EwnetMedia 2022
EwnetMedia
የሃይማኖት ምስጢርን በመግለጥ ረገድ ባህልን የመረዳት ጠቀሜታ!
==================================
የምናስተምረውን ሕዝብ ባህል ጠንቅቀን ማወቃችን የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር የበለጠ ግልጽ ለማድረግ ያግዛል፡፡ በተለይም፥ አዎንታዊ እሴቶቻቸውን በማበረታታት፣ በዚያ አማካይነት ጥልቅ ሃይማኖታዊ ጭብጦችን በቀላሉ ለማስረዳት በእጅጉ ይጠቅማል፡፡

አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦች እርስ በርስ የሚጣረሱ እስኪመስለን ድረስ ከምንወዛገብባቸው ምክንያቶች (የብዥታው መነሻዎች) አንዱ ባህሉን ጠንቅቀን አለማወቃችን ነው፡፡ እናም፥ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነብ ሰው የተጻፈለትን ሕዝብ እና የጸሓፊውን ባህል ማወቅ ይጠበቅበታል፡፡ ለምሳሌ፡- አንድ የሀገራችን ሰው የእስራኤልን የአነጋገር ዘይቤ ጠንቅቆ ካላወቀ፡- ‹‹አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?›› የሚለው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ንግግር (ዮሐ.2፥4) እና ‹‹አባትህንና እናትህን አክብር›› የሚለው ትእዛዝ (ዘጸ.20፥12) ሊጋጭበት ይችላል፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስን ባህል ቢያውቅ ግን፥በቀላሉ ሊረዳውና ሊጣላ የማይችል መኾኑን መገንዘብ ይችላል፡፡[1]
ከምንም በላይ ደግሞ፥ ታላቁ መጽሐፋችን የሚነግረን፣ ጌታችንም ያስተማረው በምሳሌ ነው (መዝ.78፥2፤ ማቴ.13፥34-35)፡- ለገበሬዎች በዘር (ማቴ.13፥1-32)፤ ለአርብቶ አደሮችም በበግ እረኝነት (ዮሐ.10፥1-16)፤ ለነጋዴዎች በዕንቁ (ማቴ.13፥45-46)፤ ለሴቶች በሚቀዱት ውኃ (ዮሐ.4፥4-30) እና ለመጋገርያ በሚጠቀሙበት እርሾ (ማቴ.13፥33፤ ሉቃ.13፥21)፤ ወዘተ፡፡
በተመሳሳይ መልኩ አንድምታችንም ሃይማኖታዊ ምስጢራትን የሚያብራራው ‹‹ኢትዮጵያዊ ባህልን›› ተከትሎ ነው፤ አብርኆቱ የሚደረገው ለሀገሬው ነውና፡፡ ለምሳሌ፡-
✍️ ‹‹ኦ ድንግል፥ አኮ ወራዙት ስፉጣን ዘናዘዙኪ አላ መላእክተ ሰማይ ሐወጹኪ…›› የሚለውን ገጸ ንባብ አንድምታችን ሲተረጉመው፡- ‹‹…ሰውን በሎሚ፣ በቀለበት የሚያታልሉ ወራዙት [ወጣቶች] ያረጋጉሽ አይደለሽም›› ይለዋል፡፡[2] በቀለበት ደናግላንን ማማለል በሌላው ክፍለ ዓለምም የሚስተዋል ቢኾንም፥ የሎሚው ግን በዋናነት የኢትዮጵያ ባህል ነው፤ ‹‹ሎሚ ጣሉባት በደረቷ….ሎሚ ብወረውር ደረቱን መታሁት….›› እያሉ የዘፈኑትም ኢትዮጵያውያን ብቻ ናቸው፡፡
✍️ (2) ከውዳሴ ማርያም ውስጥ በዕለተ ሰኞ ላይ ብቻ ‹‹ማርያም›› የሚል ቃል የለም፡፡ ይኽ ለምን እንደኾነ ዝርዝር ማብራሪያ የምናገኘው በማግሰኞው አንድምታ ላይ ነው፤ ‹‹ትላንት ስሟን አላነሣም፤ ዛሬ [ማግሰኞ] ስሟን አነሣ፡፡ በእንግዳ ልማድ እንግዳን ዕለቱን [በመጀመሪያው ቀን] ስሙን አይጠሩትም፤ ከዋለ ካደረ በኋላ ግን ስሙን ይጠሩታል፡፡ በዚያ ልማድ…ቅዱስ ኤፍሬምም እንዲሁ ስሟን አላነሳም፤ አሁን [ዕለተ ሠሉስ] ላይ ግን ቢለምዳት በስሟ ጠራት›› ይላል፡፡[3] ይኽ በቀጥታ ከኢትዮጵያ ባህል አንጻር ተተርጉሞ እንጂ በነጮቹ ባህልማ የትውውቅ መጀመሪያው በስም መጠራራት እንደኾነ ልብ ይሏል!
