#Ethiopia
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአምነስቲ ሪፖርት የሰጠው ምላሽ ፦
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “አክሱም ከተማን በተመለከተ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣው ሪፖርት የተጠቀመው የመረጃ ምንጭ ፍትህን ለማስፈን ዓላማ አይጠቅምም” ሲል ገለጸ።
ተቋሙ ለመረጃ ምንጭነት የተጠቀመው በምስራቅ ሱዳን በስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ሰዎችን እንዲሁም ውስን የአክሱም ነዋሪዎችን በስልክ ቃለ መጠይቅ ማድረጉ የተሟላ ምስል ለመያዝ እንደማያስችል ገልጿል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣው ሪፖርት አስመልክቶ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ህወሃት በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ ኖቬምበር 4 ቀን 2020 ያደረሰው ጥቃት ተከትሎ በትግራይ ክልል የህግ ጥሰትና ስርዓት አልበኝነት ተፈጥሯል ብሏል።
በክልሉ ውስጥ የተከሰቱት ውስብስብ ችግሮች ህወሃት የፈጸመው የክህደት ተግባር ቀጥተኛ ውጤቶች እንደሆኑ ገልጾ፤ “በክልሉ ለተፈጠረው የህግ ጥሰት ኃላፊነቱን መውሰድ ያለበት አካል ከህወሓት ውጭ ማንም የለም” ሲል በመግለጫው አመልክቷል፡፡
የህወሃት የጥፋት ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ በግድያ እና በሌሎች የወንጀል ድርጊቶች መሰማራቱንም አስገንዝቧል።
“መንግሥት በትግራይ ክልል የወሰደው ሕግ የማስከበር ሥራዎች አጠቃላይ ዓላማ በክልሉ ውስጥ ሕግና ስርዓትን ለማስፈን እና ወንጀለኞች ለፍርድ ለማቅረብ ነው” ያለው መግለጫው፤ ወንጀኞችን ለህግ ለማቅረብ የተካሄደው ዘመቻ በሲቪሎች እና በሲቪል ተቋማት ላይ ጉዳት እንዳያስከትል ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረጉን አውስቷል።
በትግራይ ክልል በተለይም በአክሱም ከተማ ተፈጽመዋል የተባሉ ወሲባዊ ጥቃቶች እና ሌሎች ክስተቶችን ጨምሮ የደረሰው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እጅግ አሳሳቢ ጉዳዮች መሆናቸውን ያመለከተው መግለጫው፤ ለዚህም መንግስት አስፈላጊውን ምርመራ ለማድረግ እና አጥፊዎችን በህግ እንዲጠየቁ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑንም አመልክቷል።
“በማይካድራ ከተፈፀመው ጭፍጨፋ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ በአክሱም ከተማ ተፈጽሟል የተባለው የወንጀል ድርጊት በጥልቀት መመርመር ይኖርበታል” ብሏል ፡፡
የምርመራ ሥራውን ለማከናወን ከፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የተውጣጣ ቡድን ወደ ትግራይ ክልል መሄዱን አመልከቷል።
የእነዚህ ምርመራዎች ውጤት እና ቡድኑ በሚያቀርባቸው ምክረ ሃሳቦች መንግስት ወንጀለኞችን ለፍርድ ለማቅረብ እና በክልሉ ተከስተዋል የተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና ሁከቶችን በጥልቀት ለመፍታት ያስችላቸዋል ሲል ገልጿል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ በማይካድራ በንፁሃን ዜጎች ላይ በደረሰው ጭፍጨፋ በቀጥታ የተሳተፉ 36 ሰዎች በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መቅረባቸው ልብ ሊባል ይገባል ብሏል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በሰብዓዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ ምርመራ ሲያደርግ እና ሪፖርት ሲያቀርብ መቆየቱን ያመለከተው መግለጫው፤ “የኮሚሽኑ የምርመራ ውጤት በጊዜው ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይፋ ይደረጋል” ብሏል፡፡
በአክሱም ከተማ ተከስተው ከነበሩት ክስተቶች ጋር ተያይዞ በቀረቡ ክሶች ላይ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ዛሬ ሪፖርቱን ይፋ ማድረጉን ያመለከተው መግለጫ፤ ሪፖርቱ በጣም አሳሳቢ የሆኑ ጉዳዮችን መዳሰሱን ጠቅሶ፤ “ነገር ግን ሪፖርቱን በማዘጋጀት ሂደት የተጠቀሙበት ዘዴ በምስራቅ ሱዳን ከሚገኙ ስደተኞች በተሰበሰበ መረጃ እና በአክሱም ካሉ ግለሰቦች ጋር በስልክ ቃለ-መጠይቅ ላይ የተመሠረተ ነው” ብሏል፡፡
ለአብነትም በሪፖርቱ ከተጠቀሱት ምንጮች መካከል አንዱ አምነስቲ ሪፖርት ላይ እንደተጠቀሰው ቄስ ሳይሆን በቦስተን የሚኖር ግለሰብ መሆኑንም በመግለጫው አመልክቷል።
ስለሆነም በእንደዚህ አይነት ምንጮች ላይ የተመሠረተ ዘገባ ፍትህን ለማስፈን ዓላማ አይጠቅምም ብሏል።
ከዚህ ይልቅ በህወሃት እና ግብረ አበሮቹ የሚነዛውን የተሳሳተ መረጃ እና ፕሮፓጋንዳ የበለጠ የማጠናከር አደጋ እንዳለው አሳስቧል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ክልሉን በመጎብኘት እና የኢትዮጵያ መንግስት ባለሥልጣናትን በማነጋገር እውነቱን በማጋለጥ አስፈላጊውን የመስክ ሥራ ማከናወን ይገባው እንደነበርም በመግለጫው አመልክቷል።
[የወጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት]