EwnetMedia 2022

EwnetMedia 2022

EwnetMedia

‹‹ጊንጊልቻ፥ የቋንቋ ህፀፄን የሞላች፣ ምኞቴን ያሳካችና የሐሰተኛ ትርክቶች ማንጠርጠሪያ ናት!››

====================(በአማን ነጸረ)

በቅጡ አፀፋ አልተሰጠባቸውም ብዬ ከምነጫነጭባቸው አርእስት አንዱ ሃይማኖታዊ የመደብ ጀርባቸው ኢ-ኦርቶዶክሳዊ የሆነ ትውልደ ኦሮሞ ምሁራን በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ለመምታት በማለም በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያደርጉት ዘመቻ ነበረ፡፡ በ2008 ዓ.ም. በጉዳዩ የነበረኝን ቅሬታ ሰፋ አድርጌ በፌስቡክ ገለጥኩ፡፡ ፌስቡክ ምክንያቱን ሳይነግረኝ ልጥፌን ሁለት ጊዜ አነሣብኝ (ውስጥ አዋቂዎች የኮፒ ራይት ጥበቃ ያለውን ጽሑፍ በፒ.ዲ.ኤፍ በማያያዜ መሆኑን ኋላ ነግረውኛል)፡፡ ደግነቱ ሌሎች ጓደኞቼና ዌብሳይቶች ተቀባብለው አስቀሩልኝ፡፡ ኋላ የተደራረበ ቅሬታዬን ወደ መጽሐፍ ለማሳደግ ስንደፋደፍ የቋንቋ ጉዳይ ንባብና መረዳቴን ከምሉዕነት እንደሚገታብኝ ገባኝ፡፡ ጥቂት ንጭንጭና ማለዘቢያ እንዲሆን ትውልደ ኦሮሞ ሊቃውንት በቤ/ክ - በተለይም በጎጃም የቅኔ ጉባኤያት- የነበራቸውን ሱታፌ ነካክቼ ተውኩት፡፡ ፈጣሪያችን ደግ አይደል! ህፀፄን የሚሞላ ምኞቴን የሚያሳካ በሊሃ ብርዕ (የተሳለ ብዕር ያለው) እና በአፋን ኦሮሞ የሚቀኝ የሚራቀቅ ጸሐፊ በጊዜው ጊዜ መጣ፡፡ በእርሱ በኩል በጥናት ስም በአንጻረ ቤተ ክርስቲያን የሚሰነዘረውን መደምደሚያ የቀደመው ክታብ ማንጠርጠሪያ ወንፊት ለቅድመ ኅትመት ንባብ እይታ መጣችልኝ፡፡ ሸጋ ማንጠርጠሪያ ናት−ጊንጊልቻ፡፡ ምን ይንጠረጠራል? ማንጠርጠሪያው የሚያንጠረጥረውን ትንሽ እንጠቁም!

--

በጥቅሉ በጥናት ስም የሚቀርቡት ሥራዎች አንትሮፖሎጂንና ሚቶሎጂን ከታሪክ የማዛነቅ አካሄድ አለባቸው፡፡ የተኖረውን የአብሮነት ኑሮና ለዚህም ዋጋ የከፈሉ ሰዎችን ይዘነጋሉ፡፡ መረጃቸውን ከሚተቹት አካል ይወስዱና ያንን ወደ ግራ በማንበብና በአሉታ በመተንተን (by deconstruction) ለታለመበት ዐላማና ለተመረጠ ተደራሲ የሚቀርብ ታሪክ ይጽፋሉ፡፡ በተለይም በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ፡-

ውጫዊ_እይታ_በጉልህ_ይታያል፡-

በነገረ ቤተ ክርስቲያን ራሳቸውን እንደ ኤክሰፐርት ቆጥረው በJournal of Oromo Studies የሚጽፉት እነ ዶ/ር መሐመድ ሐሰን፣ ዶ/ር መኩሪያ ቡልቻ፣ ዶ/ር ገመቹ መገርሳ፣ ዶ/ር አባስ ሐጂ … በቤተ መስጊድ ወይም በቤተ ሚሲዮን ያደጉ በመሆናቸው እይታቸው ሲበዛ ውጫዊ ነው፡፡ ስለ ቤተ ክርስቲያን ያላቸው እይታ ከቱሪስት የተሻለ ባይሆንም በውጫዊ እይታና ‹‹መርጦ በማንበብ›› በነገረ ቤተ ክርስቲያን ተጠያቂ መሆን ይዳዳቸዋል፡፡ እንደ ቄስ ልጅ ‹‹ሲሶ መሬት›› የሚለውን ተረክ እንደወረደ ውጠው ቤተ ክርስቲያን የሀገሪቱ 33 በመቶ መሬት በእጇ ነበረ ሲሉኝ ሽቅብ ይለኛል−ያልበላሁትን፡፡ በነገራችን ላይ በሕግ ት/ቤት የጁሪስፕሩደንስ ኮርስ ‹‹ውስጣዊ እይታ››ና ‹‹ውጫዊ እይታ›› የምትባለው ነገር ትልቅ ቦታ አላት፡፡ እዚህ አላብራራትም፡፡ በክርስትና ሕይወት ደግሞ ጸሐፊዋ ‹ቤተ ክርስቲያንን ከውጭ ስታያት አትገባህም፤ በውስጡዋም ሰትሆን አትገልጻትም› ትላለች፡፡

#ትውልደ_ኦሮሞ_ኦርቶዶክሳውያን_ሊቃውንት_ይዘነጋሉ፡-

ምድረ ጎጃምን በቅኔያቸው የሸፈኗት እነ የንታ ገብረ ሥላሴ፣ ውዳሴ ማርያምንና አንቀጸ ብርሃንን በ19ኛው ክፍለ ዘመን ወደ አፋን ኦሮሞ እንደ ተረጐሙ የሚነገርላቸው እነ አለቃ ኃይለ ኢየሱስ፣ በአፋን ኦሮሞ ቅኔ የሚቀኙት እነ አለቃ ዘወልዴ፣ የሸዋን ምድር በቅኔያቸው የሸፈኗት እነ የንታ ጥበቡ ገሜ፣ … በዚህች ሀገር ምንም እንዳላደረጉ ይቆጠርና በባርነት ተፈንግለው ወደ አውሮፓ ከሄዱ በኋላ በሚሲዮናውያን አርነት የወጡ ወይም ለፖለቲካ አጀንዳ ግብዓት የሰጡ የ‹‹ሃይማኖት መሪዎች›› የተለየ ትረካ ይቀርብበታል፡፡ ምክንያቱም ሃይማኖታቸው ከጸሐፍቱ ይገጥማል፡፡ ኦሮሞ እንደ ማኅበረሰብእ በዘመነ ጎንደር ከሚሲዮናውያንም ሆነ እርስ በርስ በነበረው ተጋድሎ በሁሉም ወገን እየተሰለፈ የከፈለውን ዋጋ Mordechai Abir የተባለ ጸሐፊ Ethiopia and the Red Sea በሚል መጽሐፉ አስፍሮት ነበረ፡፡ በታሪከ ነገሥቱ በስፋት የሚተረከው የእነ ደጃዝማች ቱሉ፣ የአባ ገዳ ዲላሞ (ዲላሞ አሁን አቸፈር ውስጥ ያለ የቦታ ስም ነው)፣ የኢቱ ተወላጅ የሆኑት የእነ አባ ሥልጣነ ክርስቶስ ሱታፌ፣ የጃዊና የቱለማ ጎሳዎች በዘመነ ጎንደር በተጋጋሉት የነገረ ክርስቶስ ክርክሮች ወቅት የነበራቸው ሱታፌ ለእነ መሐመድ ሐሰን ሩቅ ነው፡፡ በEtymology ተሳስበው ቦታዎችን በመጠቋቆም የጥንተ ርስትና ሙላድ ከማሰስ ባለፈ የሰዎቹን ክርስቲያናዊ ሱታፌና የነበረውን ተዛምዶ አይሹትም፤ ቦታ አይሰጡትም፡፡ በቀ.ኃ.ሥ ዘመን ለሚሲዮናውያን መቆጣጠሪያ በወጣው ሕግ ላይ በሰበብ አስባቡ በየጆርናልና መጽሐፉ የሚሰማው ጩኸት ያስተዛዝባል፡፡ ጸሐፊዎቹን በሚሲዮናዊ የጡት ልጅነት ያስጠረጥራል፡፡

