EwnetMedia 2022
EwnetMedia
የተሰባኪያንን ባህል ማወቅ፡- የትኩረት አቅጣጫን ለመወሰን፣ ከስህተትም ለመጠበቅ!
==================================
የወንጌሉን የምሥራች ለተሰባኪያን ለማድረስ በምናደርጋቸው ጥረቶች ኹሉ የሕዝቡን ባህል ጠንቅቀን ማወቃችን፥ በአንድ በኩል በምን ጉዳይ ላይ ማተኮር እንዳለብን በቂ ፍንጭ እናገኛለን፤ የተለየ አጽንዖት የሚሹ አንዳንድ ጉዳዮች በተለያዩ ባህሎች ውስጥ ይኖራሉና፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፥ አላስፈላጊ የስህተት መንገድ ውስጥ ሳንገባ በጥንቃቄ እንድናገለግል ያግዘናል፡፡

አንድን ሕዝብ ከሌሎች የሚለዩት ባህላዊ ድርጊቶች ካሉ ሕዝቡ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴውንም ከዚያው አንጻር ስለሚቃኘው ስናስተምር የት ላይ ማትኮር እንደሚገባን እንረዳበታለን፡፡ እናም፥ የትምህርት አሰጣጥ ይዘቱና ሚዛኑ (curricullum content & credit hour) ጭምር በኹሉም የአገሪቱ ክፍሎች ላሉ ምእመናን ኹሉ ተመሳሳይ ሊኾን አይገባውም ነበር፡፡ ለምሳሌ፡-
(1) ምግቡም፣ ልብሱም፣ ጌጣጌጡም፣ ክብሩም ከእንስሳት ተዋጽዖ ጋር ለተቆራኘውን የኦሮሞ ሕዝብ የጥሉላት አጽዋማት ጉዳይ በአንዲት የመድረክ ስብከት ልንለውጠው አንችልም፡፡ በተለይ አመጋገቡ የእንስሳት ተዋጽዖ የሚበዛበት መኾኑ ከጥሉላት መጾም ከባዱ ፈተናው ነው፡፡ ቡና እንኳ ያለ ወተትና ቅቤ የማይጠጣበት፣ ‹‹ቡና ጠጡ›› ተብሎ ‹‹ወተት›› በሚቀዳበት፣ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ለቅንጦት የሚዘጋጀው ገንፎ በየዕለቱ በቅቤ ተጨማልቆ ‹‹እንደ ቆሎ›› መቅረብ በተለመደበት የኦሮሞ ማኅበረሰብ ስለ (ጥሉላት) ጾም ከማሳመን በላይ የሰባኪውን ‹‹ተጋድሎ›› የሚጠይቅ ነገር ምን አለ? ሕዝቡም እነዚህን ምግቦች ለመተው ከራሱና ከሌሎች የማኅበረሰቡ አጽራረ ቤተ ክርስቲያን ጋር የሚያደርገው ተጋድሎ ሌላውን ኀጢአት ለማሸነፍ ከሚያደርገው ተጋድሎ በላይ እንደኾነ ልንረዳለት ይገባል፡፡
(2) በአለባበሱም ረገድ፡- ለአብዛኛው የማኅበረሰቡ አባላት፥ ‹‹ጨሌ›› ማለት ‹‹ጌጥ›› ማለት ነው፡፡ በሌላ ሕዝብ ውስጥ ጨሌን በባዕድ አምልኮነቱ የሚያውቅ ሰባኪ፥ ‹‹እነዚኽ ሰዎች በባዕድ አምልኮ የተዋጡ ናቸው›› ብሎ ቢያስብ ዕውቀቱ ‹‹መንደርኛ›› ብቻ ሆኗል፡፡ ስለዚኽም፥ ‹‹የጨሌ ‹ድሪቶአችንን› ጥለን ወደ እግዚአብሔር እንመለስ›› የሚል ስብከት የኦሮሞ ኦርቶዶክሳውያን ወደ ታደሙበት ጉባኤ ይዞ የሚሔድ ሰባኪ ራሱ ‹‹ድሪቶ›› እስኪኾን ሊደበደብ ሁሉ ይችላል፤ ለእነርሱ ‹‹ክርስቲያን ለመኾን የግድ ባህላቸውን መተው›› እንዳለባቸው ይመስላቸዋልና፡፡ ደግሞም፥ ቡራቡሬና ጨሌ ያለበት ከኾነ ነጭ በነጭ መልበስ ‹‹ክርስቲያናዊ ባህል እንጂ የኹሉም ኢትዮጵያዊ አለመኾኑን›› አውቆ በጥንቃቄ መናገር ብልህነት ነው፡፡
