EwnetMedia 2022

EwnetMedia 2022

EwnetMedia

‹‹ገኒ›› እና ‹‹ታቦሬ››፡- ከብቶችና እረኞቻቸው የሚነግሡባቸው በዓላት!

==================================

(1)      Gannii (ገኒ) ወይም Jaarii Loonii (ጃሪ ሎኒ)

በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ ‹‹ገኒ›› የከብቶች በዓል በመባል ይታወቃል፤ ከብቶችን ፈጥሮ ለሰጣቸው አምላክ ምስጋና የሚያቀርቡበት፡፡ በዕለቱ ከብቶች አይታለቡም፤ በዓላቸው ነውና ጥጆች በነጻ ይጠባሉ፡፡ የሚከበረውም በታህሣሥ ወር ውስጥ ነው፡፡ በእርግጥ አንዳንዶች ጊዜውን ኅዳር ውስጥ በማድረግ ‹‹ማረማ ሎኒ›› (የከብቶች ማርያም) ይሉታል፡፡[1] የበዓሉ መከበር ዋና ዓላማ ከብቶች እንዲረቡ፣ ሟርት እንዳያገኛቸው፣ እንዳይቀጭጩ፣ወዘተ. ለመመረቅ ነው፡፡[2]  

ሥርዓቱ፡- አዲስ የከብቶች በረት በሰፊው ይሠራና በለምለም ቅጠል ዙርያው ይሸፈናል፡፡ በበረቱ መሃልም ከሦስት መዓዛማ ዕጽዋት የተውጣጣና በአንድ የተገመደ እርጥብ እንጨት እንዲቆም ይደረጋል፡፡ ጎንፎም በበረቱ ውስጥ ይጎነፋል፡፡ ከብቶች ያለ ወትሮአቸው በቀን ይመጡና በተዘጋጀው የሐረግ መሹለኪያ በኩል አልፈው ወደ በረታቸው ይገባሉ፡፡ በየዓይነቱ ከሚዘጋጀው መብልና መጠጥ በመጠኑ በበረቱ መሃል በቆመው እርጥብ እንጨት ሥር ያኖራሉ፡፡ በከብቶቹም ላይ የቀለጠ ቅቤ እየተረጨባቸው ይመረቃሉ፡፡ ከዚያም የተረፈውን እየበሉና እየጠጡ ከብቶችን የሚያወዳድሱ (ለእነርሱ ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር የሚገልጡባቸው) ዜማዎችን እየተቀባበሉ ያዜማሉ፡፡[3] ለመኾኑ ከብቶች ለምን በዓል ይከበርላቸዋል? ለምን የከብቶች በዓል ኾነ? ለምንስ ‹‹ገኒ›› ተባለ? ጊዜው ታኅሣሥ መኾኑስ ምን ያመለክታል? ጎንፎውና እርጥቡ እንጨት በበረቱ መካከል የሚቀመጡትስ ለምንድን ነው? የሚሉት በአንክሮ ሊጤኑ የሚገባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ እነርሱ ግን ስያሜውና በዓሉ ከጌታ ልደት ጋር ይገናኝ ይኾን ለሚለው መላምት የሚያውቁት ነገር የለም፡፡

(2)      Taaboree (ታቦሬ)

ታቦሬ ደግሞ፥ በዋናነት የእረኞች (የወንዶች ልጆች) በዓል ነው፡፡ ሓገያ በሚባለው (ነሐሴ) ወር ውስጥ የሚከበር ነው፡፡ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የኾኑ ልጆች በአንድነት ይሰበሰቡና በእርጥብ አጣና ጊዜያዊ ጎጆ ይቀልሳሉ፡፡ በጎጆው ፊት ለፊትም ትንንሽ እርጥብ እንጨት ያቆሙና በወጉ ተሰናድቶ እስከ ጎጆአቸው ከሚመጣላቸው ጎንፎ፣ ቅቤ፣ ጠላ፣ ወተት፣...በማፍሰስ ‹‹የፈጠርከን አምላክ አሳድገን፣ ለወግ ለማዕረግ አብቃን›› ብለው ይጸልዩና እስከሚበቃቸው ሲበሉ ሲጠጡ ይውላሉ፡፡[4]

