EwnetMedia 2022
EwnetMedia
ከክርስትና አስተምህሮ ጋር የሚጣጣሙ የኦሮሞ ማኅበረሰብ የእርቅ ሥርዓቶች
==================================
ከኦሮሞ ማኅበረሰብ ውብ ባህላዊ እሴቶች መካከል የእርቅ ሥርዓት ዋነኛው ነው፡- ፍጡር ከፈጣሪው፣ ሰዎች ከሰዎች ጋር የሚታረቁበት፡፡ በየትኛውም ጊዜና ኹኔታ ውስጥ መጋጨት ያለ ነው፤ እንደ ተአምርም የሚታይ አይደለም፤ እንኳንስ ሰውና ሰው ቀርቶ አንዱ ሰው ከራሱ ጋር የሚጋጭባቸው ክስተቶች አሉና፡፡ ዋናው ቁምነገር ግን፥ ግጭቱ በአስተማማኝነት የሚፈታበትና ሰላም በቀጣይነት የሚረጋገጥበት አግባብ ነው፡፡ ከክርስትናው እሴቶች ጋር የሚዛመዱ መሰል የሕዝብ እርቅ ሥርዓቶችን መገንዘብና መጠቀም የሚያሻው ለዚኽ ነው፡፡

የኦሮሞ እርቅ ሥርዓቶች ሦስት አካላትን በማስማማት ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡- ሰውና ሰው፣ ሰውና ሌሎች ፍጥረታት፣ እንዲሁም ሰውና ፈጣሪ (ዋቃ)፡፡ ለእያንዳንዱ ምድብ የሚፈጸም የእርቅ ሥርዓትም የተለያየ ነው፡፡ ከእነዚኽም መካከል፡- ሽምግልና (jaarsummaa)፣ በተለይ በአርሲ ኦሮሞ ዘንድ የተለመደውን koottu-dhufee’፣ የቦረና/ጉጂ ኦሮሞ ‘Mataa Buufachuu’፣ የተገዳይ ካሳ ሥርዓት (Sirna Gumaa)፣ ወዘተ. ይጠቀሳሉ፡፡
(1) ሽምግልና (Jaarsummaa)
ይኽ በተለይ በመጫና ቱለማ ኦሮሞ ጎሣዎች ዘንድ የሚዘወተር ሲኾን በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነትና ከበሬታ ባላቸው አዛውንት የሚመራ፣ በሕዝቡ ዝቅተኛው አደረጃጀት ዘንድ የሚፈጸም የአለመግባባት መፍቻ መንገድ ነው፡፡ ምንም እንኳ በሒደቱ ውስጥ ያልተግባቡት ኹለቱ አካላት የየራሳቸውን ተወካይ የሚመርጡ ቢኾንም፥ ተመራጮቹ ግን ለመረጣቸው አካል ሳይኾን ‹‹ለእውነት›› እንዲወግኑ ባህሉ (ማኅበራዊ ስምምነቱ) ያስገድዳል፡፡ ‹‹ሽምግልና›› ሲባል ራሱ ከዕድሜ ይልቅ የአስተሳሰብ ብስለትን፣ ለእውነት መወገንን፣ ለእግዚአብሔር መቅረብን የሚያመላክት ጭብጥ ነው፡፡ የተፈጠሩ ልዩነቶች ተባብሰውና ሰፍተው ወደ እርስበርስ መጠፋፋት እንዳያደርሱ የሽምግልና ሚና እጅግ ወሳኝ ነው፡፡
የሽምግልናው ሒደት ከመጀመሩ በፊት ዳኚዎቹ እግዚአብሔርን ይማጸናሉ፡- ‹‹እውነትን ግለጽልን፤ እውነትም አናግረን!›› ብለው፡፡ ከሳሽና ተከሳሽም እውነትን ብቻ እንዲናገሩ ምለው ይዘጋጃሉ፤ ለጊዜያዊ አሸናፊነት ሳይኾን ለዘላቂው የነፍሳቸው ድኅነት እየተጠነቀቁ ሐሳባቸውን ይሰነዝራሉ፡፡ ሽማግሌዎቹም መረጃዎቹን በከፍተኛ ጥንቃቄ መርምረውና እውነታውን አጥርተው፡- ‹‹ከእናንተ ካገኘነው መረጃና እግዚአብሔር ካመላከተን በመነሳት ይኽንን ወስነናል›› ብለው ያሳውቃሉ፡፡