#የኦርቶዶክሳውያን_ታሪክ_በኢ-ኦርቶዶክሳውያን_ሲጻፍ፡-

የሜጫ ቱለማ ማኅበር መሥራቾችን ታሪክ እያነበብኩ ነበረ፡፡ ብዙዎቹ አጥባቂ ኦርቶዶክሳውያን ነበሩ፡፡ ቆይቶ መሪዎቹ ከንጉሡ ተጋጩ፡፡ እንደ መሸፈት አሉ፡፡ በመካከሉ ካህናት (አባ ሀብተ ማርያም ወርቅነህና አቡነ ቴዎፍሎስ) በጉዳዩ ገቡ፡፡ ግዝት ገዝተው አስታረቁ፡፡ ንጉሡ ዕርቁን ሳያከብሩ ቀሩ፡፡ ታሪክ ጸሐፊው ኋላ ታሪኩን ሲጽፍ ‹‹ግዝትና ግዞት›› አለው፡፡ ግዝት ማለቱ የቤ/ክንን ድርሻ በክፋት መወከሉ ነው፡፡ ታራቂዎች ዕርቁን ስላላከበሩ አስታራቂውን መርገም! የኦርቶዶክሳውያን ታሪክ በኢ-ኦርቶዶክሳዊ ሲጻፍ እንዲህ ነው! ዶ/ር ዐቢይ እንደ መጣ ተሞክሮ የከሸፈውን ሸኔን ያካተተ የኦነግ ዕርቅ የዳኘው ኦርቶዶክሳዊ ጳጳስ ቢሆን ይህ ‹‹የግዝትና ግዞት›› ስም ልጠፋ ይቀርለት አይመስለኝም፡፡ ላልመሰረ ተመክሮ ሁሉ ቤተ ክርስቲያንን ማሳቀል አይመስጥም!

#የጭቁን_ግንባር፡-

አንዳንድ ጓደኞቻችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከሌሎች ሃይማኖቶች ጋር መጎረባበጥ ውስጥ ከገባች ወይም በውስጡዋ አፈንጋጭ ኃይል ካቆጠቆጠ ‹‹በጣም ሚዛናዊ፣ ፍትሐዊ፣ ርቱዕ፣ …›› ካልሆንን ብለው ይገለገላሉ፡፡ ውስጧ የጠላቴ ጠላት ቢሆንም ውጭ ውጩን የጭንቁን ግንባር መሳይ ነገር ነች! ለአብነት፡- በአህመዲን ጀበል፣ በታቦር ዋሚና በመሐመድ ሐሰን መጻሕፍት መካከል የምታስደንቅ መናበብ አለች፡፡ በግርግር ‹‹አረባይዜሽን›› በእነ መሐመድ ሐሰን መኖር ከማንነት ተጋፊነት ክስ ነጻ ወጥታ ከእሬቻ መልስ ለምለም ሳር ይዞ፣ በጎፈር ባርኔጣና ለምድ ተሸልሞ፣ በዳንዴ ፈረሱ ወጥቶ በራሱ ቋንቋ በሆታ ታቦት አጅቦ ወደቤቱ የሚመለሰው ኦርቶዶክሳዊ የሸዋ ኦሮሞ ማንነቱን በሐበሾች ሴራ እንዳጣ ይሰበካል፡፡ ግንባር ደጉ! ‹ዮሐንስ› መባል የነፍጠኛ ሃይማኖት መከተል አሰኝቶ በ‹ሌንጮ› ተተክቶ ‹መሐመድና አባስ› ግን ማንነት የሚበይኑባት ግንባር!

‹‹ #የሐበሻ_ሃይማኖት››፡-

በጣም ደካማ አመለካከት ነው! ‹‹ዋቃ ጉራቻን›› ለማስረሳት ሐበሾች የነጭ ሥዕል አመጡብን ይልሀል ዶ/ር ገመቹ መገርሳ፡፡ ኧረ ጌታዬ ስለ ‹አይኮንክላስት› ምናምን ብዙ ተነግሯል…የዓለምን ከ75 በመቶ በላይ ክርስትና በሚሸፍኑት ካቶሊካውያንና ኦርቶዶክሳውያን ዘንድ ሥዕል አለ … ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት አካባቢ ያሉ ሰዎችም ቀላ ያሉ ናቸው … በጅምላ ሐበሻ በሚሉት አካባቢ እንደ አገውና ቅማንት የመሳሰሉ አጥባቂ ተዋሕዶዎችም አሉ …፣ ማለት ያምርሀል፡፡

