EwnetMedia 2022

EwnetMedia 2022

EwnetMedia

የኦሮሞ ‹‹የበዓላት ኹሉ ንጉሥ››፡- Masqala (መስቀላ)!

==================================

Masqala ‹‹መስቀል›› ማለት ነው፡፡ በሌላ ስያሜው ‹‹gubaa›› ተብሎም ይጠራል፤ በቁሙ ‹‹ማቀጣጠል›› የሚል ትርጉም ሲኖረው ከደመራ (ችቦ) ማብራት ሥርዓት ጋር ተያያዥነት እንዳለው ግልጽ ነው፡፡ ምንም እንኳ መስቀል በመላው ሀገራችን በከፍተኛ ኹኔታ የሚከበር ቢኾንም በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ ደግሞ፥ “Masqala mootii ayyaanaa” (መስቀል የበዓላት ንጉሥ) የሚል ልዩ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ ይኽ ‹‹የበዓላት ንጉሥ›› በባህሉ፥ ከክረምቱ ጨለማ ወደ ፀሐይ ብርሃን የሚወጣበት፤ አዳዲስ እህሎች ደርሰው ለመጀመሪያ ጊዜ የሚቀመሱበት፤ ዕለቱም ለሰዎች ኹሉ የጥጋብና የደስታ ከመኾን አልፎ እንስሳት እንኳ የተዘጋጀላቸውን ልዩ የመስቀል ግጦሽ (Kaloo Masqalaa) የሚበሉበት ዕለት ነው፡፡[1] በሃይማኖቱም፥ ድኅነተ ዓለም የተፈጸመበት መስቀል የሚዘከርበት ነውና ታላቅ ዕለት ነው፡፡

ምንም እንኳን በበዓሉ ላይ ባህላዊ ድርጊቶች የሚፈጸሙበት ቢኾንም የሥርዓቱ ይዘት ግን ከሃይማኖታዊ ጭብጡ ጋር ተመሳሳይ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የማኅበረሰቡ አዛውንት ግን ለምን ስያሜው መስቀላ ተባለ? ለምንስ ይከበራል (ዓላማው)? ወዘተ ለሚሉ ጥያቄዎች በሃይማኖታዊ መረጃ የተደገፈ አመክንዮ ለማቅረብ ይቸገራሉ፡፡ በጥቅሉ፥ ‹‹ከክረምት ጨለማ ወጥተን ወደ ፀሐይ ብርሃን የወጣንበት ስለኾነ፥ ከጥንት አባቶቻችን የመጣ በዓል ነው›› ይላሉ፡፡   

ሥርዓቱ፡- በመስቀላ ዋዜማ ''mucecoo'' (ደመራ እንደማለት ነው) ይከበራል፡፡ በዚህ ቀን የተለያዩ ዓይነት ዕጽዋትን (እርጥቡን ቆርጠው) ያመጡና በአንድነት በማሰር በቤታቸው በር ግራና ቀኝ ያስደግፋሉ፡፡ ወፈር ያሉትን ደግሞ ፈልጠው በእሳት ላይ ይደረድሯቸዋል፡፡ ሴቶቹም እንጀራ በቅቤ ያዘጋጁና በመጠኑ ወደ ደመራውና ወደ መሥዋዕቱ ምሶሶ ከፈሰሰ በኋላ ቤተሰቡ ሁሉ አምላካቸውን እያመሰገኑ ይበላሉ፣ ይጠጣሉ፡፡ በማግስቱ ጠዋት የአከባቢው መንደርተኞች ችቦ አብርተው በአንድ ቦታ ያቀጣጥላሉ፡፡ ሴቶችም ጠላና ዳቦ ወደ አመዱ ቦታ ያመጡና እንደተለመደው በአመዱ ላይ ትንሽ ይፈስና ይበላል፣ይጠጣል፡፡

በዚህ ሥርዓት ውስጥ የሚገርመው ጉዳይ ሊጥ በእርጥብ ቅጠል ጠቅልለው በተቀጣጠለው ችቦ ውስጥ ያስገቡና ሲበስል ርሙጦውን ቆራርሰው ለከብቶች ያበላሉ፤ እንደ እነርሱ እምነት ይህ ‹‹የከብቶችን ሆድ ቁርጠት ይከላከላል››፡፡ በተጨማሪም ''tuufoo'' የሚሉት አደይ አበባ ተነቅሎ ይመጣና ሥሩ በፍሙ ከሞቀ በኋላ ለኹሉም ሰው ይታደላል፡፡ ኹሉም በጥርሱ እያኘከ ሰውነቱን ያብስበታል፤ ይህ ደግሞ ይላሉ፥ ‹‹እባብ እንዳይነድፍ ይከላከላል››![2] የችቦውን አመድም በግንባራቸው የሚቀቡ እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በመጨረሻም፥ ከነክርስትና ስያሜውና ጭብጡ በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ የሚከበረውን መስቀልን ‹‹የዋቄፈና እምነት በዓል›› ለማድረግ የሞከሩ ጸሓፍትን ስንመለከት በእጅጉ እንገረማለን፡- ‹‹በዋቄፈታዎች ዘንድ መስቀላ ወይም ዳሞቲ የአዲስ ዓመት መጀመሪያ ቀን ነው፡፡…ኹሉም ነገር ከውጪ ካልመጣ ከሚሉት የሐበሾች አስተሳሰብ በስተቀር የመስቀልን በዓል ከክርስቶስ መስቀል መገኘት ጋር የሚያገናኝ ነገር የለም›› ያሉ አሉና፡፡[3] እኚህ ጸሓፊ ‹‹ኹሉም ነገር ከውጪ ካልመጣ የሚሉ…›› በሚል ሌላውን አካል በወቀሱበት በዚያው የመጽሐፋቸው ገጽ ላይ የመስቀል በዓልን ከፈረንጆቹ ቦን ፋየር (bonfire) እና ሆሊ ፋየር (holy fire) ጋር ማያያዛቸው ደግሞ ይበልጥ ትዝብት ላይ ይጥላቸዋል፡፡ እናም፥ በማሰላሰያ ጥያቄ ሐሳቡን እንቋጨው፡- የኦሮሞ ‹‹መስቀላ›› ሌሎች እንደሚሉት ከመስቀል ጋር የተመሳሰለው በአጋጣሚ ይሆን?! በመስቀላ አመድ የተተኮሰ ቱፎ በማጀክ ሰውነቱን የደባበሰ ሰው ‹‹እባብ አይነድፈውም›› የሚል እምነት ያለው ማኅበረሰብ ‹‹ሰይጣን በመስቀሉ ይሸነፋል›› ብሎ ከሚያምነው በአገላለጽ እንጂ በምን ይለያል?![4]

~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~

#አንብቡ! #ገንቢ_አስተያየቶችንም_ከበሳል_ትችቶች_ጋር_ስጡ! #ስድብ_በባህል_ነውር_በሃይማኖት_ደግሞ_ኃጢአት_ነውና_እንተወዉ! #እውነት https://www.facebook.com/ewnetmediapage የሚለውን ገጻችንን #Like በማድረግ ቤተሰቦቻችን ሁኑ!  ለሌሎችም #Share በማድረግ ጽሑፎችን እንዲያነቡ፣ እንዲቀላቀሉንም ጋብዙ!

#በቴሌግራም ቻናላችንም ይከታተሉን https://t.me/ewnetmedia

#አውነትን_በመግለጥና_ሐሰትን_በማጋለጥ_የሀገርን_ሰላምና_የሕዝብን_አንድነት_ለመጠበቅ_እንትጋ!


[1] Naahimii Fayyisaa; Ortodooksii Oromiyaatti; 2010:112.

[2] ጀቤሣ ኤጄታ (ባላምበራስ)፤ የኦሮሞ ብሔር ባህልና አጭር ታሪክ (ገጽ.105)፡፡

[3] ድርቢ ደምሴ ቦኩ፤ የኦሮሞ የማንነት ታሪክ፤ 2007 ዓ.ም፣ ገጽ.259፡፡

[4] ‹‹...በመስቀሉ ጥልን ገድሎ...ሰላምን ሰጠን...›› (ኤፌ.2፡16)፤ ‹‹ዓለሙን ሁሉ የሚያስተው ዲያቢሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ...›› (ራእ.12፡9)፡፡




Report Page