EwnetMedia 2022

EwnetMedia 2022

EwnetMedia

እንደ ባዕድ አምልኮ የተፈረጁ የክርስትና ጥንታውያን እሴቶች በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ!

==================================

(1)        Booranticha (ቦረንቲቻ) (ክብረ ‹‹ብኩርና››)

የኦሮሞ ቀዳሚያን ‹‹አባቶች›› (ግንዶች) የሚባሉት ሁለቱ ወንድማማቾች ናቸው፡- ቦረና (ታላቅ) እና ባሬንቱ (ታናሽ)፡፡ በኦሮሞ ዘንድ ደግሞ ብኩርና ትልቅ ክብር ስለሚሰጠው የታላቁ (የቦረና) ልዩ ክብር ‹‹Booranticha›› በሚል በዓል ያከብርለታል፡፡[1] ከኦሮሞ ሥርዓቶች፣ መንፈሳውያት ጉባኤያትና ሥርዓተ አምልኮዎች ኹሉ የቦረና ልዩ ክብርና ተሰሚነት አለው፤ ቦረና በኩር ነውና የዋቃና አያና ልዩ ስጦታዎች በዋናነት ለትውልድ የሚተላለፉት በእርሱ በኩል ስለኾነ፡፡ በበዓሉ ዕለትም የሚለበሱት አልባሳት የዋቃ ምሳሌነት በሚሰጠው ጥቁር ቀለም (ጥለት) ያጌጡ ልብሶች (የወንዱ ቡሉኮ እና የሴቷ ቆሎ/ሳባታ የሚባሉ) ሲኾኑ ለሥርዓቱ የሚታረደው ኮርማም እንዲሁ ጥቁር ነው፡፡[2] በተለይም፥ በጥቅምት እና በግንቦት እንደሚከበር አዛውንት ይናገራሉ፤ በወራቱ መመረጥ አመክንዮ ላይ ግን ወጥ የኾነ ማብራርያ ለማግኘት አልተቻለም፡፡

የብኩርናን ቦታ (ክብር) ምን ያህል እንደኾነ በኦሪት ውስጥም የምናውቀው ጉዳይ ነው፡- ከአባት ቀጥሎ የቤቱ ኃላፊ፣ ከርስት ሁለት እጅ የሚወርስ፣ የቤተ ክህነት እጩ፣ የቤተ መንግሥትም አልጋ ወራሽ ነው (ዘፍ.25፡31፤ 42፡22፤ ዘዳ.21፡17፤ 2ዜና.21፡3)፡፡ በሐዲስ ኪዳንም ቢኾን፥ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የድንግል ማርያም ‹‹የበኩር ልጅ›› ሲለው (ማቴ.1፥25፤ ሉቃ.2፥7) ሌላ ተከታይ እንዳለው ለማመላከት ሳይኾን ታላቅነቱን፣ ክብሩን ለመግለጽ እንደኾነ መተርጉማን ይገልጻሉ፡፡ 

(2)        Maarama  (ማረማ)

ኦሮሞዎች የቅዱሳንን ስም በሚመስሉ ስያሜዎች የሚያከብሯቸውም በዓላት ብዙ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንደኛውና ዋነኛው ‹‹ማረማ ፉርማ›› ሲኾን በዓሉ የሴቶች ነው፤ ወንዶች አይካፈሉትም፡፡ በእናት መሪነት ስለሚከናወን እና የሴቶች በመኾኑም ‹‹አቴቴ›› ይባላል፡፡[3] ወንዶች ለምን በዓሉን እንደማይካፈሉ ሲጠየቁ ‹‹እነርሱ የማራማን ጣዕም የት ያውቁና፣ አምጠው አያውቁ!›› በሚል አግራሞት ይመልሳሉ የማኅበረሰቡ አዛውንት፡፡[4] ማራማ የወላድ አያና እንደመኾኑ መጠን[5] በዚህ በዓል ላይ የሚለማመኑት በዋናነት ልጅ መስጠትም ሆነ መንሳት የሚቻላት ማረማን ነው፡፡

