Ethio130
Tikvah Ethiopiaኢትዮ ቴሌኮም በአዲሱ አመት በነበረው የደንበኞች ጨዋታ በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ ደንበኞቹን መሸለሙን አስታውቋል።
ተቋሙ ይህ የማስታወቂያ አማራጭ በእጅጉ አዳዲስ ደንበኞችን ለማግኘት ያገዘው እንደሆነ ገልጿል።
ኩባንያው ከተመሰረተ 130 ዓመታትን ማስቆጠሩን አስመልክቶ በተያዘው ዓመት ለስድስት ወር የሚቆይ "ኢትዮ 130" የተሰኘ ጨዋታ በተመሳሳይ ለደንበኞቹ እንደሚያቀርብ አስታውቋል።
በዚህ 6 ወር በሚቆየው ጨዋታ 6 የኤሌክትሪክ መኪኖች፤ 9 ባጃጆች፤ በርከት ያሉ የስልክ እና የፖኬጅ ሽልማቶች እንደሚኖሩት ነው የገለጸው።
ደንበኞች የአየር ሰዓት መግዛትን ጨምሮ ማንኛውም አገልግሎት ሲጠቀሙ በሚሰበስቡት Coin በቴሌብር ሱፐር አፕ ጌም መጫወት የሚያስችላቸው ሲሆን በዚሁ ጨዋታ ተሸላሚ የሚሆኑ ይሆናል።
ለመሆኑ ኩባንያው በ2017 በጀት ዓመቱ የገቢና የደንበኞችን ቁጥር ከማሳደግ አንጻር ምን አቅዷል?
- ኢትዮ ቴሌኮም፥ በ2016 በጀት ዓመት የተገኘውን 93 ቢሊየን ብር ገቢ በ74.7% በማሳደግ 163.7 ቢሊዮን ብር ለማድረስም በእቅድ አስቀምጧል፡፡
- በረሚታንስ (የሀዋላ) አገልግሎት በማሻሻልና አጋሮችን በማስፋት በበጀት ዓመቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት መጠን ወደ 282.85 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማሳደግ ታቅዷል፡፡
- የደንበኞችን ብዛትንም በ6% በመጨመር 83 ሚሊዮን ለማድረስ፤
- የሞባይል ደንበኞችን በ5.5% በመጨመር 79.7 ሚሊዮን ለማድረስ፤
- የሞባይል ዳታና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን በ16% በመጨመር 47.4 ሚሊዮን ለማድረስ፤
- የፊክስድ ብሮድባንድ ደንበኞችን በ25% በመጨመር 934 ሺህ በማድረስ አጠቃላይ የቴሌኮም ስርጸት መጠንን 73% ለማድረስ ታቅዷል፡፡
የቴሌኮም መሰረተ ልማትን ለማስፋፋት ምን እቅድ ተቀምጧል?
- 1,298 አዲስ የሞባይል ጣቢያዎችን ለመገንባት፤ 500 ተጨማሪ ከተሞችን የ4ጂ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግና 15 ተጨማሪ ከተሞችን የ5ጂ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ፤
- የዲጂታል ክፍተት (digital divide) ለማጥበብ በገጠር 331 የሩራል ኮኔክቲቪቲ ሶሉሽኖችን እንዲሁም 165 የሞባይል ኔትወርክ ጣቢያዎችን በመገንባት በድምሩ 496 ጣቢያዎች በማድረስ ለ1000 የገጠር ቀበሌዎች የኔትወርክ ሽፋን ለመስጠት፤
- 320 ሺህ አዳዲስ ኦ.ዲ.ኤን ለመገንባት፤ የፋይበር ኔትዎርክን ከ21.8 ሺህ ኪሜ ወደ 22 ሺህ 200 ኪ.ሜ ለማሳደግ እንዲሁም International Gateway (IGW) አቅምን በ25% ለማሳደግ ታቅዷል፡፡
በተጨማሪም፥ የAI ትግበራን ከማሳደግ አንፃር የተጀመሩትን አጠናክሮ መቀጠል እና በኔትዎርክ ፐርፎርማንስ፣ የቴሌኮም ማጭበርበርን መከላከልና መለየት እንዲሁም የደንበኞችን አገልግሎት ከማሻሻል አንፃር በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል ማቀዱን ገልጿል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም “ሊድ” የተሰኘ የሦስት ዓመት ስትራቴጂውን በ2015 በጀት ዓመት ማስተዋወቁ ይታወሳል። አዲሱ የ2017 በጀት አመት የስትራቴጂ ዘመኑ ሶስተኛው አመቱ ይሆናል።