EwnetMedia 2022

EwnetMedia 2022

EwnetMedia

‹‹ከፍረጃ ይልቅ ‹አላውቅም› ብትሉ ካላዋቂ አጥፊነት ትተርፋላችሁ!››

(ሊቀ ማእምራን ደጉዓለም ካሣ)

==================================

አንድ ቀን ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሐዲሳት መምህር ከነበሩት (በረከታቸው ይደርብንና) የኔታ ደጉዓለም ካሣ ከልጅነቴ ገጠመኝ ጋር የሚመሳሰል ቁምነገር አደመጥኩ፡፡ ያስተምሩን ከነበረው ክፍል በመስኮት በኩል ወደ ውጭ አጮልቀው እያሳዩን፡- ‹‹ይኽ የእንጦጦ አቅጣጫ ሰማይ ይታያችኋል አይደል? አዎ፤ እዚህ ኾነን እንደምንመለከተው ሰማዩ እንጦጦ ተራራ ላይ ድፍት ያለ ስለሚመስል ከተራራው ጀርባ ሌላ ሀገር ያለ አይመስለንም፡፡ በቦታው ላይ ስንደርስ ግን መሬት የነካ ይመስል የነበረው ሰማይ እኛ ከደረስንበት በእጅጉ ይርቀናል፤ የሌለ የመሰለን መሬትም የማይደረስበት ሰፊ ኾኖ እናገኘዋለን፡፡ እናም፥ አንድ ሰው አራት ኪሎ ቆሞ በሚረዳው እውቀቱ ብቻ ‹ከእንጦጦ በኋላ መሬት የሚባል ነገር የለም› ብሎ ማሰብ የለበትም! ይኽ የእኛን ማሰብያ አድማስ ውስንነት የሚያሳይ እንጂ የሰማዩን ርቀት ምጡቅነት፣ የምድሪቱንም ስፋት ልክ የሚገልጽ አይደለም፡፡ እናም፥ ምንጊዜም አዲስ ነገር ሲገጥማችሁ ቶሎ ከመፈረጅና ከመውቀስ ይልቅ ‹ገና ያላወቅሁት ነገር ቢኖር ነው› ብትሉ ካላዋቂ አጥፊነት ትተርፋላችሁ!›› አሉን፡፡ ኹሉም ታዳሚ በጣም ተገርሞ እንደነበር አስታውሳለሁ፤ ለእኔ ግን ከመገረምም በላይ ከልጅነት ገጠመኜ ጋር ገጥሞልኝም ስለነበር ደስታዬ ወደር አልነበረውም፡፡ እናም፥ ክት ከኾነው ማስታወሻዬ ላይ አሰፈርኩት፤ አኹን ደግሞ ለእናንተ አጋራሁት፡፡

እነሆ ከእነዚህ ነገሮች በኋላ ለኅሊናዬ የሚጎረብጡ ነገሮች በሰማሁ ቁጥር፣ በጉዳዩ ዙርያ የተሻለ ግንዛቤ እያለኝ እንኳን ‹‹አውቃለሁ!›› ብዬ ከመናገርና ከመጻፍ መቆጠብን እመርጥ ነበር፤ ምናልባትም እኔ ከደረስኩበት እውነት የተለየ መረጃና ማስረጃ ሌሎች ዘንድ ይኖራል በሚል፡፡ በሌሎች ጉዳዮች በተናጋሪነቴ የምታወቀውን ያህል በታሪክ ጉዳዮች ላይ ግን ዝምታን እመርጥ ነበር፤ ሰው ተናግሮ ትውልዱን ሊጠቅም ካልቻለ ቢያንስ ዝም ቢል ተጨማሪ ጥፋት አይፈጽምም ብዬ ስለማስብ፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በደንብ የማውቃቸው ወንድሞቼና እህቶቼ ጭምር የዐዲሱ ትርክት ፊታውራሪዎች ኾነውና ራሳቸውን የኦሮሞ ሕዝብ እንደራሴ በማድረግ የማያውቁትን ጭምር እጅግ ከፍ ባለ ድምፅ እየደሰኮሩ የሚዲያ ላይ አርበኞች መኾናቸውን ሳይና ስሰማ ደግሞ በዝምታዬ ይበልጥ ደስተኛ ሆንኩ፤ በእነርሱና በሚዲያዎቹ ቦታ ግን እኔ መሸማቀቄ አልቀረም፡፡ 

