Ethiopia

Ethiopia


የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 26ተኛ መደበኛ ስብሰባ የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል፡፡ 

1ኛ. የፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ የሁለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች የስራ ስንብትን አስመልክቶ የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ተመልክቷል።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የውሳኔ ሀሳቡን አቅርበዋል፡፡ የውሳኔ ሀሳቡም ቁጥር 2/2016 ሆኖ ለዝርዝር እይታ ለህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ ተመርቷል፡፡

2ኛ. የፌደራል መንግስት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010ን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ነው።

የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር የተከበሩ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት አዋጁ በስራ ላይ ከዋለ ስድስት አመት ያስቆጠረ መሆኑንና አሁን ካሉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ጋር ማጣጣም በማስፈለጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

እንዲሁም ነባሩ አዋጅ ስራ ላይ ከዋለ በኋላ በትግበራ ወቅት የታዩ ችግሮችን በመፍታት የመንግስትን የመፈጸም ብቃት በማጎልበት የዜጎችን ፍላጎት የሚያረካ አገለግሎት ለመስጠት የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት አስፈላጊ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ 

በሌላ በኩል የመንግስት ሰራተኞች የሰው ሀይል ምልመላና መረጣ ግልጽነት ባለው ውድድርና ብቃት ላይ የተመሰረተ ሆኖ ሁሉንም ባካተተና ብዝሀነትን በጠበቀ መልኩ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ስርአት መዘርጋት በማስፈለጉ ረቂቅ አዋጁ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

በረቂቅ አዋጁ ማሻሻያ ከተደረገባቸው ጉዳዮች ውስጥ የደሞዝ ጭማሪ፣ የደሞዝ እርከን፣ ክፍያና ጥቅማጥቅሞች ማትጊያና ማበረታቻ ስርአት እንዲሁም የሰራተኞች ብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ስልጠና አሰጣጥ ስራ ስምሪት እና ነጻ ገለልተኛ ስርአት መገንባት፣ የመንግስት ሰራተኛነት ውል ማቋረጥና ማራዘም የሚሉት እና ሌሎችም እንደሚገኙበት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡

የምክር ቤት አባላትም ረቂቅ አዋጁ መዘጋጀቱ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው ብቃትን መሰረት አደረጎ ለብሔር ብሔረሰቦች እኩል ዕድል ለመስጠት አስፈላጊ መሆኑን፣ አዋጁ የፌደራል ተቋማት ኢትዮጵያን እንዲመስሉ እንደሚያግዝ እና ሌሎች መታየት አለባቸው ያሏቸውን አስተያየቶች ሰጥተዋል፡፡ 

ረቂቅ አዋጁም አዋጅ ቁጥር 13/2016 ሆኖ በሙሉ ደምጽ ለሰው ሀብት ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡ 

3ኛ. የኢትዮጵያ ደረጃዎች ረቂቅ አዋጅ እና የሕጋዊ ስነ ልክ ረቂቅ አዋጅን የሚመለከቱ የውሳኔ ሀሳቦችን አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡ ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጆቹን መርምሮ አዋጅ ቁጥር 14/2016 እና15/2016 ሆነው በሙሉ ድምጽ ለንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርተዋል፡፡

4. የተጨማሪ እሴት ታክስ ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት አዋጁ ከወጣ ወዲህ የተደረጉ ለውጦቸን፣ የኤሌክትሮኒክስ ግብየትና በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸውን አዳዲስ እሳቤዎችን በሀገራቸን የህግ ማዕቀፎች በማካተት ታክሱ ለኢኮኖሚ ዕድገት የሚፈለገውን እገዛ እንዲያደርግ ማስቻል ተገቢ ሆኖ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡  

በተጨማሪም ግልጽነት በጎደላቸው አንቀጾች ምክንያት በታክስ ከፋዩና በታክስ ሰብሳቢው መካከል ሲፈጠር የነበረውን ያለመግባባት በማስወገድ ምቹ የሆነ የታክስ አስተዳደር እንዲኖር ያግዛልም ብለዋል፡፡ 

ምክር ቤቱ ረቂቀ አዋጁን መርምሮ ለፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አዋጅ ቁጥር 16/2016 አድርጎ በሙሉ ድምጽ መርቷል፡፡



Report Page