EwnetMedia 2022
EwnetMedia
‹‹ስማኝ-ልስማህ›› እየተባባሉ መደማመጥ (Ilaafi Ilaamee)
==================================
በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ ‹‹ Ilaafi Ilaamee›› (‹‹ስማ-ልስማህ›› እያሉ መደማመጥ) ከነበሩና ካሉት መልካም እሴቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ ይኽም፥ ተነጋግሮ ለመግባባት ያላቸውን ፍላጎት እና በተለያዩ አካላት መካከል የሚኖሩ ልዩነቶችም በሐሳብ የበላይነት ብቻ እንደሚፈቱ የሚጠቁም ነው፡፡ አላስፈላጊ የስድብ ቃላት መወራወር፣ ውስጥ ለውስጥ መናቆር (በስውር ሴራ መጎዳዳት)፣ ከዚያም ሲያልፍ መደባደብና መገዳደል የማኅበረሰቡ እሴት አልነበረም፤ አይደለምም ማለት ነው፡፡ አንዱ፥ “ilaa…” (ስማ፣ አድምጠኝ) ብሎ ሐሳቡን ያቀርባል፤ ሌላኛውም በተራው፥ “ilaamee…” (እኔ እንደሰማሁህ አንተም ስማኝማ) እያለ ምላሹን ይሰጣል፡፡ እንዲህ ዓይነት የመነጋገርና የመደማመጥ ባህልን ያዳበረ ማኅበረሰብ በምንም ኹኔታ ውስጥ አንድነቱ ሊናድ አይችልም! “Waliigalan, alaa galan!”(የተግባባ፣ ከዱር ገባ) የሚለው የማኅበረሰቡ አባባልም ይኸንኑ የሚያረጋግጥ ነው፡፡

ነባሩ የኦሮሞ ማኅበረሰብ ሰውን ከመጣላትና እንደ ጠላት ከማየት በላይ የሚጸየፈው የለም ማለት ይቻላል፡፡ ከማኅበረሰቡ ጋር ተያይዞ የሚታየው ኦዳ (ዛፍ) ራሱ ከመነጋገር ባህሉ ጋር የተገናኘ ነው፡- ማኅበረሰቡ ኦዳ ሥር ተቀምጦ ሲወያይ፣ አለመግባባቶችን ሲፈታ፣ ሕግጋትን ሲያወጣ እንደነበር ታሪኩ ይጠቁመናልና፡፡ በዚህም ሒደትና እሴት ውስጥ አራት ዋና ዋና ቁምነገሮችን እንቀስማለን፡-
(1) ተከባብሮ በመነጋገር መግባባት (Respectful Negotiation)
ሰው ኹሉ እንደ መልኩ ሐሳቡም ይለያያል፤ ይህ በራሱ ችግር አይደለም፡፡ እንዲያውም፥ የሐሳብ ልዩነት መኖር የተለያዩ ምልከታዎችን ስለሚያጎናጽፍ የበሰለና ፍቱን ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ያግዛል፡፡ መሰል የሐሳብ ልዩነቶችን ደግሞ ተከባብሮ፣ በትዕግሥት መነጋገር መቻል ታላቅነት፣ ለማኅበረሰቡም አንድነት የሚበጅ ነው፡፡ ‹‹Ilaa…ilaamee…›› እየተባባሉ መደማመጥ፣ አንዱ የሌላኛውን ሐሳብ ማክበር፣ ተራው እስኪደርስ ጠብቆ የራሱን ምላሽ ማቅረብ ልዩነትን ያጠብባል፤ የሕግ መዋቅራት ዘንድ ለመካሰስ የሚፈጀውን ጊዜና ውጣ ውረድ ይቀንሳል፤ የማኅበረሰቡን ሰላምና መረጋጋትም ያረጋግጣል፡፡
(2) በነጻነት ሐሳብን መግለጽ (Freedom of Speech)