ለዚህ መጽሐፍ መዘግየትም ትልቁን ቦታ የሚወስዱት ኹለት መሠረታዊ ነጥቦች ናቸው፡- አንደኛው በዚኹ አቋሜ መሠረት ያልሰማሁትን፣ ያላነበብኩትንና ያላየሁትን አዲስ ነገር ፍለጋ፡፡ እንዲያውም በኢትዮጵያም ይኹን በኦሮሚያ ጉዳዮች ላይ ‹‹ታሪክ›› የሚል ርእስ ይዞ የወጣ መጽሐፍን ተሽቀዳድሜ እገዛለሁ፤ አንዳች የተለየ ነገር ባገኝበት ብዬ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በመጽሐፋቸው ርእስ ላይ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከጥንት እስከ አሁን! እስካሁን ያልተሰሙና ያልተነበቡ! በታሪክ ክፍለ ጊዜያት ያልተነገሩ!›› የሚሉ የመጽሐፉ ማሻሻጫ ቃላትን በርእሱ ላይ በመጨመር ልቤን ክፉኛ ይሰቅሉታል፤ በመጨረሻ ግን የእነርሱን ልዩ የሚያደርገው ርእሱን ከቁምነገሩ በላይ ማጮኻቸው ብቻ ኾኖ አገኘዋለሁ፡፡ በኦሮሚያ ላይ ያለውን ውዝግብ የተረዱት አንዳንዶችም እንደዚሁ አጓጊ ርእሶችን ከላይ በማስቀመጥ መድኀኒት ፍለጋ ለሚኳትነው ታማሚ ትውልድ እየቸበቸቡ ኪሳቸውን ከማደለብ ያለፈ ያን ያህል ለውጥ አላመጡም፡፡ አንዳንዶቹ ጸሓፍት እንዲያውም አውቀውትም ይኹን ሳያውቁት ቁስሉን ከማከም ይልቅ ይበልጥ እንዲያመረቅዝ አድርገዋል፤ አንደኛውን ስሕተት ለማረም ሲሉም ወደ ሌላ ተጨማሪ ስሕተት የሚወስደውን አካሄድ ተከትለዋል (ጥቂቶቹን በዚኹ መጽሐፍ ውስጥ በተገቢው ቦታ እየጠቀስኩ ለማሳየት ሞክሬአለሁ)፡፡ 

በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹ልብ የሚገኘው በ40 ዓመት›› በሚለው የሀገሬ ብሂል መሠረት ሰከን ብዬ ነገሮችን ወደማስተውልበት ዐርባዬ እስክጠጋ ታግሻለሁ፡፡ እናም፥ እኔ በዚኽ አካሄድ ‹‹አዲስና ሚዛናዊ ነገር›› ፍለጋ ለበርካታ ዓመታት ስባዝን ግን ነጭ ውሸቶች ጭምር ተደጋግመው ከመነገራቸው የተነሣ እውነት እየመሰሉ፣ ከሚጠበቀውም በላይ በትውልዱ አእምሮ ውስጥ ተደላድለው እየተቀመጡ፣ እጅግ በፈጠነ ኹኔታም እንግዳ አስተሳሰቦችንና ድርጊቶችን መውለድ ጀመሩ፡፡ እኔ የማውቀውን ብቻ ጽፌ ትውልድ እንዳላጠፋ ስሰጋ የማውቀውም ሌላ ቅርጽ ይዞ የባሰ ጥፋት ማምጣት ጀመረ፡፡ እናም፥ ቢያንስ በደረስኩበትና በተረዳኹበት መጠን፣ የማውቀውን እየተናገርኩና እየጻፍኩ ያልደረስኩበትን መፈለግ፤ ከእኔ የተሻሉት ደግሞ አበጥረው እንዲተቹ፣ በተሻለ አቅምና መረጃም ብቅ እንዲሉ መቀስቀሱ ይበልጥ ትውልድን ይታደግ ይኾናል በሚል ቅን ኅሊና ያለችኝን እነሆ ማለቱን መረጥኹ፡፡

አኹንም ቢኾን ግን፥ ለመጻፍ የሞከርኩት ‹‹የታሪክ መጽሐፍ›› ሳይኾን የራሴን መረዳት ነውና በዚኽ ጽሑፌ ውስጥ ትክክለኛውን ታሪክ ሳልደርስበት ቀርቼ በስሕተት ሕዝብን፣ ቤተ እምነቶችን፣ ኢትዮጵያንና መሪዎቿን አቃልዬ ከኾነ ፈጣሪ ይቅር እንዲለኝ እለምናለሁ፡፡ በአንጻሩ ደግሞ እነዚኽን ኹሉ ከሚገባቸው ትክክለኛ ክብር በላይ በማጋነን አቅርቤ ከኾነ ደግሞ የታሪክና ትውልድን ይቅርታ እማጸናለኹ! በዚያም ኾነ በዚኽ እርምት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ሲኖሩ በእናንተው ግብረ-መልስ መሠረት በቀጣይ ኅትመቶች የሚታረሙ ይኾናል፡፡ የእኔ ዋና ዓላማ ግን የትኛውንም አካል ለመውቀስም፣ ለማወደስም ሳይኾን ትውልድ እውነታውን አውቆ በተሳሳተ የታሪክ ትርክት ከመወዛገብ እንዲድን፣ ወደ ትክክለኛው መሥመርም ተመልሶ ሰላማዊ ኑሮውን እንዲመራ ብቻ ነው!

መቅድሙ ከተአምሩ ረዝሞ እንዳያሰለቻችሁ በዚኹ ይብቃኝ፤ መልካም ንባብ!

(ከጊንጊልቻ መጽሐፍ መቅድም የተወሰደ፤ ክልስ ዕትም፣ ገጽ XVIII-XX)

~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~

#አንብቡ! #ገንቢ_አስተያየቶችንም_ከበሳል_ትችቶች_ጋር_ስጡ! #ስድብ_በባህል_ነውር_በሃይማኖት_ደግሞ_ኃጢአት_ነውና_እንተወዉ! #እውነት https://www.facebook.com/ewnetmediapage የሚለውን ገጻችንን #Like በማድረግ ቤተሰቦቻችን ሁኑ!  ለሌሎችም #Share በማድረግ ጽሑፎችን እንዲያነቡ፣ እንዲቀላቀሉንም ጋብዙ!

#በቴሌግራም ቻናላችንም ይከታተሉን https://t.me/ewnetmedia

#አውነትን_በመግለጥና_ሐሰትን_በማጋለጥ_የሀገርን_ሰላምና_የሕዝብን_አንድነት_ለመጠበቅ_እንትጋ!


Report Page