#EZEMA
Voice of Americaየኢዜማ አባላቶቼ ተደበደቡብኝ እና ታሰሩብኝ ክስ እና የመንግስት ምላሽ ፦
ኢዜማ ከ11 በላይ የፓርቲው አባላት በደቡብ ክልል ኮንሶ ዞን የምርጫ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ እያሉ ድብደባ እንደተፈፀመባቸውና ለቀናት መታሰራቸው በኃላም ከእስር መፈታታቸውን ፓርቲው አስታውቋል።
ኢዜማ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ ፥ "ባለን መረጃ የካቲት 4 የመንግስት የድጋፍ ሰልፍ ይደረግ ነበር በኃላም ይህ ሰልፍ ተሰርዞ ምርጫ ቅስቀሳ እንዲደረግ በተያዘለት ጊዜ ሲደረግ ኢዜማ የምርጫ ቅስቀሳ ከማድረግ ተቆጥቦ ሰልፉ ከተካሄደ በኃላ ነው ወደ ቅስቀሳ የገቡት ከዚህ በኃላ ነው እስርና ድብደባው በአባላቶቻችን ላይ የደረሰው" ብለዋል።
የፓርቲው አባላት ሲታሰሩ የኢዜማን አርማ መያዛቸውን ፣ የፓርቲውን የምርጫ ምልክት ያለበት ቲሸርትም ለብሰው እንደነበር በኮንሶ ዞን የኢዜማ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ፍቅሩ ብርሃኑ ገልፀዋል።
ምክትል ሊቀመንበር ፥ የአካባቢው ፀጥታ አካላት የኢዜማን ቲሸርት የለበሱ አካላትን እየቀጠቀጡ እና እየደበደቡ ነበር ብለዋል። አንደኛው የኢዜማን ቲሸርት የለበሰ ሃኪም በሳንጃ ሁሉ ተወግቷል ሲሉ ገልፀዋል።
መንግስት በኢዜማ አባላት ላይ በማህበራዊ ኑሮ ላይ ሳይቀር ከፍተኛ ጫና እያዳደረ መሆኑንም አብራርተዋል። ሁኔታው አሳሳቢ መሆኑ አሳውቀዋል።
አቶ ፍቅሩ ፥ "እነሱ በየአዳራሹ ቅስቀሳ ያደርጋሉ፣ ቀበሌዎች ላይም በመንግስት ሃብት (ሞተር እና መኪና) እንደልባቸው እየተንቀሳቀሱ ቅስቀሳ ያደርጋሉ እኛ ግን በራሳችን ፅ/ቤታችን እንኳን እንዳንሰበሰብ ሊያደርጉን ነው" ብለዋል።
የታሰሩት የኢዜማ አባላት ማክሰኞ እለት ተፈተዋል።
የኮንሶ ዞን የሰላም እና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሃሰን ወላሎ፥ በኢዜማ ምርጫ ቅስቀሳ ምክንያት የታሰረ ሰው የለም ብለዋል።
ነገር ግን መንግስት ፈርሷል እያሉ ኢ-ህገመንግስታዊ ሰንደቅ ዓላማ በመያዝ በአደባባይ ሲያውጁ/ሁከት እና ብጥብጥ ለመቀስቀስ ሲጥሩ የነበሩ ግለሰቦች እንደነበሩ ገልፀዋል።
መንግስት የለም እያሉ መቀስቀስ ለአካባቢው ደህንነት እጅግ አደገኛ መሆኑን በማንሳት በአካባቢው ያለውን ውስብስ የፀጥታ ችግር ዳግም እንዲያገረሽ የሚያርግ ወንጀል ነው ግለሠቦቹ የፈፀሙት ብለዋል።
ኢዜማ እንደ የትኛውም ፓርቲ የራሱን ፕሮግራም እና ዓላማ በሰላም ወርዶ ማወያየት ይችላል ነገር ግን ሰዎች የሚለዩት በምርጫ ካርድ እንጂ በሁከት እና በብጥብጥ አይደለም ብለዋል።
ግለሰቦቹ ኢዜማ የሚወክሉ አይደሉም፤ በኢዜማ ካባ መንገድ ስለሌለባቸው ኢዜማን አይወክሉም ብለዋል።
የኢዜማው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ ግን የታሰሩት የኢዜማ አባላት ናቸው ያሉ ሲሆን ፓርቲያቸው የምርጫ ቅስቀሳ የሚያደርገው የአባላት እና የደጋፊዎች ስነምግባር ደንብ እና መመሪያ በመከተል ነው ብሏል።
[ጋዜጠኛ ዮናታን ዘብዲዮስ፣ የአሜሪካ ድምፅ ሬድዮ ጣቢያ]
Compiled By : Tikvah-Ethiopia