EwnetMedia 2022
EwnetMedia
ምርቃት (Eebba)፡- የኦሮሞ ተግባራት ኹሉ መጀመሪያ!
==================================
የኦሮሞ የትኛውንም ኅብረታዊ ድርጊቱን የሚጀምረው በአዛውንት ምርቃት (''eebba'') ነውና ምርቃት በማኅበረሰቡ ባህል ውስጥ ትልቅ ሥፍራ ያለው፣ ‹‹የኹሉም ነገር መቅድም›› ሊባል የሚችል ነው፡፡ በምርቃት የተጀመረው ክንውን ሲፈጸምም የማጠቃለያ ምርቃት ማድረግ የተለመደ ነው፤ ከጅምሩ ‹‹አንተ ምራን›› ተብሎ እንደተለመነ ኹሉ ‹‹ስለመራኸን እናመሰግንሃለን›› የሚል ምስጋና መኾኑ ነው፡፡ በምርቃቱ ውስጥም በዋናነት ዋቃ [እግዚአብሔር] ስሙ እየተጠራ ይለመናልና በምርቃት የተጀመረ ተግባር የተሳካ እንደሚኾን በሙሉ ልብ ይታመናል፡፡

ምርቃቱን የሚያከናዉኑት ‹‹አዛውንት ናቸው›› ስንል የዕድሜ ጉዳይ እንዳለ ኾኖ በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ ግን አንድ የተለየ ሥርዓትም አለ፡፡ ይኸውም፡- ቅድምና የሚሰጣቸው ጎሣዎች አሉ፤ ኹሉም በየራሳቸው ተዋረድ ብቻ ይመርቃሉ፡፡ ለምሳሌ፡- በኦሮሞ የትውልድ ሐረግ ቅደም ተከተል መሠረት፥ ቦረና የኦሮሞ ጎሣዎች ኹሉ ታላቅ ነው ተብሎ ስለሚታመን ከዚያ ጎሣ የኾነው (በዕድሜ ታናሽ ቢኾን እንኳ) ቀድሞ እንዲመርቅ (ጉባኤውን እንዲያስጀምር) ይደረጋል፡፡ በአንዱ ጎሣ ውስጥም ደግሞ፥ በተመሳሳይ መልኩ የታላቅና ታናሽ ቅደም ተከተሎች አሉ፤ ንዑሳን ጎሣዎቹ በየትውልድ ተዋረዳቸው መሠረት ይመርቃሉ፡፡
እነዚኽ የተለያዩ የኦሮሞ ጎሣዎች የየራሳቸው የምርቃት ዓይነቶች (ይዘቶች) አሏቸው፡- የቦረና፣ የመጫ፣ የቱለማ፣ የጉጂ፣ የከረዩ፣ የአርሲ፣ ወዘተ. ምርቃት የሚባሉ አመዳደቦች አሉ፡፡ የየምርቃቶቹን ተናጠላዊ ትኩረት ስንመለከት፡- በአብዛኛው የቦረናው ለሰላም ልዩ ቦታ ይሰጣል፤ የመጫው ሊመጣ ከሚችለው መዓት እግዚአብሔር እንዲያርቅ ይለምናል፤ በቱለማው ውስጥ የእግዚአብሔር ስም ተደጋግሞ ይነሣል፤ የጉጂው ደግሞ የቱለማንና መጫን ባማከለ መልኩ የእግዚአብሔርን ስም ከሰላም ጋር አያይዞ ያቀርባል፡፡
በሌላ መልኩ፥ ምርቃቶቹ ከሚቀርቡባቸው ጉዳዮች አኳያም ከፋፍሎ ማየት ይቻላል፡- ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መሥዋዕት ላይ የሚመረቅ፤ አዲስ ዓመትን በማስመልከት የሚደረግ፤ የጋብቻ ምርቃት፤ ከእርቅና ፍርድ በፊት የሚካሔድ፤ ለሕጻናትና አዳጊዎች የሚደረግ፤ ከእግዚአብሔር ዝናመ ምሕረት፣ እክለ በረከት የሚለመንበት፤ መንገደኞች በሰላም ወደቤታቸው እንዲመለሱ የሚጸለይበት፤ በውጊያ ላይ ላሉትም ፈረሳቸው እንዳይደክም፣ ጦራቸው ዒላማውን እንዳይስት፣ ክንዳቸው እንዳይዝል፣ ድል እንዲያደርጉ የሚመኙበት፤ የተሰማሩ እንስሳት እንኳ በሰላም ውለው ወደ በረታቸው እንዲመለሱ የሚለመንበት ምርቃት፣ ወዘተ. ኹሉ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይኽም በጥቅሉ ሲታይ፥ ከኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ‹‹በእንተ ቅድሳት›› ጸሎት ጋር በእጅጉ ተመሳሳይ ኾኖ እናገኘዋለን፡- በዚኽም ስለ ሰላም፣ ስለ ሃይማኖት፣ ስለ አንድነት፣ ስለ ትዕግሥት፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች፣ ረዳት ስለሌላቸው ግፉአን፣ ስለ ደናግል፣ ስለ መሃይምናንና ንዑሰ ክርስቲያን፣ ስለ ኢትዮጵያ፣ ስለ መኳንንትና ሥልጣን ስላላቸው፣ ስለ ዓለም ኹሉ፣ በባህርና በደረቅ ስለሚሔዱት ሰዎች፣ ስለ ተራቡና ስለ ተጠሙ ሰዎች፣ ስለ አዘኑና ስለ ተከዙ ሰዎች፣ ስለ ታሠሩ ሰዎች፣ ስለ ተማረኩ ሰዎች፣ ስለ ተሰደዱ ሰዎች፣ ስለ ታመሙትና ስለ ድውያን፣ ስለ ሞቱ ሰዎች፣ ስለ በደሉ ወገኖቻችን፣ ስለ ዝናብ፣ ስለ ወንዝ ውኃ፣ ስለ ምድር ፍሬ ‹‹እንማልዳለን›› እየተባለ፣ ስማቸው አንድ በአንድ እየተጠራ ይጸለያልና!
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
#አንብቡ! #ገንቢ_አስተያየቶችንም_ከበሳል_ትችቶች_ጋር_ስጡ! #ስድብ_በባህል_ነውር_በሃይማኖት_ደግሞ_ኃጢአት_ነውና_እንተወዉ! #እውነት https://www.facebook.com/ewnetmediapage የሚለውን ገጻችንን #Like በማድረግ ቤተሰቦቻችን ሁኑ! ለሌሎችም #Share በማድረግ ጽሑፎችን እንዲያነቡ፣ እንዲቀላቀሉንም ጋብዙ!
#በቴሌግራም ቻናላችንም ይከታተሉን https://t.me/ewnetmedia
#አውነትን_በመግለጥና_ሐሰትን_በማጋለጥ_የሀገርን_ሰላምና_የሕዝብን_አንድነት_ለመጠበቅ_እንትጋ!
