#ETH
ሩዋንዳ የመጀመሪያውን የኤሌክትሪክ መኪና በኪጋል ማሽከርከር ጀመረች
ሩዋንዳ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነች የቮልስዋገን ምርት ኢ-ጎልፍ የተሰኘች በኤሌክትሪክ የሚሰትራ መኪና ሥራ አስጀመረች።
የማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ የቮልስዋገን እና የሳይመንስ ሙከራ ፕሮጀክት አንድ አካል መሆኑንም ሲ ጂ ቲ ኤን በዘገባው አስነብቧል።
በሩዋንዳ ለሚንቀሳቀሱት አራት ኢ-ጎልፍ ኤሌክትሪክ መኪኖች የሙከራ ኘሮጀክትም የመጀመሪያ ምዕራፍ የሆነ አንድ የኃይል መሙያ ጣቢያ መኖሩም ተጠቅሷል።
ወደፊት 16 የሚሆኑ ተጨማሪ መኪኖች ገበያውን የሚቀላቀሉ መሆናቸውን የሀገሪቱ ባለስልጣናት ጠቁመው፤ ለዚሁ ፕሮጀክት የሚሆኑ 15 የሃይል መሙያ ጣቢያ መሰረት ልማቶች በኪጋሊ እንደሚኖርም ተናግረዋል፡፡
በሙከራ ኘሮጀክቱ ላይ የኤሌክትሪክ መኪኖችን አፈፃፀም፣ በተገልጋዮች ዘንድ ያለውን ቅቡልነትና ያሉ አዝማሚያዎችን፣ ለመኪኖቹ ተስማሚ ሁኔታዎችን እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ላይም መረጃ መሰብሰብ እና ትንታኔ የመስራት ሂደት እንደሚከናወንም ነው የተነገረው፡፡
ለጊዜውም ቢሆን መኪኖቹ ለሽያጭ በገበያ ላይ ስለማይገኙ ቮልስዋገን የሙከራ ፕሮጀክቱን በሩዋንዳ ለማስፋት ዕቅድ እንዳለውም መረጃው ጠቁሟል፡፡
በሩዋንዳ የቮልስዋገን ዋና ስራ አስፈፃሚ ሚኬላ ሩገዊዛነጎጋ እንዳሉት መኪኖቹ ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ናቸው።
ሃላፊዋ በማከልም የቮልስዋገን የሙከራ ፕሮጀክት በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ዓለም ዓቀፉን የአረንጓዴ መርሃ-ግብር አማራጭ ጥረትን የመደገፍ አንድ አካል ነው ብለዋል፡፡
ሃይል ከተሞላላቸው መኪኖቹ የሚሸፍኑት ርቀት እንደ መሬቱ አቀማመጥና የጭነት መጠን የሚወሰን ቢሆንም ሃይል ሙሉ በሙሉ ከተሞላላቸው እስከ 230 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚጓዙ መሆናቸውን ሲ ጂ ቲ ኤን በዘገባው አስፍሯል፡፡