እንደ አብዛኛው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ኹሉ ኦሮሞዎችም፥ አንዲት ሴት ስታረግዝ፡- ‹‹በማርያም እጅ ተያዘች!›› ይላሉ፤ ስታምጥ፡- ‹‹ማርያም! ማርያም!›› እያሉ ይማጸናሉ፤ ስትወልድ ደግሞ፥ ‹‹እንኳን ማርያም ፈታችሽ›› ይባባላሉ፡፡ እንደ እነርሱ እምነት ማርያም ፈቅዳ ስለምትፈታ ነው እንጂ እርግዝና (ምጥ) ከባድ እስራት ነው፤ እንዲህ ባለ በዓል ከተማጸኗት ትፈታለች፣ አለበለዚያ እስራቱን ወደ ሞት ትቀይረዋለች፡፡ ምጡ ኹሉ አልፎ ልጅ ሲወለድ መረማ በማኅበረሰቡ አዛውንት የምትመሰገንበት ዜማ አላት፡- “Kan dhiiga mucaa gootu; kan hiika dhugaa gootu; kan Maariyamiin namaa gootu; Haati ofii namaa hin gootu!” (ደምን አርግታ ሕጻን የምታደርግ፣ በሰላም የምትገላግል ማርያም ናት! ማርያም ለሰው ልጅ የምትሰጠውን ስጦታ እናት እንኳ መስጠት አይቻላትም!) የሚል ነው፡፡ በመጨረሻም፥ ‹‹ማርያም በሽልም ታውጣሽ!›› ብለው ይሰናበታሉ፡፡

የበዓሉ አከባበር፡- ሴቶች ተሰብስበው ልዩ ልብስ (‹‹ቆሜ›› የሚባለውን የማራማ ዥጉርጉር ልብስ) ለብሰው፣ ጠላ ሹመው፣ እናት በግ አዘጋጅተው (አርደው) ያከብራሉ፡፡ ዘካሪዋ እናት እንደ ዝክረ ሰንበቱ ሁሉ ''Maaramaaf nan dhaapha'' (‹‹ለማርያም ቆሜአለሁ››) ስትል ሌሎች ሴቶች የተሾመችውን ምንቸት ዙረው ይቀመጡና ''Maaramiin siif ha dhaabattu'' (ማርያም ትቁምልሽ) ይሏታል፡፡ ከዚያም ሰርዶ ቀልጦ በተዘጋጀው ቅቤ ውስጥ እየነከረች ልጆችን ጨምሮ በሁሉም ግንባር ላይ ታስነካለች፡- ይህንን ''mijuu'' (ሚጁ) ይሉታል፡፡ ስትባርካቸውም፡- ''guddadhu, adda jabaadhu, of-koli'' ትላለች፤ በጥሬ ትርጉሙ ‹‹እደግ፣ ግንባረ ጠንካራ ሁን፣ እንከን አያግኝህ›› ማለት ነው፡፡[6] ከበሉና ከጠጡ በኋላ ማራማን በዜማ ያመሰግኗታል፡፡[7]

ምንም እንኳ ስያሜውም፣ በዕለቱ የሚዜመውም ኾነ ድርጊቱ ኹሉ ድንግል ማርያምን የሚያሳስብ ቢኾንም፥ አንዳንዶች ግን ከባህልና ከባዕድ አምልኮ ጋር ለማያያዝ ጥረት ሲያደርጉ ይታያል፡፡

(3)        Garanfasa (ጋረንፈሳ)

ገረንፈሳ ስያሜው ከምን እንደመጣ ለማብራራት ይከብዳቸዋል፤ ብቻ ቀኑ በማባቺ አምስተኛ ቀን ላይ እንደኾነ ኹሉም ይስማሙበታል፡፡ ለምሳሌ፡- መባቺ ዓርብ ከዋለ ገረንፈሳ ማክሰኞ ይውላል ማለት ነው፡፡ ይህ በዓል በዋናነት ለሕጻናት ጤንነት፣ ለጥጃና ለላም መፋፋት እንደሚከበር የሚናገሩ አሉ፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚያደርጉት በዚህ ዕለት ላሞች እንኳ የማይታለቡ (ጥጆች በነጻ የሚጠቡበት) ቀን መኾኑን ነው፡፡ በዕለቱ እርሻም ሆነ ሌላ ሥራ አይሠራበትም፤ የግዝት በዓል መኾኑ ነው፡፡ በዓመት ውስጥ በሰባት ወር አንዴ ገረንፈሳ እና ሰንበታ የሚደራረቡበት ኹኔታ ስለሚፈጠር በእርድ እንደሚከበር አዛውንቱ ይናገራሉ፡፡ ይህ ተጨማሪ ጥናት ቢጠይቅም ቢያንስ ከሚከበርበት ቀንና ከስያሜው መመሳሰል የተነሣ የኦሮሞ ገረንፈሳ ‹‹ገብረ መንፈስ ቅዱስ›› እንደኾነ ይገመታል!  

