩ›› ከሚሏቸው ቦታዎች ጥቂቶቹን ለማጥቀስ ያህል፡- 

(ሀ) ገልማ ወይም ወልዳ፡- የቃሉ የመንፈሳዊ ክብረ በዓልና የስግደት ማድረጊያ ቦታ ‹‹ገልማ›› የሚባል ሲኾን የሚቆረቆረውም በአምባ ጫፍ ላይ፣ ወይም በርካታ ትላልቅ ዛፎች እጅብ ብለው በበቀሉበት ውስጥ፣ ወይም በጅረቶች አከባቢ፣ በትላልቅ ተራራዎችና ቋጥኞች (አለቶች) አከባቢ ወዘተ. ነው፡፡[3] በትላልቅ ዛፎች አካባቢ የሚደረገው ይህ ሥርዓተ አምልኮ ግን፥ ከማኅበረሰቡ ቅድመ ታሪክ ጋር የተያያዘ እንጂ ዛፉን የማምለክ ምልክት አይደለም፡፡[4] በአንዳንድ ቦታዎች ዛፎች ብቻ ባሉበት የሚከናወን ሲኾን በሌሎች ዛፎቹ እንደ አጸድ ብቻ ይኾንና በእነርሱ የተከበበ ሌላ የማምለክያ ቤት (ቤተ ጸሎት) ይሠራል፡፡

በቤት መልክ ከሚሠራው ባሻገርም በጫካ ውስጥ የተለየ ሥፍራ ለይተው በማጠር፣ በመካከሉ ትላልቅ ድንጋዮች በማቆም የሚጸልዩበት ኹኔታም አለ፡፡ ይህንን ቦታ ‹‹ሲዳ›› በማለት ይጠሩታል፤ የተከበረ የአምልኮ ሐውልት እንደማለት ነው፡፡ ምናልባትም፥ ይህ ኹኔታ የፍኖተ ሎዛውን የአባታችን ያዕቆብ ‹‹ቤቴል›› ታሪክ ያስታውሰን ይኾናል፡- ‹‹...ያዕቆብም ማልዶ ተነሣ፤ ተንተርሷት የነበረችውንም ድንጋይ ወስዶ ሐውልት አድርጎ አቆማት፣ በላይዋም ዘይት አፈሰሰባት፡፡...ያዕቆብም እንዲህ አለ፡-...ለሐውልት ያቆምኋት ይህች ድንጋይ የእግዚአብሔር ቤት ትኾንልኛለች...›› እንዲል (ዘፍ.28፥10-22)፡፡


ሌላው የሚገርመው ጉዳይ በእነዚህ የአምልኮ ሥፍራዎች ዙርያ የሚገኙ እንጨቶች ፈጽመው አይቆረጡም፡፡ ልክ እንደ ቤተ ክርስቲያን አጸድ ማለት ናቸው፡፡ በተጨማሪም በውስጥ የሚያድሩ፣ በዙርያቸው የተኮለኮሉ አውሬዎችም እንዲታደኑ (እንዲገደሉ) አይፈቀድም፤ ለእነርሱ እነዚህ ‹‹አውሬዎች›› ሳይኾኑ ‹‹አዋይ›› (የሥፍራው ክብር መገለጫዎች/የበረከት ምንጮች) ናቸው፡፡ በብሉይ ኪዳን መሰል የአምልኮ ሥፍራዎች የተለመዱ እንደነበሩ የሚያመላክቱ ነገሮች አሉ፤ የአህዛብ ማምለኪያ ሥፍራዎች እና ቅዱስ የእግዚአብሔር መገለጫ ሥፍራዎችም ተደርገው ተጠቅሰዋል (ዘዳ.12፥2-4፤ዘፍ.18፥1፤ ዘፀ.24፥12-18፤ ዘዳ.32፥2፤ መዝ.46፥2)::

(ለ) ስምንቱ የዋቃ ተራሮች:- (በተለይ) የቱለማ ኦሮሞዎች ‹‹የእግዚአብሔር ተራሮች›› በሚል ከኦዳ ነቤ ጋር የሚጠቅሷቸው፣ ለዋቃ ቶክቻ የምስጋና ሥነ-ሥርዓት የሚፈጽሙባቸው ማእከላት ስምንት ሲኾኑ እነርሱም፥ ቱሉ ጩቃላ፣ ቱሉ ኤረር፣ ቱሉ ፉሪ፣ ቱሉ ገላን፣ ቱሉ ዋቶ ዳለቻ፣ ቱሉ ፎየታ፣ ቱሉ ሆጮጫ እና ቱሉ ኤግዱ ናቸው፡፡[5]

