#ETH

#ETH


ኤፍራታና ግድም አካባቢ ያለውን የፀጥታ ችግር መንግሥት በአስቸኳይ ሊቆጣጠረው ይገባል ሲሉ ነዋሪዎች ጠየቁ። በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳ አጣዬ አካባቢ ከትናንት ጀምሮ የፀጥታ ችግር መከሰቱን ይታወቃል፡፡ የፀጥታ መደፍረሱ ትናንት በቁጥጥር ሥር የዋለና ዛሬ ረፋድም አንጻራዊ መረጋጋት እንደነበረ የተገለጸ ቢሆንም እንደገና የተኩስ ልውውጥ መጀመሩን ነዋሪዎች ለአብመድ ተናግረዋል።

‹‹ከቤታችን አልወጣንም፤ ከባድ ተኩስ እየተሰማ ነው፤ ማን እንደሚተኩስ አናውቅም፤ መከላከያ፣ ፖሊስ፣ ልዩ ኃይል አሉ፤ የታጠቁ ኃይሎችም በተራሮች አካባቢ አሉ፤ ከባድ መሣሪያ ጭምር እየተተኮሰ ነው›› ብለዋል አንድ የአጣዬ ከተማ ነዋሪ ለአብመድ ሲናገሩ፡፡

ሱኒ መውጫ እና አቡበከር ተራራ አካባቢ እየተተኮሰ መሆኑን ያስታወቁት ነዋሪው ከትናንት ጀምሮ ከባድ ስጋት ውስጥ እንደሆኑ አመልክተዋል፡፡ ነዋሪው እንደተናገሩት ትናንት ጠዋት አንድ የታጠቀ ግለሰብ በኮማንድ ፖስት በሚተዳደርና ትጥቅ ይዞ መንቀሳቀስ በማይቻልበት አካባቢ ታጥቆ ሲንቀሳቀስ በፀጥታ አካላት እንዲቆም ሲነገረው አሻፈረኝ ብሎ ተኩስ በመክፈቱና በአጸፋ ተኩስ ሕይወቱ በማለፉ ነው የፀጥታ መደፍረሱ የተከሰተው፡፡

አንድ ሌላ የአጣዬ ነዋሪ እንደተናገሩት ደግሞ የፀጥታ መደፍረሱ ከአጣዬ ውጭ ወዳሉ ቀበሌዎችም እየተዛመተ ነው፡፡ ነዋሪው እንደተናገሩት አላላ እና ይምሎ ቀበሌዎች ዛሬ ተደጋጋሚና የከባድ መሣሪያ ጭምር ተኩስ እየተሰማባቸው ነው፡፡ "መንግሥት ሁኔታውን በአስቸኳይ ሊቆጣጠረው ይገባል" ሲሉም ነዋሪው አሳስበዋል፡፡

የአጣዬ ከተማ አስተዳድር ከንቲባ ጌታቸው በቀለ ሁለተኛው አስተያዬት ሰጪ የተናገሩትን ሐሳብ አጠናክረዋል፡፡ "ከተማው ዙሪያ እና አላላና ይምሎ በሚባሉት ቀበሌዎች የከባድ መሣሪያ ጭምር ተኩስ አለ፤ ሁለት ሠላማዊ ሰዎች ይምሎ ቀበሌ 'ሞሉ በር' አካባቢ ቆስለው ሆስፒታል መግባታቸውንም ሰምቻለሁ" ብለዋል ከንቲባ ጌታቸው፡፡

ከባድ መሣሪያም እየተተኮሰ እንደሆነ ያስረዱት ከንቲባ ጌታቸው "ሦስት ቦንብ፣ አንድ ክላሽ ከአራት ካዝና ጋር ታጥቆ ባልተፈቀደ አካባቢ ሲንቀሳቀስ የነበረ ግለሰብ 'ቁም!' ሲባል አልቆምም ብሎ በተከፈተ የተኩስ ልውውጥ ህይዎቱ ካለፈ በኋላ ነው ትናንት የፀጥታ መደፍረስ ያጋጠመው" ብለዋል፡፡ ግለሰቡ ታጥቆ ይንቀሳቀስ የነበረው 01 ቀበሌ አካባቢ እንደነበርም አስታውቀዋል፡፡

ምንጭ፦ አብመድ

Report Page