(4)        Mikaa'ela (ሚካኤላ)

ሚካኤላ ደግሞ በገረንፈሳ ሳምንት ይከበራል (የመባቺ ዐሥራ ሁለተኛ ቀን መኾኑ ነው)፡፡ በየወሩ ቀለል ባለ ኹኔታ ከሚከበረው በተጨማሪ በዓመት ሁለት ጊዜ (ማለትም የኅዳር እና የሰኔ ሚካኤላ) በልዩ ዝክር (በእርድ) የሚከበሩ ናቸው፡፡ ከዚህ ባለፈ ‹‹ሚካኤላ ማን ነው? ለምንስ ይከበራል? ለምንስ የኅዳርና የሰኔ ቀናቱ የተለዩ ሊኾኑ ቻሉ?›› ለሚሉት ጥያቄዎች የአዛውንቱ ምላሽ ''qooda isaati'' (‹‹ሥርዓቱ ነው››) ወይም ''duruu kan ture dha'' (‹‹ከጥንትም የነበረ ልማድ ነው››) የሚል ነው፡፡ ያም ኾነ ይህ ሚካኤላ ‹‹ሚካኤል አይደለም›› ብሎ የሚከራከር ካለ፥ ስያሜው እንዴት ሊመሳሰል ቻለ? ለምን በገረንፈሳ ሳምንት ይከበራል? የኅዳሩና የሰኔውስ ለየት ተብሎ መከበሩ ለምንድን ነው? ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ 

(5)        Madina (መድና)

ለኦሮሞ መድና ሰብሎችን ከመብረቅ፣ ከዐውሎ ነፋስና ከበረድ የሚጠብቅ አምላክ ነው፡፡ ስለዚህም (በግምት ነሐሴ አጋማሽ አከባቢ) ገበሬው ገንፎ በቅቤ አዘጋጅቶ ይዞ በየማሳዎቹ ይዞርና እንደ ወጉ እየቆነጣጠረ ከወረወረባቸው በኋላ በአንድ ጥላ ሥር ተቀምጦ ‹‹ተረፈ መሥዋዕቱን›› ይበላል፡፡ እርድም የሚካሄድበት ኹኔታ አለ፡፡ ይህ በአንዳንድ ቦታዎች፥ ‹‹ማረማ ሀገያ›› (የነሐሴ ማርያም) እየተባለ ይከበራል፡፡[8]

ዋናው ዓላማ ሰብሉ ያለ ምንም ችግር በዝናብ በቅሎ፣ በፀሐይ በስሎ ወደ ጎተራ ይገባ ዘንድ መማፀን ነው፡፡ ስለዚህም ከመድና ቁጣ ለመዳን የግድ ይኸን በዓል ማክበር ያስፈልጋል፤ በዕለቱ ምንም ዓይነት ሥራ አይሠራም፡፡ ጉዳዩ በተጨማሪ ምርምር መረጋገጥ ቢኖርበትም መድና የሚለው ቃል ‹‹መድኅን››፣ ‹‹መድኃኔ ዓለም›› ከሚሉት ጽንሰ አሳቦች ጋር ተያያዥነት እንደሚኖረው ይገመታል፡፡

(6)        Addaam  (አዳም)

ቃለ-መጠይቅ የተደረገላቸው አዛውንት ‹‹አዳም›› የሚባል የኦሮሞ በዓል መኖሩን እንጂ የስያሜውን የትመጣ እንዲሁም የመከበሩን መነሻ በውል አያስረዱም፡፡ ባላምበራስ ጀቤሣ ግን በመጽሐፋቸው ላይ፡- ‹‹ኦሮሞዎች እግዚአብሔር የመጀመርያውን ሰው አዳምን እንደፈጠረና ሰው ኹሉ ከእርሱ እንደመጣ ያምናሉ፤ ስለዚህም፥ ‹አዳም› ብለው በስሙ የሚያከብሩት በዓል አላቸው፡፡›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡[9]