የሽምግልና ውሳኔዎች በተቻለ መጠን ኹሉንም ወገን ‹‹አሸናፊ›› የሚያደርጉ መፍትሔዎች (win-win situation) እንዲኾኑ ከፍተኛ ጥረት ይደረጋል፤ አንዱ ብቻ ደስተኛ፣ ሌላኛው አኩራፊ ከተደረገ ቀጣይነት ያለው ሰላም አይሰፍንምና፡፡ ይኽ ማለት ግን፥ ‹‹ኹላችሁም ጥፋት የለባችሁም›› በሚል መሸፋፈንና ፍትሕን ማጓደል አይደለም፤ እያንዳንዱ እንደየጥፋቱ መጠን መመከሩ፣ ይቅርታ እንዲጠይቅ መደረጉና የቅጣት ካሳ መክፈሉ አይቀሬ ነው፡፡ የቱንም ያኽል ከባድ ጥፋት ያለበት ቢኖር እንኳ፥ ‹‹የማርያም መንገድ›› ሰጥቶ ነገር ማብረድ ለማለት ያኽል ነው፡፡
የሽማግሌዎች ውሳኔ [የሚጎረብጥ ነገር ያለው ቢመስል እንኳ] አንዴ ከተላለፈ በኋላ፥ ‹‹እግዚአብሔር የተናገረው›› ያኽል ይከበራል እንጂ አይቀለበስም፡፡ ይኽንን ውሳኔ መቃወምም ኾነ ለመቀልበስ መሞከር ሰፉን አለማክበር ነው፤ እነርሱን የመራና ያናገረውን እግዚአብሔርንም መናቅ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ አንዳንዴ ያልተጠበቀ ከባድ ውሳኔም ሊተላለፍ ይችላልና ያለው ብቸኛ አማራች በጸጋ መቀበል ነው፡- ማኅበረሰቡ ‹‹ሽማግሌ አር ያበላል›› የሚለውም ለዚሁ ነው፤ የቱንም ያኽል ቢዘገንን መዋጥ ግድ ነው ሲል፡፡
(2) ‹‹ና-መጣሁ›› (Koottu Dhufee)
ይኽ በተለይ በአርሲ ኦሮሞ ጎሣ ዘንድ የሚዘወተር የእርቅ ሥርዓት ሲኾን[1]፥ እንደ ሽምግልናው ሒደት ኹሉ ሁለቱ አካላት እንዲቀርቡ ይደረግና፡- ‹‹ነገራችሁን ወዲኽ በሉ፤ እንይላችሁ›› ይባላሉ፡፡ በዚሁ መሠረት፥ ሁለቱም የየራሳቸውን ሐሳብ ካቀረቡ በኋላ፥ ሽማግሌዎቹ የእጅ መዳፋቸውን ወደ ሰማይ ከፍ አድርገው የዳኝነት ሥልጣኑን ለፈጣሪ አሳልፈው ይሰጣሉ፡- ‹‹እግዚአብሔር ሆይ፥ ይኽንን ነገር አንተ ፍታልን! ሐሰትን አርቅልን፤ እውነትንም ብቻ አናግረን! አለመግባባትን አጥፍተህ ሰላምህን አውርድልን!›› ሲሉም ይማጸናሉ፡፡ በዚኽም፥ ለማንም እንደማይወግኑ፣ እግዚአብሔር የሚወደውን እውነት ብቻ እንደሚናገሩ በፈጣሪ ፊት ቃል ይገባሉ፡፡ ከዚያች ቅጽበት ጀምሮ ተናጋሪዎችም፣ ሰሚዎችም፣ ፈራጆችም ‹‹ለእግዚአብሔር ተላልፈው ተሰጥተዋልና››፥ እያንዳንዱ ለንግግሩም ኾነ ለድርጊቱ ኃላፊነት ይወስዳል፡፡
ከሳሽ (“Qora Mataa”) ተከሳሽን (“Qora Miillaa”) ና! (“koottu”) ይላል፤ ተከሳሽም መጣሁ! (“dhufe”) ይላልና ሒደቱ ‹‹ና-መጣሁ›› (“koottu-dhufe”) ተብሎ ይጠራል፡፡ ሁለቱ አካላት በተቃራኒ አቅጣጫ፣ ፊት ለፊት እንዲቀመጡ ይደረጋል፤ ዓይን ለዓይን እየተያዩ፣ አንዱ የሌላውን እንቅስቃሴ እየታዘበ፣ እውነትን ሳይቀለብሱ ይናገሩ ዘንድ፡፡ ደግሞም፥‹‹ነገር በዓይን ይገባል›› ዓይነት መኾኑ ነው፡፡ ሽማግሌዎቹም የረቀቀውን አጉልተው፣ የራቀውን አቅርበውና የተሰወረውን ገልጠው ለትክክለኛ ውሳኔ ይዘጋጁ ዘንድ ታሪኮችን፣ ተረታ-ተረቶችን፣ ምሳሌያዊ ንግግሮችንና መሰል ጥበቦችን ይጠቀማሉ፡፡ ኹሉም ነገር ተጣርቶና ወደ የጋራ መግባባት ሲደረስ የሽማግሌዎቹ መሪ ‹‹muramte›› (ተወሰነ) ይላል፡፡ ከዚያች ቅጽበት ጀምሮ የተፈረደበትም፣ የተፈረደለትም ለውሳኔው ተገዢ ይኾናሉ፤ ለኦሮሞ ማኅበረሰብ የሽማግሌ ቃል እንደ ቃለ እግዚአብሔር ነውና!