(3) በንግድ ዓለም ውስጥ የማጭበርበር አዝማሚያን ያዳበረ ማኅበረሰብ ሲኖር ለቀራጮች የተሰጠውን ‹‹ከታዘዘላችሁ አብልጣችሁ አትውሰዱ›› የሚለውን የጌታ ትምህርት ማጠንከር ይገባል (ሉቃ.3፥13)፡፡
(4) ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ‹‹ደም መላሽ›› ተብሎ ላደገና ‹‹ዱር ቤቴ›› ዘፈኑ ለኾነ ሕዝብ ‹‹አትግደል›› ከሚለው ትእዛዝ በላይ ዋና ትምህርት የለም፡፡ ይኽ ሕዝብ ዓርብ ጧት ‹‹ጦሙ እስኪደርስ፣ በባዶ አፉ›› ጠላቱን ተበቅሎ (ገድሎ) ሊመጣ ኹሉ ይችላልና፡፡ ልጆቻቸውን በዚኽ ሥነ-ልቡና የሚያሳድጉትንም የማኅበረሰብ አካላት ጠንቅቆ ማወቅ ይጠይቃል፡፡[1]
(5) በአንደበታቸው ‹‹በሰንበት ቅጠል እንኳ አልበጥስም›› እያሉ በዚያው ዕለት በየመጠጥ ቤቱ የሚሰክሩና ዝሙት የሚፈጽሙትን ሰዎች፥ ጌታቸውን ሰቅለው ከገደሉ በኋላ ‹‹ሥጋው በሰንበት መስቀል ላይ እንዳይውል›› ከሚጠነቀቁት ግብዝ አይሁድ ለይቶ ማየት አይቻልም (ዮሐ.19፥31)፡፡
(6) መንግሥት በታክስ መልክ ከሕዝብ እየቆረጠ በየወሩ የሚከፍላቸው ሠራተኞች በጉቦና ሙስና ሕዝቡን ሲያማርሩ፥ ‹‹ደመወዛችሁ ይብቃችሁ›› ብሎ መገሠጽ ተገቢ ነው (ሉቃ.3፥14)፡፡
እነዚኽን ኹሉ የስብከተ ወንጌል ትኩረቶች መለየት የሚቻለው የተሰባኪውን ሕዝብ ባህልና ሥነ-ልቡና በጥንቃቄ በማጤን ነው፡፡ ሕዝቡን ማእከል ማድረግ ማለት እንዲህ የትኩረት ጉዳዮችን መለየትንም ያካትታል፡፡
የሕዝቡን ባህል ጠንቅቆ ማወቅ ያልተፈለገ ስህተት ውስጥ እንዳንገባም ይጠብቀናል፣ በጥንቃቄ እንድናገለግል ይረዳናል፡፡ በንግግርም ይኹን በድርጊት የምንፈጽማቸው ስህተቶች ለወንጌል አገልግሎት እንቅፋት የመኾን ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡ ለምሳሌ፡-
✍️ አንዳንድ ቃላት በአንዱ አከባቢ ጥሩ ይኾኑና ሌላው ቦታ ላይ ደግሞ ስድብ ሆነው ይገኛሉ፤
✍️ ከሌላ ቦታ የሔደው ሰባኪ ‹‹ነውር›› ብሎ የሚናገረው ባህል ሕዝቡ ግን ‹‹እንደ ዐይን ብሌን›› የሚጠነቀቅለት ሊኾን ይችላል፤
✍️ ወንድ ሴትን ልጅ በመጨበጥ ሰላም ካለ ሌላ ትርጉም የሚሰጥበት፣ ሊያስወግርም የሚችል እርምጃ ሊያስከትል የሚችልባቸው ቦታዎች አሉ፤