የባላምበራስን ሐሳብ እውነት የሚያደርገው ደግሞ፥ በማኅበረሰቡ አባላት ዘንድ በዓሉ የሚከበርበት ጊዜ (ዕለት) ነው፡፡ አዳምን የሚያከብሩት በጸሎተ ሐሙስ ሳምንት (ከፋሲካ ቀጥሎ ባለው ሐሙስ) ነው፡፡ በውኑ ይህ ዕለት ዛሬም በቤተ ክርስቲያናችን ከሚከበረው የአዳም በዓል ጋር አንድ ቀን አይውልምን? ወይስ በአጋጣሚ ተገናኝቶ?!

ስለመከበሩ ምክንያት ወ/ሮ ሀንገራሼ እንዲህ ሲሉ ይገልጻሉ፡- ‹‹የአዳም እናት[10] ባለፈው ዓርብ[11] ለጸሎት አጎንብሳ ልመናዋ ተሰምቶላት ቀና ያለችው በዚህ ቀን ነው ብለው አያቶቻችን ስለነገሩን ‹አዳም› ብለን እናከብርላታለን፤ ዋቃ እርሷን ስለሰማት እናመሰግነዋለን፣ እኛንም እንዲሰማን ደግሞ እንለምነዋለን፡፡›› 

አከባበሩ በአንድነት በመኾን፣ የተለያዩ እህልና መጠጥ ዓይነቶችን በማዘጋጀት ለወጉ የሚኾነውን ወደ ኢሬሣ (መሠዊያ) ከበተኑ (ካፈሰሱ) በኋላ በመመገብ ነው፡፡ ይህ በዓል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ታስቦና ተከብሮ ቢገኝ እንጂ በማኅበረሰቡ ዘንድ ብዙም አይስተዋልም፡፡ ኦሮሞ ግን ሲያከብረው ነበር፤ ዛሬም አሻራው አልጠፋም፡፡ ታዲያ ይህ ማኅበረሰብ በሆነ ሰዓት ከማንም የተሻለ ስለ ክርስትና እና በዓላቱ ግንዛቤ እንደነበረው ፍንጭ አይሰጥምን?!

~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~

#አንብቡ! #ገንቢ_አስተያየቶችንም_ከበሳል_ትችቶች_ጋር_ስጡ! #ስድብ_በባህል_ነውር_በሃይማኖት_ደግሞ_ኃጢአት_ነውና_እንተወዉ! #እውነት https://www.facebook.com/ewnetmediapage የሚለውን ገጻችንን #Like በማድረግ ቤተሰቦቻችን ሁኑ!  ለሌሎችም #Share በማድረግ ጽሑፎችን እንዲያነቡ፣ እንዲቀላቀሉንም ጋብዙ!

#በቴሌግራም ቻናላችንም ይከታተሉን https://t.me/ewnetmedia

#አውነትን_በመግለጥና_ሐሰትን_በማጋለጥ_የሀገርን_ሰላምና_የሕዝብን_አንድነት_ለመጠበቅ_እንትጋ!


[1] Duudhaa (1998:9)፤ ታቦር ዋሚ፣ የውገና ድርሰቶችና የታሪክ እውነቶች፤ 2006 ዓ.ም፣ ገጽ.196-197፡፡

[2] እዚያው፡፡  

[3] Dirribii, Ilaalcha Oromoo (2009:119)::

[4] ቃለ መጠይቅ (ወ/ሮ አንገራሼ)፡፡

[5] Duudhaa (1998:12).

[6] ቃለ መጠይቅ (ወ/ሮ ሀንገራሼ)፡፡

[7] ጀቤሣ ኤጄታ (ባላምበራስ)፤ የኦሮሞ ብሔር ባህልና አጭር ታሪክ (ገጽ.104)፡፡

[8] Dirribii, Ilaalcha Oromoo (2009:120).

[9] ጀቤሣ ኤጄታ (ባላምበራስ)፤ የኦሮሞ ብሔር ባህልና አጭር ታሪክ (ገጽ.101)፡፡

[10] እርሳቸውም ሲሉ ሰምተው እንጂ ማንን ለማለት እንደፈለጉ አላወቁም፡፡ 

[11] በስሌቱ መሠረት ዕለቱ ስቅለት ላይ ይውላል፡፡ 



Report Page