(3) የካሳ ሥርዓት (Gumaa Baasuu)
የሁለት አካላት አለመስማማት ወደ ግጭት አምርቶ የአካል መጉደልና ነፍስ መጥፋት ደረጃ ከደረሰ፥ በዚኽናው ሥርዓት መሠረት አስፈላጊው ካሳ (Gumaa) ለተበዳይ ይከፈላል፤ እርቅም ይፈጸማል፡፡ ምንም እንኳ መሰል ጉዳት ማድረስ በራሱ በማኅበረሰቡ ዘንድ ‹‹ሰፉን አለማክበር›› ቢኾንም፥ በስህተትም፣ በድፍረትም የሚከሰትባቸው አጋጣሚዎች አይጠፉም፡፡ የሚከፈለው ካሳ የጠፋውን አካልና ነፍስ ይተካል ተብሎ ባይታመንም፥ ካሳውን መፈጸም ግን እርቅ ያመጣል፤ ሊመጣ ካለውም የነፍስ ተጠያቂነት ይታደጋል ተብሎ ይታመናል፡፡
በዚኽ አግባብ የእርቅ ሥርዓት እስኪፈጸም ድረስ፥ ጥቃት አድራሹ አከል (ከቤተሰቡና ዘመዶቹ ጭምር) ከመኖርያ አካባቢው ሸሽቶ መሸሸግ አለበት፡፡ ተጠቂው በስሜት ውስጥ ባለበት ቅጽበት ራቅ ብሎ ሳይሸሸግ የቀረ እንደኾነ ግን በዚያ ምክንያት ለሚፈጠረው ነገርም ተጠያቂ ይኾናል፡፡
የካሳውን ሥርዓት የሚፈጽሙት ሽማግሌዎች ጥቃቱ የተፈጸመው ኾን ተብሎ አልያም በድንገት መኾኑን በጥንቃቄ ካጣሩ በኋላ፥ የካሳውን ደረጃ (የክፍያውን መጠን) ይወስናሉ፡- ከፍተኛ፣ መካከለኛና ዝቅተኛ ብለው፡፡ በዚሁ አግባብ የተወሰነው ካሳም ለተጎጂው አካል እንዲከፈል ይደረጋል፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች፥ ነፍስ ያጠፋው አካል ከዘጠኝ ቀናት በኋላ ዘመዶቹንና ሽማግሌዎችን ሰብስቦ ወደ ተጎጂው ሰፈር በመሔድ፥ ለዘጠኝ ቀናት ይሰግዱላቸዋል (ይማጸኑአቸዋል)፡፡[2] የተማጽኖ ቀናቱ ሲጠናቀቁ የእርቅ መፈጸሚያ ንዋያት (ከለቻ፣ ቦኩ፣ ጫጩና ሲንቄ የመሳሰሉትን) ከተሸለመ ፈረስ ጋር ይዘው በተጎጂዎቹ ቤት ፊት ለፊት ይቆማሉ፤ ለካሳ ሥርዓት (እርቅ) የተቀባይነት ምልክት እስኪያገኙ ድረስ፡፡ በኦሮሞ ገዳ ሥርዓትና እሴት መሠረት በዚኽ መልኩ የቀረበውን ተማጽኖ መግፋት (አልቀበልም ብሎ መመለስ) ፈጽሞ የማይታሰብ ነው፤ ይኽ በራሱ ደግሞ ሰፉን መተላለፍ ነው፤ ለከፍተኛ ርግማን ይዳርጋል፡- ‹‹ሰውም፣ ከብቱም ሰላም አያገኝም፤ ያረሰው አይበቅልለትም፤ ከበቀለም ፍሬ አያፈራለትም›› ተብሎ ይታመናል፡፡
