EwnetMedia 2022
EwnetMedia
‹‹መባቺ›› እና ‹‹እንግጫ››፡- ዝክረ አዲስ ዓመት በኦሮሞ ማኅበረሰብ!
==================================
(1) Mabaachii (መባቺ)
በቅዱስ መጽሐፍ አስተምህሮ መሠረት መባቻ የሚባለው ፀሐይ ልክ ስትገባ፣ ጨረቃ ተወልዳ በከፊል የምትታይበት ቀን ነው፡፡[1] ይህም የወር መጀመርያ ቀን ነው፡፡ ቀኑም የተቀደሰ ነው፡- ‹‹በመባቻ ቀን በታወቀችው በዓላችን ቀን መለከትን ንፉ...›› እንዲል (መዝ.80፥3)፡፡ እንዲያውም፥ አይሁድ ከእግዚአብሔር ጋር ካላቸው የአምልኮ ግንኙነት ይልቅ መሰል በዓላትን ማድመቅ ያስበልጡ ስለነበር እግዚአብሔር፥ ‹‹መባቻችሁንና ሰንበቶቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች...›› በማለት አስጠንቅቆአቸዋል (ኢሳ.1፥14)፣ ቅ/ጳውሎስም፥ ‹‹...ስለ ወር መባቻ ማንም አይፍረድባችሁ... (ቆላ.2፡16) በማለት ለአማናዊቷ ዕረፍት ምሳሌ ይኾኑ ዘንድ የተበየኑ በዓላት የድኅነት እንቅፋት እንዳይኾኑ አስረግጦ ተናግሯል፡፡ እነዚህ ኹሉ አይሁድ ምን ያህል በተለይ መባቻን በትኩረትና በጥንቃቄ ያከብሩት፣ ከምንም በላይ ይጨነቁለት እንደነበሩ የሚያመላክቱ ነገሮች ናቸው፡፡

በኦሮሞ ዘንድም (በተለይ በመጫ)፥ ‹‹መባቺ›› የወራቸው መጀመርያ ነው፤ በልዩ ኹኔታም ይከበራል፡፡ ለምሳሌ፡- በዕለቱ ወደ ሌላ የሚሔድ ዕቃ፣ ገንዘብ፣ እህል፣ ወዘተ ውጭ ያድራል፤ እቤት ካደረ በመባቺ ወደ ሌላ መሔድ ክልክል ነውና፡፡ በተመሳሳይ ኹኔታ ከውጭ የሚመጣ ሰው (እንግዳ) ቢኖር እንኳ የቤቱን እህል የማይቀምስባቸው ቦታዎች አሉ፤ በእነርሱ አባባል ‹‹ባዕዳን ናቸውና አይገባቸውም!››፡፡ በብሉይ ኪዳን ከአሮን ልጆች በቀር ለሌሎች ያልተፈቀደ መብል እንደነበረ (ዘፀ.29፡33)፣ ለእስራኤላውያን ብቻ የተፈቀደው የፋሲካ መሥዋዕት ‹‹ከእርሱ ባዕድ ሰው አይብላ›› ከተባለው (ዘፀ.12፡43) ጋር ተዛምዶ ያለው ይመስላል፡፡
(2) Ingiccaa (እንግጫ)
በአንዳንድ ድርሳናት ላይ ‹‹ግጫ›› ወይም ‹‹ቆጽለ ብሥራት›› እየተባለ የሚጠራ ሲኾን ይኸውም፥ በኦሪቱ የጥፋት ውኃ ዘመን ርግቢቷ ለኖህ ይዛለት የመጣችው የለመለመ የወይራ ቅጠል (‹‹ውኃው ጎድሏል›› የሚል የምስራችን (ዘፍ.8፥11) መነሻ በማድረግ ፍጻሜው፥ ጌታችን ሞትን በትንሣኤ ድል ነሥቶ በሲኦል ለነበሩት ነፍሳት ሰላምን ለሰበከበት መዳረሻ ምሳሌ ኾኗል (1ጴጥ.3፥19-20)፡፡ ይኽንኑ የነፍሳት ከሲኦል መውጣት እያሰብን የወይራ ልምላሜ ቢታጣ ግጫን እየተዳደልን የምሥራች የምንባባልበት ወቅትም የክረምቱ ጊዜ አልፎ ዝናቡ/ባህር ሲጎድል ነው፡፡[2]