የማኅበረሰቡን ፈሊጣዊ አነጋገሮችና አባባሎችን በመጠቀም፣ እንዲሁም በተለመዱ የሕዝቡ ባህላዊ ተረቶችንና ታሪኮች በማስታከክ የረቀቁ የሃይማኖት ምስጢራትን ማጉላት የሚቻልባቸው ዕድሎችም አሉ፡፡ መምህራነ ወንጌል፥ ‹‹የትኛውን ሥነ-ቃል ለየትኛው ጽንሰ ሐሳብ ልጠቀም?›› የሚለውን ካወቁ (ሥነ-ቃሎቹን ማወቅ ብቻ ሳይኾን የመምረጥ ችሎታ ካላቸው) ብዙ መልፋት አይጠበቅባቸውም፤ ለአንድ ሰዓት የተሰበከን ስብከት አንድ ዐረፍተ ነገር በማይሞላ ሥነ-ቃል ለማስጨበጥ የሚቻልበት ጥሩ አጋጣሚ አለና፡፡ ለምሳሌ፡- በአንድምታዎቻችን ውስጥ የምናገኛቸው በርካታ ‹‹ግጥማዊ›› አገላለጾች ለዚኽ ማሳያ ናቸው፡፡[4] ሌላው ቀርቶ፥ ሐዋርያው ቶማስ የእመቤታችንን ትንሣኤ ‹‹የተጠራጠረ መምሰሉ›› እንኳ የተገለጸው በኢትዮጵያዊው ባህልና ቋንቋ ነው፡- ‹‹ሞት በጥር፣ በነሐሴ መቃብር…እንዴት ይኾናል?›› በሚል፡፡ ‹‹ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ፥ አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም›› (ማቴ.6፥15) የሚለውን የጌታ ትምህርት በምእመናን ልቡና በደንብ ቀርጾ ለማስቀረት፡- ‹‹ሳል ይዞ ስርቆት፣ ቂም ይዞ ጸሎት›› ከምትለዋ በላይ ቅልብጭ ያለች አገላለጽ አትገኝም፡፡
በባህላዊ እምነቶችና ድርጊቶች ደረጃ፣ የኢትዮጵያውያን ሕዝቦች ነባራዊ ኹኔታ ስንመረምርም፥ የክርስትናን ሐዋርያዊ ተልእኮ የሚያፋጥኑ ርካታ እሴቶችን እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ፡- የሲዳማ ማኅበረሰብ ‹‹ወራሞ›› በሚል የሚጠራው የተመረጠ ኮርማ፣ በጾታ እንጂ በክብር ከበሬ ጋር የማይነጻጸር፣ በሕይወት እያለ የሚከበርና በኋላም ለመስዋዕት የተገባ (የሚቀርብ)፣ የፈለገውን እህል ቢበላ እንኳ የማይከለከል (የማይመታ) ‹‹ገደብ አለፍ›› ነጻነት ያለው፣ በአጠቃላይ በስስት ዓይን የሚታይ ክቡር እንስሳ አለው፤ የማኅበረሰቡ ጀግኖችም በእንስሳው አንጻር ‹‹የእገለ ወራሞ›› ብለው ሲፎክሩ ትልቅ ኩራት ይሰማቸዋል፡፡[5] በዚኽ ላይ አትኩሮ በርካታ ሃይማኖታዊ ጭብጦችን ለማኅበረሰቡ ማስረዳት ይቻላል፡፡
የካፋ ሕዝብ ደግሞ፥ መልካም ሥነ ምግባርን ከተላበሰው የሰላምታ አሰጣጥ ባህላቸው የተነሣ ታናናሾች ለዕድሜ ታላላቆቻቸው ሰላምታ ሲሰጡ፡- ‹‹ሾዎች ቀቦን›› ይሏቸዋል፤ በጥሬ ትርጉሙ ‹‹መሬት ልተኛልዎ›› እንደማለት ሲኾን ታላቅም ለዚህ ሰላምታ አጸፋ ሲሰጥ ‹‹ሾወ ዳምባ ዴቢ›› ይላል፤ ‹‹ከመሬት በላይ ኑር›› ማለት ነው፡፡[6] ለዚኽ ሕዝብ የክርስትናን ሥነ-ምግባር ለማስተማር ብዙም ላንቸገር እንችላለን!