በመጨረሻው የእርቅ ቀን (“Hanxaxii Cabsaa”) ሁለቱም አካላት 16 ዓይነት የዕጽዋት ዓይነቶችን በመያዝና በ44ቱ ኃይላት መናፍስት (abarreen 44)[3] ስም ቃል ኪዳን ይገባባሉ (ይማማላሉ)፡- ጎጂው የተፈረደበትን ካሳ ሊከፍልና ‹‹አትድረስ›› በተባለ ቦታ ላይደርስ፤ ተጎጂውም ይኽንን የካሳ ሥርዓት ችላ ብሎ ለበቀል ጥፋት ላይነሣሣ፡፡ እዚኽ ላይ እጅግ የሚደንቀው ነገር፥ ነፍስ ያጠፋው አካል የቱንም ያኽል የናጠጠ ሀብታም ቢኾን ካሳውን የሚከፍለው ግን ለምኖ መኾኑ ነው፡- በኀፍረት በሕዝብ መካከል እየተዘዋወረ፣ የሰው ነፍስ ማጥፋቱን እየተናዘዘ እና አንገቱን ደፍቶ ከክብሩ እየተዋረደ ባገኘው ካሳውን ሲከፍል የነፍሲቷ ባለቤት እግዚአብሔርም ጭምር ይቅር ይለዋል ተብሎ ስለሚታመን፡፡ በዚኽ መልኩ ከተሰበሰበው ገንዘብ ኹሉም የተጎጂው ዘመድ አዝማድ (በትንሹም ቢኾን) መውሰድ አለባቸው፤ ‹‹ካሳ አልበላሁምና›› በሚል ለበቀል እንዳይነሣሡ፡፡
በመጨረሻም፥ በኦሮሞ ማኅበረሰብ ባህላዊ እምነትና ሥርዓት መሠረት፡- ‹‹የፈሰሰ ደም ሊታጠብ [ይቅርታ ሊያገኝ የሚችለው] ደም ሲፈስ ብቻ ነው›› ተብሎ ስለሚታመን፥ የካሳ (እርቅ) ሥርዓቱ ደም በማፍሰስ (በእርድ) ፍጻሜውን ያገኛል፡፡ ይኽም፥ “sirna harka dhiqaa” (‹‹እጅን የመታጠብ ሥርዓት››) ይባላል፡፡ ከታረደው ከብት ሥጋ በየጥቂቱ ተቆራርጦ ለሁለቱም አካላት (ጎጂና ተጎጂ) ይሰጣል፤ እነርሱም ከቀመሱ በኋላ፡- “gumaa nyaanne” (‹‹እነሆ ካሳ በላን!››) ይላሉ፡፡ ከዚያች ቅጽበት ጀምሮ እርቅ ወርዷል፤ ዝምድናም ተመልሷል፤ “waliin nyaatanii wal-hin nyaatani!”(‹‹አብሮ በልቶ፣ መልሶ መባላት አይታሰብምና!))
