#ETH

#ETH


በፀጥታ ስጋት በርካታ ውድድሮች ተሰርዘዋል

የአዲስ አበባ ዋንጫ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ከመጀመሩ አስቀድሞ በተለያዩ ከተሞች የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች የሚካሄዱ መሆኑ ይታወቃል። ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆነው አንጋፋው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ መራዘሙን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከመንግስት አካላት ጋር ባደረገው ምክክር ዘንድሮ ለ14ኛ ጊዜ የሚካሄደውን ውድድር ለቀናት ለማራዘም ተችሏል። በመሆኑም ውድድሩ በመጪው ሐሙስ ጥቅምት 27 የሚጀመር ይሆናል፡፡

የደቡብ የሰላም ዋንጫ

ከዚህ ቀደም የደቡብ ካስትል ካፕ በመባል በደቡብ ክልል ይካሄድ የነበረው ውድድርም በተመሳሳይ የመካሄዱ ነገር አሳሳቢ መሆኑን ሶከር ኢትዮጵያ ዘግቧል። የደቡብ የሰላም ዋንጫ በሚል ስሙን የቀየረው ውድድር ከጥቅምት 20-ህዳር 01/2012 ዓ.ም ለማካሄድ የተወሰነ ሲሆን፤ የእጣ ማውጣት ስነስርዓቱም ከትናንት በስቲያ ነበር። ነገር ግን ለትናንት የተራዘመ ሲሆን፤ ምክንያቱም የክልሉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከጸጥታ አካላት ጋር ባደረገው ውይይት መግባባት ላይ አለመድረሱ ነው። ተሳታፊ ክለቦችም በዚህ ምክንያት ወደ የመጡበት መመለስ እንደጀመሩ ተጠቁሟል።

የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ

በመጪው እሁድ ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫም ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል። የ2011 ዓ.ም የፕሪምየር ሊግ አሸናፊ መቀሌ ሰባ እንደርታ እና የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊው ፋሲል ከነማ መካከል ጥቅምት 23/2012 ዓ.ም ሊካሄድ የነበረው ጨዋታ ለሌላ ጊዜ መሸጋገሩና ወደ ፊት የሚገለጽ መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

30 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር

ሌላው የተራዘመው ውድድር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሚያዘጋጀው የ30 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ነው። በቢሾፍቱ ከተማ ለስድስተኛ ጊዜ በመጪው እሁድ ጥቅምት 23/2012 ዓ.ም ለማካሄድ የታቀደው ውድድሩ ላልተወሰነ ጊዜ የተራዘመ ሲሆን፤ ውድድሩ የሚካሄድበትን ጊዜ ወደ ፊት እንደሚያሳውቅ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።

(ኢፕድ)

Report Page