በክስታኔ ቤተ ጉራጌ (በተለይ) አንድ ለአቅመ አዳም/ሔዋን የደረሰ/ች ልጅ ቢኖር እናቱ ወይም አባቱ በሞቱበት ጊዜ ሽማግሌዎች ይሰበሰቡና፡- ‹‹ለመሆኑ አባትህና እናትህ በሕይወት ዘመናቸው ጦረሃል ወይ;›› ብለው ይጠይቁታል፡፡ ካልረዳ ግን መቃብሩ አከባቢ እንዳያለቅስና እንዳይቀብር ይደረጋል፡፡ ከተቀበረ በኋላም ሀፍረትን ለብሶ ብቻውን እንዲሄድ ይደረጋል፤ ‹‹እግዚአብሔር ያጥናህም›› አይባልም፤ የተረገመ ነውና፡፡ በአንጻሩ ሟቹን በአግባቡ የረዳና ያስታመመ (ከፍተኛ ባለውለታ የሆነ) ቤተሰብ መሆኑ በሁሉም ዘንድ ከተመሰከረ በሐዘኑ ወቅት ከጥቁር ይልቅ ነጭ ልብስ እንዲለብሱ ተደርጎ ቅቤ ተቀብተው በሕዝቡ መካከል ተቀምጠው ይመረቃሉ፤ ጸጸታቸውን ባደረጉት መልካም ተግባር ጨርሰዋልና ሐዘን አይገባቸውም ለማለት ነው፡፡[7] ይኽ ባህላዊ አስተሳሰብና ድርጊት ያለምንም መጨመርና መቀነስ የክርስትና እሴት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል (ሊበረታታ የሚገባ) ነው!
እነዚኽ ኹሉ አቀራረቦች በቀላሉ ለማስረዳት የምንቸገርባቸውንና ለማሳመን በእጅጉ የምንደክምባቸውን ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ጭብጦችን በሕዝቡ ልብ ውስጥ በቀላሉ ለማስቀመጥ ያስችሉናል፡፡ እናም፥ ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎችን ለመጠንቀቅ ከምናደርገው ዝግጅት ባሻገር (ምናልባትም ከዚያው ባልተናነሰ ትኩረት) እነዚኽንም ማጥናት፣ በተገቢው ቦታም መጠቀም አስፈላጊ ነው!
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
#አንብቡ! #ገንቢ_አስተያየቶችንም_ከበሳል_ትችቶች_ጋር_ስጡ! #ስድብ_በባህል_ነውር_በሃይማኖት_ደግሞ_ኃጢአት_ነውና_እንተወዉ! #እውነት https://www.facebook.com/ewnetmediapage የሚለውን ገጻችንን #Like በማድረግ ቤተሰቦቻችን ሁኑ! ለሌሎችም #Share በማድረግ ጽሑፎችን እንዲያነቡ፣ እንዲቀላቀሉንም ጋብዙ!
#በቴሌግራም ቻናላችንም ይከታተሉን https://t.me/ewnetmedia
#አውነትን_በመግለጥና_ሐሰትን_በማጋለጥ_የሀገርን_ሰላምና_የሕዝብን_አንድነት_ለመጠበቅ_እንትጋ!
[1] ዓባይነህ ካሤ (ዲ/ን)፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፥ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፤ 2ኛ መጽሐፍ፣ 1994 ዓ.ም፣ ገጽ.151፡፡
[2] መጽሐፈ ቅዳሴ፥ ንባቡና ትርጓሜው፤ 1988 ዓ.ም፣ ምዕ.5፣ ቁ.6፣ ገጽ.242፡፡
[3] ውዳሴ ማርያም አንድምታ፤ ዘሰሉስ፤ 1915 ዓ.ም፣ ገጽ.32-33፡፡
[4] እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ፣ እንደ አንድ ልብ መካሪ፤ እንደ ገል ቀጥቅጦ፣ እንደ ሰም አቅልጦ፤ በእጁ ጭብጥ፣ በእግሩ እርግጥ፤ ውኃ በገበታ፣ ሹመት በተርታ፣ የነገሩትን የማይረሳ፣ የለመኑትን የማይነሳ፣ የቄስ ቃል፣ አንድ ይበቃል፤ ወዘተ. የሚሉትን በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
[5] ቤታና ሄጤሶ፤ ሲዳማ፡-ሕዝብና ባሕሉ፤ 1983 ዓ.ም፣ ገጽ. 118-119፡፡
[6] በቀለ ወ/ማርያም አዴሎ፤ የካፋ ሕዝቦች እና መንግሥታት አጭር ታሪክ፤ 1996 ዓ.ም፡፡
[7] ወርቁ ተስፋ (አዘጋጅ)፣አይመለል፤ 1987 ዓ.ም፣ ገጽ.80፤ድንበሩ ዓለሙ፣ መንግሥቱ ኃ/ማርያም፣ ፍቅሬ ኃ/ማርያም፣ ተስፋዬ መኩሪያ፣ ተዘራች ቢረዳ፣ ግርማ ጥላሁን፣ ምትኩ ተሾመ፣ እንዲሁም የባህልና ስፖርት ባልደረቦች፤ ጎጎት፥ የጉራጌ ብሔረሰብ ታሪክ፣ ባህልና ቋንቋ፤ 1987 ዓ.ም፣ ገጽ.133፡፡