(4) ‹‹ራስን ዝቅ ማድረግ›› (Mata Buusii)
አስቀድመው የተጠቆሙት የእርቅ ሥርዓቶች (ሽምግልና፣ ና-መጣሁ እና የካሳ ሥርዓት) በሰዎችና ሰዎች መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶችን የሚዳኙ ናቸው፡፡ ይኽኛው የእርቅ ሥርዓት ግን ሰዎች ከፈጣሪአቸው ጋር የሚታረቁበት ነው፡፡ በዋናነትም በገዳ ሥርዓት (በተለይም በጉጂና ቦረና ጎሣዎች) ውስጥ የሚዘወተር ኾኖ፥ እግዚአብሔርን ከሚያሳዝኑ ተግባራት ኹሉ ለመራቅ፣ ወደፊትም ‹‹ንጹህ የእግዚአብሔር ሰው›› ለመኾን ራሳቸውን ለሚዘጋጁ ሰዎች የሚፈጸም ነው፡፡ እናም፥ ይኽ ሥርዓት የሚፈጸምላቸው ዕድሜአቸው ከ80 በላይ ለኾኑ፣ 40 ዓመት የሞላው ልጃቸውን ለገዳ ያበቁ [ራሳቸው ደግሞ ‹‹ገደሞጂ›› ወደሚባለው እርከን የተሸጋገሩ]፣ በቀሪው ዘመናቸው እግዚአብሔርን ለማስደሰት የወሰኑ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ ‹‹ገደሞጂ›› ደረጃ ላይ የደረሱ (‹‹መታ ቡሲ›› ሥርዓት የተፈጸመላቸው) አዛውንት በሰውም፣ በእግዚአብሔርም ዘንድ ተቀባይነት እንዳላቸው ስለሚታመን ኹለቱን አካላት (ፍጡርንና ፈጣሪን) ለማስታረቅ የተገቡ (ሥልጣን ያላቸው) ናቸው፡፡
‹‹መታ ቡሲ›› (ራስን ዝቅ ማድረግ) በሰው ዘንድ ከበሬታን የሚያስገኝበት፣ በእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታዎች መሞላትን የሚገልጽበት ትልቁ ምስጢር ከተፈጥሮም ጋር አገናኝተን የምንማረው ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ዕጽዋት በርካታ ፍሬ ሲያፈሩ እንደቀድሞ አቋማቸው ቀጥ አይሉም፤ ፍሬው ስለሚከብዳቸው ያጎነብሳሉ እንጂ፡፡ ገደሞጂም ራሱን ዝቅ የሚያደርገው በታላቁ እግዚአብሔር ክብር ሥር ነው፤ ለእግዚአብሔር ያጎነበሰ ደግሞ በሰዎች መካከል በታላቅ ክብር ከፍ ብሎ እንደሚኖር የታወቀ ነው፡፡[4] እርሱ ራሱ የፈጣሪን ሕግጋት መጠበቅ (ከኃጢአት መራቅ) ብቻ ሳይኾን የማስጠበቅም ኃላፊነት ይወስዳል፤ ለሌሎች የሚያስተምረውን በተግባር ይኖረዋል (በሕዝቡ መካከል በአርአያነት ይመላለሳል)፡፡ በዚኽ ልክ የሚኖር አረጋዊ ደግሞ፥ በሰው ዘንድ ተናግሮ የሚደመጥ፣ ጸሎቱም ቅድመ እግዚአብሔር እንደሚደርስ እሙን ነው፡፡ እናም፥ በሁለቱም መካከል የሚፈጠረውን አለመግባባት ይዳኝ ዘንድ በሰዎች ዘንድ ሞራላዊ ብቃት፣ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ያለው ነው፡፡
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
#አንብቡ! #ገንቢ_አስተያየቶችንም_ከበሳል_ትችቶች_ጋር_ስጡ! #ስድብ_በባህል_ነውር_በሃይማኖት_ደግሞ_ኃጢአት_ነውና_እንተወዉ! #እውነት https://www.facebook.com/ewnetmediapage የሚለውን ገጻችንን #Like በማድረግ ቤተሰቦቻችን ሁኑ! ለሌሎችም #Share በማድረግ ጽሑፎችን እንዲያነቡ፣ እንዲቀላቀሉንም ጋብዙ!
#በቴሌግራም ቻናላችንም ይከታተሉን https://t.me/ewnetmedia
#አውነትን_በመግለጥና_ሐሰትን_በማጋለጥ_የሀገርን_ሰላምና_የሕዝብን_አንድነት_ለመጠበቅ_እንትጋ!
[1] የዚህ ጽሑፍ አብዛኞቹ ጭብጦች የተገኙት ከአዳባ ወረዳ ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት (“Waajjira Koominikeeshinii Aanaa Adaabbaa”) ስለኾነ ስለመረጃው ወረዳውን እናመሰግናለን፡፡
[2] Waajjira Koomunikeeshinii aanaa Ilfataa.
[3] ይህ በተለምዶ፥ ‹‹44ቱ ታቦታት›› ከሚባለው ጋር ይገናኝ፣ አይገናኝ ለማወቅ አልተቻለም፤ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላትም እንዲህ ተብሎ መገለጹን እንጂ መነሻውንና ምንነቱን ለማብራራት ተቸግረዋል፡፡
[4] በመጽሐፍም፡- ‹‹እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ›› (1ጴጥ.5፥6)፤ ‹‹በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ ከፍ ከፍም ያደርጋችኋል›› (ያዕ.4፥10) የሚሉ ተመሳሳይ መልእክቶች እንዳሉ ልብ ይሏል፡፡