#ብሔር_ተኮር_ማስተሐቀር_ሰፍኗል_ማሰኘት፡-

ባይነገር ጥሩ ነው! ግን አልሆነም! በመጽሐፍ ቅዱስም ስለ ግብጽ፣ ሰዶም፣ ገሞራ፣ አማሌቅ፣ … አስተሐቃሪ ቃል ይነገራል፡፡ በግእዝ መዛግብት ስለ ጎጃም፣ ጎንደር፣ ወሎ፣ አማሬ/ራ፣ ትግሬ/ራይ፣ አገው፣ … የተጻፉ መጽልም ጽሑፎች አሉ፡፡ ‹‹ጋላ›› የሚለው በእርግጠኝነት ከግእዝ፣ አማርኛና ትግርኛ (አንዳንድ የብሔር ግንባር ለመፍጠር ሲባል የሚክዱ ወዳጆች ቢኖሩኝም በትግርኛም ቃሉ ስለመጠቀሱ በርካታ የትግርኛ ግጥማዊ ማስረጃዎችን ማቅረብ እችላለሁ) በተጨማሪ በአፋርኛ፣ ሶማልኛ፣ ኑዌር፣ በአፋን ኦሮሞ ፉከራዎችም (The Folk Literature of Glalla በተሰኘው መጽሐፍ በጊቤ ሙስሊሞችና በምዕራብ ኦሮምያ የባህላዊ እምነት ተከታዮች መካከል በነበረው ግጭት መካከል የምዕራቦቹ በዚህ ስም ይፎክሩ ነበር፤ ሃንቲንግ ፎርድም የቃሉ ምንጭ ከሰሜን ነው መባሉን አይደግፍም) ጥቅም ላይ ሲውል የነበረና ስያሜው በደባትር ወጣ ለማለት ማስረጃ ያለው አይደለም፡፡ በጠብ ጊዜ ከላይ የተጠቀሱት የየክፍለ ሀገሩ ተወላጆች በጅምላ እየተፈረጁ ባልተገባ ስያሜ እንደሚጠሩት ኦሮምኛ ተናጋሪዎችም በጅምላ ይጠራሉ፡፡ ልዩ ሁኔታ የለውም፡፡ በብዝኃ ብሔረሰብ ሀገር ውስጥ እንዲህ ያለው አነጋገር እንዲኖር ባይመረጥም በታሪክ ሂደት ግን ሊያስወግዱት የሚቻል አልነበረም፡፡ ታላላቅ ወንድሞቻችን ድርጊቱ አንድን ወገን ብቻ ዒላማ በማድረግ − ትናንትን በዛሬ ሚዛን የኋሊት እየመዘኑ- እንደ ተጻፈ አስመስለው ይተርኩታል፡፡ ይህ ዓይነቱ ታሪክን መሞረድ በታሪክ ምሁራኑ ቋንቋ ‘Anachronism’ ይባላል አሉ፡፡ ይኸንን ሁሉ ታንጠረጥራለች - ጊንጊልቻ!

--

ከሁሉም ከሁም ስማችንን − የደባትርን ስም- ያጠፋሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ መካሰሴ አይቀርም፡፡ የእነ ‹‹መጥምቅ›› ግርማና የእነ ኢዩ ጩፋ የ‹‹ድግምት›› ክስ አንሶን ስማቸውን ጠርቼ የማልዘልቃቸው በርካታ የብሔረሰብ ጸሐፍት ስቅ እስኪለን ይጠሩናል፡፡ የሚገርመው ከሚተቹት ደብተራ የተሻለ ሚዛናዊ ሆነው አለመገኘታቸውና እነርሱም በፊናቸው ሕሊናቸውንና ምሑራዊ ቁመናቸውን (intellectual integrity) በስመ ብሔር ጆሮውን ብለው የሸጡት መሆናቸው፡፡ ድብትርናን ለማስተሐቀር መጋጋጣቸው አይቆጭም፡፡ የሚቆጨው በስመ ደባትር ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ለማጽለም መሞከራቸው፡፡ በእርግጥ ይኸም ይንጠረጠራል - በጊንጊልቻ!

--

መልካም ንባብ!

https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=2923604984555389&id=100007177473347  

~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~

#አንብቡ! #ገንቢ_አስተያየቶችንም_ከበሳል_ትችቶች_ጋር_ስጡ! #ስድብ_በባህል_ነውር_በሃይማኖት_ደግሞ_ኃጢአት_ነውና_እንተወዉ! #እውነት https://www.facebook.com/ewnetmediapage የሚለውን ገጻችንን #Like በማድረግ ቤተሰቦቻችን ሁኑ!  ለሌሎችም #Share በማድረግ ጽሑፎችን እንዲያነቡ፣ እንዲቀላቀሉንም ጋብዙ!

#በቴሌግራም ቻናላችንም ይከታተሉን https://t.me/ewnetmedia

#አውነትን_በመግለጥና_ሐሰትን_በማጋለጥ_የሀገርን_ሰላምና_የሕዝብን_አንድነት_ለመጠበቅ_እንትጋ!


Report Page