(ሐ) ስድስቱ የዋቃ ሆራዎች (‹‹ቅድሳት ሐይቆች››)፡- በኦሮሞዎች ዘንድ ሆራ የመፈወስ ኃይል ያለው፣ ከሌሎች ውኃማ አካላት የተለየ የድኅነት ማግኛ የኾነ ፍል ውኃ (ሐይቅ) ነው፡፡ እንደ እነርሱ እምነት፥ በዚህ ሐይቅ መነከር ለሰዎችም ኾነ ለከብቶች ፍቱን ‹‹መድኃኒት›› ነው፡፡ ይህ በክርስትናው ‹‹ጠበል›› መኾኑ ነው፡፡ እንዲያውም፥ የዛሬዎቹን አንዳንድ የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን የጠበል ቦታዎች (እንጦጦንና የዝቋላ አቦን ጨምሮ) ‹‹ተነጥቀው ነው እንጂ ጥንት የኦሮሞ ሆራዎች ነበሩ›› ብለው የጻፉ የዘመኑ ‹‹ምሁራን›› አሉ፡፡[6] በተለይም፥ ኦዳ ነቤን ማእከል የሚያደርገው የቱለማ ኦሮሞ ‹‹ስድስቱ የዋቃ ሐይቆች›› የሚላቸው የእምነት ማእከላት አሉ፡- ሆራ አርሰዲ፣ ሆራ ኪሎሌ፣ ሆራ ሃዶ፣ ሆራ ግንድብ፣ ሆራ ወርጦ፣ ሆራ ኤረር ይባላሉ፡፡[7]

(መ) አምስቱ የኦሮሞ ኦዳዎች፡- በኦሮሞ ታሪክ ውስጥ፥ የእምነት፣ የፖለቲካና ማኅበራዊ-ነክ ጉዳዮች ምክክር የሚደርግባቸው በኦዳ (የተከበረ ዛፍ) ጥላ ሥር ነው፡፡[8] በማኅበረሰቡ ዘንድ አምስቱ [ዋና ዋና] የኦሮሞ ኦዳዎች ተብለው የሚታወቁትም፡- ኦዳ ቢሲል (ምዕ/ሸዋ፣ ኢሉ ገላን ወረዳ)፣ ኦዳ ሮባ (ባሌ፣ ግንꬊር ወረዳ)፣ ኦዳ ነቤ (ምሥ/ሸዋ፣ አቃቂ ወረዳ)፣ ኦዳ ቡልቱም (ምዕ/ሐረርጌ፣ ኦዳ ቡልቱም ወረዳ) እና ኦዳ ቡሉቅ (ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ ሆሮ ወረዳ) ናቸው፡፡[9]

(ሠ) Gabalaa (ገበላ) (የኦሮሞ ‹‹ቤተ መቅደስ››)፡- በተለይ በቦረና (ጉጂ) ኦሮሞ ዘንድ የገዳ አባቶች (አባ ቦኩዎች) በየጊዜው የሚሰበሰቡበት ቦታ ሚኤ ቦኮ የሚባል ሲኾን ይኸው ቦታ ተለይቶ ይታጠርና ልዩ ክብር ይቸረዋል፡፡ እንደ አቶ ዋቴ ገለጻ ይህ ሥፍራ Gabalaa (ገበላ) ይሰኛል፤ እንደ ‹‹ቤተ መቅደስ›› የሚቆጠር ስውር ቦታ ነው፡፡ ጫማ ተደርጎ አይገባበትም፡፡ ከሚገባቸው ሰዎች በስተቀርም ኹሉም የማይደረስበት ነው፡፡ መግባት የሚፈቀድላቸው በሥርዓቱ ልዩ ሥልጣን ያላቸው፣ በማኅበረሰቡም ዘንድ ‹‹በንጽህናቸው›› የታወቁ ሰዎች ብቻ (ለምሳሌ፡-እርግማን የሌለበት፣ የእናት አባቱን ተዝካር ያወጣ፣ ወዘተ) ናቸው፡፡

በመጨረሻም፥ ስለ እነዚህ ‹‹ቅዱሳት መካናት›› በአንክሮ ሊጤኑና በጥንቃቄ ሊጠኑ የሚገባቸውን ጥቂት ነጥቦች በመጠቆም እናጠቃልል፡- 

(1ኛ) እነዚህ ኹሉ ወንዞች፣ ተራሮች፣ ዛፎች፣ ወዘተ፥ የጸሎት እና መሥዋዕት ማቅረቢያ ቦታዎች እንጂ ራሳቸው የሚመለኩ አለመኾናቸውን ልብ ይሏል፡፡[10]

(2ኛ) የኦሮሞ ማኅበረሰብ እነዚህና መሰል የመሥዋዕት ማቅረቢያ ቦታዎችን በተለምዶ ‹‹adbaarii›› እያለ ይጠራቸዋል፤ አድባር ደግሞ በግእዙ ‹‹ተራሮች›› ማለት ነው፡፡ እናም፥ በዚህም የኦሪቱንና የኦሮሞ ማኅበረሰብን ሥርዓተ አምልኮ ተዛምዶ እንገነዘብ ይኾናል፡፡

