EwnetMedia 2022
EwnetMedia
ከክርስትና አስተምህሮና ሥነ-ምግባር ጋር የሚደጋገፉ የኦሮሞ ባህል እሴቶች- ‹‹ሰፉ›› እንደ ማሳያ!
==================================
በአሁኑ ጊዜ የተለየ መልክ ይዘው የሚገኙ አንዳንድ የማኅበረሰቡ ድርጊቶች በጭፍኑ በባዕድ አምልኮነታቸው ተፈርጀው እንጂ እንደ ክርስትና ትምህርት መነሻ እሴትነታቸው ታይተው የሚያውቁ አይመስልም፡፡ አንዳንድ የኦሮሞ ጎሠኛ ፖለቲከኞች እና አጽራረ ቤተ ክርስቲያን እንደሚያራግቡት ያይደለ፤ አብዛኞቹ የኦሮሞ ባህላዊ ድርጊቶች እና እሴቶች ከኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን እምነት (አስተምህሮ)፣ ሥርዓተ አምልኮና ትውፊት ጋር ጥብቅ ቁርኝት (ተዛምዶ) እንዳላቸው በበርካታ መመዘኛ ነጥቦች ተገምግመዋል፤ ሊታረቁም እንደሚችሉ በጥናት ተረጋግጧል፡፡[1] በዚኽ ጽሑፍ ውስጥ፥ ለማሳያ ያህል አንዱን ብቻ (ሰፉ/Safuu) እንደሚከተለው ለማቅረብ ተሞክሯል፡፡

የመጫን ኦሮሞ አጠቃላይ አኗኗርና እምነት በማጥናት የሚታወቁት ጀርመናዊ ምሁር (ላምበርት) እንደሚገልጹት፥ ሰፉ ኹሉን አቀፍ ጽንሰ ሐሳብ ኾኖ ማንኛውም የዚኽ ዓለም እንቅስቃሴ የየራሱ ቦታ እንዳለው የሚያምን፣ በምድርና በሰማይ ያሉት ፍጥረታት በሙሉ በየራሳቸው ክበብ ጸንተው መኖርና በተመደበላቸው ሥርዓት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው የሚደነግግ፣ ለሰው ልጆችም የክፉና ደግ መለያ መሠረት (basis of moral value) ነው፡፡[2] በዚኽ ጸሓፊ አገላለጽ፡- ሰፉ ሰዎች የሚደነግጉት ሕግ ሳይኾን እግዚአብሔር በተፈጥሮ በሰዎች ልቡና የሚያኖረው የሥነ-ምግባር ሕግ (divinely inspired moral conduct) ነው፡፡ ዶ/ር ገመቹ መገርሳም፡- ‹‹በማኅበረሰባዊ አካላት (ምድራውያን) እና ሰማያዊ ኃይላት መካከል የሚኖር ሥነ-ምግባራዊ ትስስር›› ሲሉ ገልጸውታል፡፡[3]
በአንድ በኩል፥ ኹሉንም አዎንታዊ ማኅበራዊ ሕጎችን ያጠቃልላል፡- ታናናሾች ታላላቆቻቸውን እንዲያከብሩ፣ ልጆች ለወላጆቻቸው እንዲታዘዙ፣ ወላጆችም ትውልዱን ሊቀርጹበት ስለሚገባ አካሔድ፣ የሰው ልጅ ያለውን ልዕልና፣ ወዘተ. ኹሉ የሚያካትት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፥ እውነትን መናገርና ለእውነት ብቻ መኖርን የሚያስገድድ ነው፡፡ ተፈጥሮም የራሷን ሥርዓትና ሒደት እንድታከብር የሚያስብ ነው፡- መዓልቱ ለሰው ልጆች፣ ሌሊቱ ለአራዊት የተፈቀደ በመኾኑ ኹሉም በዚኽ ሥርዓት መሠረት መንቀሳቀስ አለበት፡፡ አራዊት፣ አፍላጋት፣ አድባራትና ዕጽዋት ኹሉ የሚገባቸው ክብር አላቸውና እንደፈለጉ ወግቶ መግደል፣ አፍስሶ ማደፍረስ፣ አፍርሶ መደልደል እና ቆርጦ ማጥፋት ሰፉ ይከለክላል፡፡ ከእነዚኽ ኹሉ ተግባራት የተነሣ ደግሞ እግዚአብሔርም በፍጥረቱ ይደሰታል ተብሎ ይታመናል፡፡ ሌላው ቀርቶ፥ እግዚአብሔር [ዋቃ] ራሱ ደግሞ የፈጠረውንና የሠራውን ሥርዓት እንደማያዛንፍ የሚታመንበት ነው፡- በዝናብ አብቅሎ፣ በፀሐይ አብስሎ ፍጥረቱን መመገብ እንዳያቋርጥ ‹‹አንተም ሰፉህን ጠብቅ፤ ሰማይንና ምድርን አስታርቅ!›› ተብሎ ይለመናልና፡፡[4] በአጠቃላይ፥ ሰፉን ማክበር፥ በፈጣሪና ፍጥረቱ መካከል ያለውን ሚዛን (check and balance system) መጠበቅ ነው ሊባል ይችላል፡፡ በዚኽም የሰው ልጆች አኗኗር ይቃናል፤ የዓለም ሰላም ይረጋገጣል፡፡ በአንጻሩ፥ ሰፉ ሲጣስ ግን በሰውና እግዚአብሔር፣ በሰዎችና ሰዎች፣ በሰዎችና አራዊት፣ በሰዎችና ምድሪቱ፣ ወዘተ. መካከል ያለው ሰላማዊ መስተጋብር ይቃወሳል፤ ጥፋትና ሞትን ያስከትላል! ምንም እንኳ እንደ ታቦር ዋሚ ያሉት የዘመናችን ጸሓፍት ከራሳቸው እሳቤና ፍላጎት ጋር ለማቀራረብ ሲሉ፥ ‹‹የዋቄፈና እምነት እሴት›› አድርገው ሊያቀርቡት ቢሞክሩም፥ ሰፉ ግን የመላው ኦሮሞ ማኅበረሰብ ማኅበራዊ ፍልስፍናና ኑሮ አስኳል መኾኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡[5]
ከቅርብ ጊዜያት ወዲኽ ለኦሮሞ ሕዝብ ነጻነት እንታገላለን የሚሉ አንዳንድ አካላት የሰውን ልጅ በማንነቱ ብቻ ላይተው በአሰቃቂ ኹኔታ እየገደሉ (እያረዱ) መኾናቸውን ስንሰማ ነባሩ የማኅበረሰቡ እሴት ምን ያህል እንደተሸረሸረ እናስተውላለን፡፡ የጥንቱ ኦሮሞስ፥ መግደል ይቅርና ለመመረቅ ሲፈልግ እንኳ አስፈቅዶ ነው፤ ‹‹na ofkalchaa!›› ይላል፤ ‹‹በእናንተ ፊት በመናገሬ /ለመመረቅ በመነሳቴ/ ይቅር በሉኝ!›› እንደማለት ነው፡፡ “Ofkali” (ፈቅደንልሃል፤ ሳትሳቀቅ ተናገር!) ካልተባለ በቀርም አይናገርም! እንኳንስ ሰው አጋድሞ ሊያርድ ቀርቶ፥ ሥጋ እያማረው ከብቱን አርዶ ለመብላት እንኳ የሚሰቀቅ፣ ‹‹የራስን ልጅ እንደመግደል›› የሚቆጥር፣ ‹‹በሕይወት እያሉ የጠቀሙኝን ለሆዴ ስል ልገድላቸው አይገባም›› የሚል ነበር፡- ‹‹በራሳቸው በረት የተወለደና ያሳደጉትን ከብት በሌላ ለውጠው ካልኾነ በቀር ራሱን አርደው አይበሉም ነበር፡፡ ምክንያቱም፥ ‹በእጃችን ተወልዶ በእጃችን ያደገውን ጥለን በስለት አንገቱን መቁረጥ ያሳዝናል› ይላሉ›› እንዲል፡፡[6] ሕዝቡ እንኳንስ ለሰው ለእንስሳት የነበረውን ፍቅርና ርኅራኄ አስመልክቶ ፕሮፌሰር ጌታቸውም ስለ አንድ የኦሮሞ ገበሬ ትዝብታቸውን እንዲህ አስፍረዋል፡- ‹‹በሬውን ገበያ ወስዶ ከሸጠው በኋላ መልሶ ቀምቶት መጣ፡፡ ‹ለምን ሽጠህ ደግሞ መለስከው?› ተብሎ ሲጠየቅ ‹ሲቸግረኝ ሸጥኩት፣ የገዛው ሰው ግን የግጦሽ መሬት የለውም፤ በሬዬ በረሃብ ከሚሞት እኔ ልቸገር ብዬ ነው› አለ›› በሚል፡፡[7]
