#ETH

#ETH


የኢትዮጵያ መንግሥት የፀረ ሽብሩን ሕግን አላግባብ በመጠቀም ተተቸ። ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል መንግሥትን ይተቹ ነበር የተባሉ 22 ሰዎች ለፍርድ ሳይቀርቡ ለ4 ወራት ታስረው ትናንት መለቀቃቸውን አስመልክቶ ዛሬ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት አሁንም የፀረ-ሽብር ሕጉን አለአግባብ መጠቀሙን አላቆመም ሲል ወቅሷል። በድርጅቱ የአፍሪቃ ቀንድ ጉዳዮች ተመራማሪ አቶ ፍስሃ ተክሌ ዛሬ ለጀርመን ድምፅ ራድዮ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ትንናት የተለቀቁት 22 ሰዎች ከሰኔ 15ቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ግድያ በኋላ ከተያዙት ከ200 ይበልጣሉ ካሏቸው ሰዎች መካከል መሆናቸውን ገልጸው ለፍርድ ሳይቀርቡ ለአራት ወራት መታሰራቸዉ ኢፍትሀዊ እንደነበረ ተናግረዋል። አቶ ፍስሀ ያለማስረጃ ነው የታሰሩት ያሏቸው እነዚሁ ሰዎች በስተመጨረሻ በመታወቂያ እንደተለቀቁ ገልፀው ይህም የፀረ ሽብር አዋጁ ትችት የሚያቀርቡ ሰዎችን ለማጥቃት እየዋለ መሆኑን ያሳያል ብለዋል። ከዚህ ቀደም በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የዚህ አዋጅ ሰለባ መሆናቸውን ያስታወሱት አቶ ፍስሀ ሕጉ ይነሳል ተብሎ በሚጠበቅበት በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ በመደረግ ላይ መሆኑን ተችተዋል። ከተለቀቁት ውጭ በመጻፋቸው እና መጸሀፍ በማሳተማቸው አሁንም የታሰሩ ሰዎች እንዳሉም ተናግረዋል። ለዚህም «ሰገሌ ቄሮ» ከሚባለው «የሚዲያ ቡድን»የታሰሩትን ጋዜጠኞች በአብነት ጠቅሰዋል። የፀረ ሽብሩ ሕጉ በአስቸኳይ እንዲስተካከል የአምነስቲ ጥያቄ መሆኑን የተናገሩት አቶ ፍስሃ በዚህ ሕግ የታሰሩ ሰዎች ጉዳይ በግልጽ እና በማያሻሙ የሕግ ድንጋጌዎች እንጂ በዚህ ሕግ መታየት እንደሌለበት፣ ይህ ካልሆነም መለቀቅ እንዳለባቸው አስረድተዋል።

Via DW

Report Page