#ETH

#ETH


ኤጀንሲውና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎቹ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ታገዱ!

ኤቢኤች ሰርቪስስ ኃ/የተ/የግል ማህበር የተባለው የማማከርና የምርምር ተቋም በከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ እና በኤጀንሲው አምስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ የብር 174.6 ሚሊዮን ካሣ ይከፍሉት ዘንድ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 241863 ክስ ማቅረቡ የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ለሳምንታት የዜና ሽፋን የሰጡት ዘገባ መሆኑ ይታወሳል፡፡ 

ኤቢኤች ከክሱ በኋላ ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባቀረበው የዕግድ አቤቱታ ተከሳሾቹ የስም ማጥፋት ተግባራቸውን እንዲያቆሙ የዕግድ ትዕዛዝ ይሰጥለት ዘንድ የጠየቀ ሲሆን ፍ/ቤቱም በአቤቱታው ላይ ተከሳሾቹ አስተያየታቸውን እንዲሰጡበት በማድረግ ክርክሩን ከሰማ በኋላ መስከረም 2 ቀን 2012 ዓ.ም የዕግድ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ፍ/ቤቱ በሰጠው የዕግድ ትዕዛዝ እንደ ኤቢኤች ያሉ የግል ድርጅቶች ህግና ሥርዓትን ተከትለው ከማንኛውም ተቋም ጋር ውል ተዋውለው የመስራትና የተቋቋሙበትን አላማ የማሳካት መብት እንዳላቸውና ኤቢኤችም ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር ውል አድርጎ በመስራት ላይ የሚገኘው ዩኒቨርሲቲው በአዲስ አበባ ለከፈተው ካምፓስ እንደ የመማሪያ ክፍሎች፣ የቤተ መፃህፍት፣ የካፌና የመሳሰሉትን አገልግሎቶች የማቅረብ ሥራ በመሆኑ ኤጀንሲው ኤቢኤችን መቆጣጠርም ሆነ ስሙን ያለአግባብ ማንሳትና ማብጠልጠል እንደማይችል ገልጿል፡፡

በተጨማሪም ተከሳሾቹ በልዩ ልዩ የመገናኛ ብዙኃን ቀርበው የኤቢኤችን መልካም ስም በሚጎዳ አኳኋን ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር አጣምረው ሲያነሱ እንደነበረ ፍ/ቤቱ የቀረበለትን የቪዲዮ ማስረጃ በመመልከት ማረጋገጡን ገልፆ ይኸው ድርጊታቸው የኤቢኤችን ገፅታና መልካም ስም በማበላሸት ድርጅቱ ወደፊት ከተለያዩ አገር በቀልና የውጭ ድርጅቶች ጋር ለሚያከናነው ሥራ እንቅፋት እንደሚሆንና ጉዳት እንደሚያስከትል ገልፆ ተከሳሾቹ ሲፈፅሙት የነበረውን የስም ማጥፋት ተግባር ከመስከረም 2 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ እንዳይፈፅሙ አዟል፡፡

ፍ/ቤቱ በፍትሃብሔር ሥነ ሥርዓት ህጉ አንቀጽ 155 መሠረት የዕግድ ትዕዛዙን የሰጠው ኤቢኤች በወንጀል ተከሶ ጥፋተኛ መሆኑ ባልተረጋገጠበትና ኤጀንሲውም ሆነ የኤጀንሲው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የሆኑት ቀሪዎቹ ተከሳሾች ኤቢኤች ህገ ወጥ ሥራ ሲሰራ እንደነበረ ተገቢውን ጥናት አድርገው ባላረጋገጡበት ሁኔታ በመገናኛ ብዙኃን የድርጅቱን ስም የሚጎዳ መግለጫ መስጠታቸው ከኤጀንሲውም ሆነ ከቀሪዎቹ ተከሳሾች የማይጠበቅ መሆኑን ጭምር በመግለፅና የተከሳሾቹን ድርጊት በመተቸት ነው፡፡

በተጨማሪም ፍ/ቤቱ 1ኛ ተከሳሽ የሆነው የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ እና ጅማ ዩኒቨርሲቲ በአዲስ አበባ ከሚሰጠው ትምህርት ጋር በተያያዘ ያልተግባቡበት ሁኔታ መኖሩን በትዕዛዙ የሐተታ ክፍል ገልፆ ተከሳሾቹ በዚሁ ካምፓስ በሚሰጠው ትምህርት ላይ ችግር ከፈጠሩ ዩኒቨርሲቲው ዕግድ መጠየቅ እንደሚችል ጠቁሟል፡፡ 

ተከሳሾቹ በቀረበባቸው ክስ ላይ መልስ እንዲሰጡ ለመስከረም 26 ቀን 2011 ዓ.ም እና ክርክሩን ለመስማት ለጥቅምት 24 ቀን 2011 ዓ.ም የተያዘው ቀጠሮ እንዳልተለወጠም ፍ/ቤቱ አክሎ ገልጿል፡፡

Report Page