(3ኛ) በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አንዳንድ ሥርዓቶች እንዳለው ኹሉ ወደ አብዛኞቹ እነዚህ ቦታዎች መቅረብ የሚገባቸውና የማይገባቸው አካላት አሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ሃይማኖታዊ ሥርዓት በሚፈጸምበት የተቀደሰ ዋርካ (ኦዳ) ሴቶች እንዲቀርቡ የማይፈቀድበት ኹኔታ አለ፡፡[11]

(4ኛ) አንዳንድ ጸሓፍት፥ ‹‹የኦሮሞ ቅዱሳት መካናት›› እያሉ ከእነዚህ ቦታዎች ጋር የሚጠቅሷቸው አንዳንድ ቦታዎች የራሳቸውን ፍላጎትና እምነት የሚያንጸባርቁ እንጂ ‹‹የኹሉም ኦሮሞ›› አይደሉም፡፡ ለምሳሌ፡- እነ ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰን የባሌውን ድሬ ሼክ ሁሴንን ጭምር ‹‹ዋነኛ የኦሮሞ አምልኮ ማእከል›› ሊሉን ሞክረዋል፤ እስልምና የኹሉም ኦሮሞ እምነት የኾነ ይመስል፡፡[12] አንዳንዶች ደግሞ፥ በዚሁ አጋጣሚ የይገባኛል ይዞታ ጥያቄ ለመተንኮስ ሞክረዋል፡- ‹‹ዛሬ ላይ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት የተሰሩባቸው የመሃልና የሰሜን ሸዋ ቦታዎች ‹የኦሮሞ የአምልኮ ቦታዎች ነበሩ›› ብለዋልና፡፡[13]

~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~

#አንብቡ! #ገንቢ_አስተያየቶችንም_ከበሳል_ትችቶች_ጋር_ስጡ! #ስድብ_በባህል_ነውር_በሃይማኖት_ደግሞ_ኃጢአት_ነውና_እንተወዉ! #እውነት https://www.facebook.com/ewnetmediapage የሚለውን ገጻችንን #Like በማድረግ ቤተሰቦቻችን ሁኑ!  ለሌሎችም #Share በማድረግ ጽሑፎችን እንዲያነቡ፣ እንዲቀላቀሉንም ጋብዙ!

#በቴሌግራም ቻናላችንም ይከታተሉን https://t.me/ewnetmedia

#አውነትን_በመግለጥና_ሐሰትን_በማጋለጥ_የሀገርን_ሰላምና_የሕዝብን_አንድነት_ለመጠበቅ_እንትጋ!


[1] Ilaalcha Oromoo (2009); Duudhaa (1998:33). ታቦር ዋሚ፤ የውገና ድርሰቶችና የታሪክ እውነቶች፤ 2006 ዓ.ም፣ ገጽ.239፡፡


[2] Sirna Gadaa; Biiroo Aadaafi Tuurizimii Oromiyaa; 1999: 94.


[3] ባኃሮ ቢያንሣ፤ ኦሮምያ፤  1985 ዓ.ም፣ ገጽ.32፡፡


[4] ጀቤሣ ኤጄታ (ባላምበራስ)፤ የኦሮሞ ብሔር ባህልና አጭር ታሪክ (ገጽ.100)፡፡


[5] Sirna Gadaa; Biiroo Aadaafi Tuurizimii Oromiyaa; 1999: 101-102.


[6] DUDHAA (2008:10)


[7] Sirna Gadaa; Biiroo Aadaafi Tuurizimii Oromiyaa; 1999: 101.


[8] Sirna Gadaa; Biiroo Aadaafi Tuurizimii Oromiyaa; 1999: 92.

[9] Seenaa Uummata Oromoo Hanga Jaarraa 20ffaa, Biiroo Aadaafi Tuurizimii Oromiyaa.

[10] ታቦር ዋሚ፤ የውገና ድርሰቶችና የታሪክ እውነቶች፤ 2006 ዓ.ም፣ ገጽ. 210-212፡፡

[11] እሸቱ ኢረና፤ የኦሮሞ ታሪክ፤ 2001 ዓ.ም፣ ገጽ.175 (William Cornwallis Harris, "The Highlands of Ethiopia", 1844፡56 ጠቅሰው እንደጻፉት)፡፡

[12] Mohammed Hassen, The Oromo of Ethiopia: A History (1570-1860), P.7. እሸቱ እረና፣ 2001 ዓ.ም፣ ገጽ.175፡፡


[13] እሸቱ ኢረና፤ የኦሮሞ ታሪክ፤ ገጽ.174፡፡ 




Report Page