ዕለቱ፥ የክርስትና አባትና እናት የታቦሬ ዳቦ (ልዩ ሙልሙል) ይዘው ልጆቻቸውን የሚጠይቁበት ቀንም ነው፡፡ በዚህ ዕለት ልጆቹን የማይጠይቅ አባት፣ እናት የመባል ሞራል እንደሌለው በማኅበረሰቡ ዘንድ ይታመናል፤ ልጆችም በጉጉት የሚጠብቁት ስጦታቸው ነው፡፡ በክርስትና ትውፊትም፥ ጌታ ብርሃነ መለኮቱን በገለጠባት በደብረ ታቦር ዕለት በዱር በሜዳ ከብቶችን ይጠብቁ የነበሩት እረኞች ከፍተኛ ብርሃን ከማየታቸው የተነሣ ያልመሸ መስሎአቸው በተለመደው ሰዓት ወደ ቤታቸው እንዳልተመለሱ፣ ከዚህም የተነሣ ቤተሰቦቻቸው ሙልሙል ዳቦ ይዘው ይፈልጓቸው ዘንድ እንደወጡ፣ ይኽም ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ ኖሮ የባህላችን አካል ሊኾን መቻሉ ይተረካል፡፡

እስካሁን ድረስ እንዳየናቸው በዓላት ኹሉ ለምን ታቦሬ ተባለ?[5] ለምንስ ይከበራል? ለምን በዳስ ውስጥ ኾነ? ለሚሉ ጥያቄዎች በቂ ምላሽ ማግኘት አልተቻለም እንጂ ብዙ ያልተገለጡ ነገሮችን ማገናዘብ እንደሚቻል ይገመታል፡፡ ያም ኾነ ይኸ ግን፥ የስም ስያሜውም ኾነ አጠቃላይ ሥርዓቱ የሚያስታውሰን ነገር ይኖረዋል፡- በብሉይ ኪዳን በ7ኛው ወር፣ በ15ኛው ቀን እህል ከተከማቸ በኋላ የእስራኤል ልጆች ሰባት ቀን በዳስ ውስጥ ተቀምጠው አምላካቸውን ያመሰግኑ ነበር፤ ይህ በዓል በዓለ መጸለት (የዳስ በዓል) ይባል ነበር (ዘሌዋ.23፡33-43፤ ዘኁ.29፡12፤ ዘዳ.16፥13፤ ነህ.8፥14-17)፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ስያሜው፣ የእረኞች በዓል መባሉ፣ በነሐሴ ወር እና በዳስ ውስጥ መከበሩ ምሥጢረ መለኮት ገሃድ የኾነበትን የሐዲስ ኪዳን ዕለት (በዓለ ደብረ ታቦርን) አይነግረን ይኾን?

~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~

#አንብቡ! #ገንቢ_አስተያየቶችንም_ከበሳል_ትችቶች_ጋር_ስጡ! #ስድብ_በባህል_ነውር_በሃይማኖት_ደግሞ_ኃጢአት_ነውና_እንተወዉ! #እውነት https://www.facebook.com/ewnetmediapage የሚለውን ገጻችንን #Like በማድረግ ቤተሰቦቻችን ሁኑ!  ለሌሎችም #Share በማድረግ ጽሑፎችን እንዲያነቡ፣ እንዲቀላቀሉንም ጋብዙ!

#በቴሌግራም ቻናላችንም ይከታተሉን https://t.me/ewnetmedia

#አውነትን_በመግለጥና_ሐሰትን_በማጋለጥ_የሀገርን_ሰላምና_የሕዝብን_አንድነት_ለመጠበቅ_እንትጋ!


[1] Dirribii; Ilaalcha Oromoo (2009:119).

[2] ቃለ-መጠይቅ (ወ/ሮ ሀንገራሼ)፡፡

[3] ጀቤሣ ኤጄታ (ባላምበራስ)፤ የኦሮሞ ብሔር ባህልና አጭር ታሪክ (ገጽ.108)፡፡

[4] ጀቤሣ ኤጄታ (ባላምበራስ)፤ የኦሮሞ ብሔር ባህልና አጭር ታሪክ (ገጽ.107)፡፡


[5] በእርግጥ አንዳንድ የኦሮሞ ፖለቲከኞችና የጎሣ ታሪክ ጸሓፍት የስያሜውንም ምንጭ ወደ ኦሮሞነት ለመሳብ ሞክረዋል፡- ‹‹ታቦሬ›› የተባለው ከታቦር ተራራ የተወሰደ ሳይኾን ‹‹ታኣ-ቦሬ›› (የነገው አደራ ተቀባዮች፣ የተስፋው ትውልድ) ለማለት ነው ብለው፡፡ (ታቦር ዋሚ፤ የውገና ድርሰቶችና የታሪክ እውነቶች፤ 2006 ዓ.ም፣ ገጽ. 216)




Report Page