✍️ የአካል እንቅስቃሴዎች በተለያዩ ቦታዎች የተለያዩ ትርጉሞች አሉአቸው፤
✍️ ‹‹ያለ ዕድሜ ጋብቻ ክልክል ነው›› ብለን በምንናገርበት እኛ በምንበይነው ዕድሜ ላይ ማግባት የሚያሳፍርበት ማኅበረሰብ አለ፤
✍️ ሰባኪው ካደገበት ማኅበረሰብ ባህል ተነስቶ፥ ‹‹ጨሌ የአምልኮ ነውና ካላስወገዳችሁት ወዮላችሁ!›› በሚል ኦሮሞን ቢሰብክ ያንን መድረክ መልሶ የማግኘት ዕድሉ ጠባብ ነው፤ ኦርቶዶክሳውያኑን ከሃይማኖታቸው ገፍትረው ከሚያስወጧቸው ድርጊቶች መካከልም መሰል አገላለጾች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ለጌጥ እንደሚጠቀሙበት አውቆና አስታውሶ ከማጌጫነት አልፈው ሌላ ትርጉም እንዳይሰጡት ማስተማር ግን ትክክል ይኾናል፡፡
✍️ በሌላ በኩል፥ በቡራቡሬ/ባለ ቀለማት አልባሳቱ ለሚታወቀው ሕዝብ፡- ‹‹ነጭ በነጭ የኾነ ኢትዮጵያዊ አለባበሳችን›› የሚለው አገላለጽ ኦሮሞን ከኢትዮጵያዊነቱ አሽቀንጥሮ እንደሚያስወጣዉ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ምንም እንኳን ኢትዮጵያዊነት አለባበስን ጨምሮ ከክርስትና እሴቶች የወሰዳቸው በርካታ ባህሎች መኖራቸው ባይካድም፥ ‹‹ነጭ በነጭ አለባበስ›› ግን ለኹሉም ኢትዮጵያዊ ላይኾን ይችላል፤ ‹‹ክርስቲያናዊ አለባበስ›› ቢባል ግን በአንጻራዊነት ሃይማኖታዊ ማብራሪያ ይኖረዋል፡፡
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
#አንብቡ! #ገንቢ_አስተያየቶችንም_ከበሳል_ትችቶች_ጋር_ስጡ! #ስድብ_በባህል_ነውር_በሃይማኖት_ደግሞ_ኃጢአት_ነውና_እንተወዉ! #እውነት https://www.facebook.com/ewnetmediapage የሚለውን ገጻችንን #Like በማድረግ ቤተሰቦቻችን ሁኑ! ለሌሎችም #Share በማድረግ ጽሑፎችን እንዲያነቡ፣ እንዲቀላቀሉንም ጋብዙ!
#በቴሌግራም ቻናላችንም ይከታተሉን https://t.me/ewnetmedia
#አውነትን_በመግለጥና_ሐሰትን_በማጋለጥ_የሀገርን_ሰላምና_የሕዝብን_አንድነት_ለመጠበቅ_እንትጋ!
[1] ምንም እንኳን ይኽ በአብዛኛው የአማራውን ማኅበረሰብ የሚመለከት ቢኾንም፥ በጥንቱ የኦሮሞ ታሪክና የገዳ ሥርዓት ውስጥም፥ አንድ ሰው ትልቅ አውሬ (አንበሳ፣ ጎሽ፣ ነብር፣ ዝሆን) ወይም እነርሱ ‹‹ጠላት›› ብለው የሚገልጹአቸውን ሰዎች ያልገደለ ጠጉሩን አይላጭም ነበር (ጌታቸው ኃይሌ፤ የአባ ባሕርይ ድርሰቶች፤ 1995 ዓ.ም፣ ገጽ.91 እና 127 )፡፡ ይኽ ባህል ዛሬ ላይ እምብዛም ነው፤ አስተሳሰቡም ጭምር ጠፍቷል ማለት ይቻላል፡፡