ኦሮሞና የሥነ-ምግባር ሕጉ (ሰፉ) እንዲኽ ከነበረ፥ በድንጋይ ወግሮ፣ በሽመል ደብድቦና በሜንጫ አርዶ ሰውን የሚገድል ‹‹ኦሮሞ ነኝ›› ባይ ከወዴት መጣ? የዘጠኝ ወር ነፍሰ ጡር አርዶና አወራርዶ የሚጨፍር ቡድን እንስሳትን ለማረድ እንኳ ይሰቀቅ ከነበረው ማኅበረሰብ ውስጥ እንዴት ሊወጣ ቻለ? መግደሉ ሳያንስ፥ ‹‹የነፍጠኛ ሬሳ በመሬታችን ላይ አይቀበርም!›› በሚል የሟችን አስከሬን ጭምር የሚያንገላታ ፍጥረት ከወዴት ተገኘ? ወላድ እናቶችን እንደ እግዚአብሔር መልእክተኛ ከሚቆጥር ሕዝብ መካከል አንዲትን እንስት ለአራትና አምስት የሚደፍሩ ወንዶች እንዴት ተወለዱ? ለመኾኑ፥ የኦሮሞ ሰፉ ወዴት አለ?!
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
#አንብቡ! #ገንቢ_አስተያየቶችንም_ከበሳል_ትችቶች_ጋር_ስጡ! #ስድብ_በባህል_ነውር_በሃይማኖት_ደግሞ_ኃጢአት_ነውና_እንተወዉ! #እውነት https://www.facebook.com/ewnetmediapage የሚለውን ገጻችንን #Like በማድረግ ቤተሰቦቻችን ሁኑ! ለሌሎችም #Share በማድረግ ጽሑፎችን እንዲያነቡ፣ እንዲቀላቀሉንም ጋብዙ!
#በቴሌግራም ቻናላችንም ይከታተሉን https://t.me/ewnetmedia
#አውነትን_በመግለጥና_ሐሰትን_በማጋለጥ_የሀገርን_ሰላምና_የሕዝብን_አንድነት_ለመጠበቅ_እንትጋ!
[1] በማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል አማካይነት ተጠንቶ፥ በ ‹‹የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥናት መጽሔት›› (ቅጽ-2፣ 2004 ዓ.ም) ላይ የታተመውን ልብ ይሏል፡፡
[2] Lambert, Oromo Religion: an attempt to understand; 1990:172-339.
[3] “Saffu is a mutual relationship between elements of the social and cosmic orders which maintains practice obligatory through ethical conduct” (Gemetchu Megerssa; Oromumma: Tradition, Consciousness and Identity. In: Baxter, et al; Being and Becoming Oromo, 1996:97).
[4] Dirribii Damussee Bokkuu, Seenaa Eenyummaa Oromoo; 2007:248.
[5] ታቦር ዋሚ፤ የውገና ድርሰቶችና የታሪክ እውነቶች፤ 2006 ዓ.ም፣ ገጽ.208-209፡፡
[6] ጀቤሣ ኤጄታ (ባላምበራስ)፤ የኦሮሞ ብሔር ባህልና አጭር ታሪክ፤ ገጽ.12፡፡
[7] ጌታቸው ኃይሌ፤ የአባ ባሕርይ ድርሰቶች፤ 1995 ዓ.ም፣ ገጽ.19::