“Ilaafi ilaamee”ሐሳብን በነጻነት ለመግለጽ የሚያግዝ ነው፡፡ ሁለቱም አካላት ሳይሳቀቁ ይናገራሉ፤ የማይስማሙበት አቋም ቢኾን እንኳ ያከብራሉ፡፡ ‹‹ለምን ይህን ተናገርክ?›› ከመባባል ይልቅ፥ የተነገረው ሐሳብ ለምን ስህተት እንደኾነ በተረጋጋ መንፈስ ያጋራሉ፡፡ በዚህ መልክ መነጋገር የቻሉ አካላት ደግሞ ታፍነው ከማጉረምረምና ቂም ከመቋጠር ይተርፋሉ፡፡
(3) እኩልነት (Equal Status)
በዚኽ ሒደት ውስጥ ኹሉም ተናጋሪዎች በመናገር ቅደም ተከተል ይቀዳደሙ እንደሁ እንጂ፥ የበላይ-የበታች የሚባል የደረጃ ክፍፍል (መበላለጥ) የለባቸውም፡፡ የሽማግሌዎችን ሐሳብ ማክበር እጅግ አስፈላጊና ግዴታ ቢኾንም፥ የሕጻናትንና ወጣቶችን ሐሳብ ማግለል ደግሞ ተቀባይነት የለውም፤ ‘ilaa fi ilaamee’ ዕድሜን፣ ሥልጣንን፣ ጾታን፣ የትምህርት ደረጃን፣ ሀብትን፣ ወዘተ. ተገን አድርጎ ሌላውን አካል (እውነትን) መደፍጠጥ ይጸየፋልና፡፡ በእኩልነት ተቀምጦ የማይነጋገር፣ በሌላ ሴራ ሐሳቡን በሌላው ላይ ለመጫንና በስውር ለማጥቃት የሚሞክር ግን [ጠላቱ እንኳ ቢኾን] ሰፉን አላከበረምና ከማኅበረሰቡ አንድነት የተገለለ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ፥ አባ ገዳው እንኳ ሥልጣኑን ተጠቅሞ በጋራ ያልተመከረበትን የውሳኔ ሐሳብ (የራሱን ስሜት) በሕዝቡ ላይ ለመጫን አይችልም፤ የገዳው ሥርዓት የሥልጣን እርከንን የፈጠረው የብዙኃንን ሐሳብ ለመደፍጠጥ ሳይኾን በጋራ የተወሰነውን ለማስፈጸም ይቻል ዘንድ የመሪነት ሚና እንዲጫወቱ ብቻ ነውና፡፡
(4) የጋራ ተጠያቂነት (Shared Accountability)
ነባሩ ኦሮሞ በራሱ ማኅበረሰብ መካከል ሰላምን ለማውረድ ብቻም ሳይኾን የመጣበትን ጠላት ለመመከት ሲያስብ እንኳ አስቀድሞ ‘ilaa….ilaamee’ ብሎ ይመካከራል፤ የእርምጃውን ጥቅምና ጉዳት ያመዛዝናል፡፡ የማኅበረሰቡ አባላት በዚህ መልኩ መክረው ከወሰኑ በኋላ ግን፥ ውጤቱ (የውሳኔአቸው ፍሬ) ክፉም ይኹን ደግ በጋራ ኃላፊነት ይወስዳሉ፡፡ አንድ ሐሳብ ለውይይት ሲቀርብ ሐሳቡን የሚደግፉም፣ የሚነቅፉም ይኖራሉ፤ ለ‘ilaa fi ilaamee’ መድረክ ቀርቦ፣ ሐሳብ በሐሳብ ተሞግቶ፣ በውጤታማ ክርክር (Constructive Dialogue) የጋራ መግባባት ላይ ከተደረሰ በኋላ ግን ኹሉም ለውሳኔው መገዛት፣ የሚመጣውንም ኹሉ በጸጋ መቀበል የግድ ይለዋል!
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
#አንብቡ! #ገንቢ_አስተያየቶችንም_ከበሳል_ትችቶች_ጋር_ስጡ! #ስድብ_በባህል_ነውር_በሃይማኖት_ደግሞ_ኃጢአት_ነውና_እንተወዉ! #እውነት https://www.facebook.com/ewnetmediapage የሚለውን ገጻችንን #Like በማድረግ ቤተሰቦቻችን ሁኑ! ለሌሎችም #Share በማድረግ ጽሑፎችን እንዲያነቡ፣ እንዲቀላቀሉንም ጋብዙ!
#በቴሌግራም ቻናላችንም ይከታተሉን https://t.me/ewnetmedia
#አውነትን_በመግለጥና_ሐሰትን_በማጋለጥ_የሀገርን_ሰላምና_የሕዝብን_አንድነት_ለመጠበቅ_እንትጋ!
