#ETH

#ETH


ፖሊስ አዳማ ከተማ ወደ መረጋጋት መመለሷን ገልጿል!

በአዳማ ከተማ ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር በመቃለሉ አሁን ወደ መረጋጋት መመለሱን ፖሊስ አስታወቀ። የከተማው ፖሊስ መምሪያ የሰላም ማረጋገጥ የስራ ሂደት መሪ ምክትል ኮማንደር አለምሸት ኃይሉ እንዳሉት ባለፉት ሁለት ቀናት በከተማዋ መንገድ እንዘጋለን አትዘጉም በሚል በሁለት ቡድኖች መካከል በተነሳው ጸብ ግጭት ተፈጥሮ ነበር። በዚህም አንድ ሴትን ጨምሮ የ13 ሰዎች ሕይወት ማለፉን አስታውቀዋል።(ቢቢሲ የሆስፒታል ምንጮችን ጠቅሶ ትላንት እንደዘገበው የሟቾች ቁጥር 16 ይደርሳል)

ከ50 በላይ ሰዎች ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በአዳማ ሪፈራል ሆስፒታልና ሜዲካል ኮሌጅ የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ መደረጉን ገልፀዋል። እንዲሁም በተለያዩ ንብረቶች ላይ ጉዳት ደርሷል። ጉዳት ከደረሰባቸው ንብረቶች መካከል በከተማዋ አፍሪካ ዱቄት ፋብርካ ንብረት የሆኑ 13 ተሽከርካሪዎች ፣ አንድ መኖሪያ ቤት እና ሰባት ባጃጆች ይገኙበታል። የጸጥታ ችግሩን ለማርገብ የፀጥታው አካላት ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ባደረጉት ጥረት ከተማዋ አሁን ወደ መረጋጋት መመለሷን ምክትል ኮማንደር አለምሸት ተናግረዋል።

በተለይ ወጣቱ ለጥፋት መጠቀሚያ መሆን እንደሌለበት ከደረሰው ጉዳት መማር እንደሚገባ አሳስበዋል። የተከሰተው የጸጥታ ችግር ለማጣራት አንድ ቡድን ተዋቅሮ ጥናት መጀመሩንና እንደተጠናቀቀም በህግ የሚጠየቁ አካላት ተለይተው ለፍርድ እንደሚቀርቡ አስታውቀቃል።

“በአሁኑ ወቅት የከተማው ስላም ለማሰጠበቅ ፖሊስ ህዝቡን በማሳተፍ እየሰራ ነው” ያሉት ምክትል ኮማንደሩ በተለይ ሁሉንም ችግር በፀጥታ አካላት ብቻ መፈታት ስለማይቻል የኃይማኖት አባቶች ፣የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

Via ENA

@tikvahethiopia


Report Page