ይህ በዋናነት የልጃገረዶች በዓል ኾኖ፥[3] የሚከበረውም በዓመት አንዴ፣ በመባቺ ቀን ላይ (የዘመን ወለወጫ፣ የወር መጀመርያ ቀን) ነው፡፡ ምንም እንኳ የኦሮሞ ዘመን መለወጫ ከመስከረም ጥቂት ቀደም ብሎ (ነሐሴ አጋማሽ አከባቢ) ቢኾንም ይህ በዓል የአዲስ ዓመት መቀበያ ነውና የዚህ ደስታ ማብሰሪያ ቄጤማ በልጃገረዶች አማካይነት የሚታደልበት ቀን ነው፡፡ ልክ እንደ ሌላው ኹሉ ከዚህ በዓል በፊት የጳጉሜን አምስት ቀናት በኦሮሞም ዘንድ የታወቁ ናቸው፡፡[4]
ሥርዓቱ፡- በዋዜማው ''Allaadduu buqqisaa'' (ቀጤማ ነቀላ) ይደረግና ሲገመድ አድሮ በማግሥቱ ሴቶች አምረውና ደምቀው ከየቦታው ተሰባስበው በአንድ ላይ እየዘፈኑ በየቤቱ እየዞሩ አበባ ይበትናሉ፣ የቀጤማ ጉንጉን ያድላሉ፡፡ ባለቤቶቹም ልዩ ግብዣ ያደርጉላቸዋል፣ ጠጉራቸውን ቅቤ ይቀቡላቸዋል፡፡[5] በዚህች ቀን ማንም እነዚህን ልጃገረዶች ሊያስቀይም አይሞክርም፤ እነርሱ በዕለቱ ‹‹ቅሩባነ እግዚአብሔር ናቸው›› ተብሎ ስለሚታመን ቢራገሙም ቢመርቁም ፈጥኖ ይሰማላቸዋልና! እንዲያውም የሚገርመው ለረጅም ጊዜያት ልጅ አጥተው የኖሩ ካሉ ልጃገረዶቹ ሲመጡ ይሳሉላቸውና ‹‹ይስማሽ›› ከተባሉ ይወልዱ እንደነበር በእርግጠኝነት የሚናገሩ አሉ፡፡
አሁንም እንጠይቅ፡- መባቺ እና ይህ በዓል በአንድ ቀን መግጠሙ የዘመን መለወጫነቱ በቂ ምስክር አይደለምን? እነርሱ በዚህ መልኩ ባያብራሩትም ይህ በዓል በቄጤማ ማብሰር ታጅቦ መከበሩ ‹‹ማየ አይኅ ጎደለ›› ከሚል ታሪክ ጋር አይናበብ ይኾንን? (ዘፍ.8፥11) የልጃገረዶች በዓል መኾኑና በዘፈናቸው መድመቁስ ከወለተ ሄሮድያዳ ታሪክ ጋር አይገናኝ ይኾን? (ማቴ.14፥6) የሚሉት ሊጤኑ የሚገባቸው ነጥቦች ናቸው፡፡
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
#አንብቡ! #ገንቢ_አስተያየቶችንም_ከበሳል_ትችቶች_ጋር_ስጡ! #ስድብ_በባህል_ነውር_በሃይማኖት_ደግሞ_ኃጢአት_ነውና_እንተወዉ! #እውነት https://www.facebook.com/ewnetmediapage የሚለውን ገጻችንን #Like በማድረግ ቤተሰቦቻችን ሁኑ! ለሌሎችም #Share በማድረግ ጽሑፎችን እንዲያነቡ፣ እንዲቀላቀሉንም ጋብዙ!
#በቴሌግራም ቻናላችንም ይከታተሉን https://t.me/ewnetmedia
#አውነትን_በመግለጥና_ሐሰትን_በማጋለጥ_የሀገርን_ሰላምና_የሕዝብን_አንድነት_ለመጠበቅ_እንትጋ!
[1] የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፤ 1992 ዓ.ም፣ ገጽ.36፡፡
[2] ሞገስ ዕቁበ ጊዮርጊስ (ሊቀ መዘምራን)፤ መርሐ-ጽድቅ ባህለ ሃይማኖት፤ 1989 ዓ.ም፣ ገጽ.68፡፡
[3] በአንዳንድ ቦታዎች ወንዶችም ቆነጃጅቱን የሚያጅቡበት (የሚሳተፉበት) ኹኔታ አለ፡፡
[4] ጀቤሣ ኤጄታ (ባላምበራስ)፤ የኦሮሞ ብሔር ባህልና አጭር ታሪክ (ገጽ.104)፡፡
[5] ዝኒ ከማሁ (ገጽ.107)፡፡
