#ETH
የታላቁ ህዳሴ ግድብ የግንባታ ወጪን ለመሸፈን ታስቦ ለህዝብ ሲቀርብ የነበረው የቦንድ ሽያጭ በ2010 ከነበረበት 2.14 ቢሊዮን ብር ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በማሽቆልቆል በተገባደደው የ2011 በጀት ዓመት 970 ሚሊዮን ብር ብቻ ሆኖ ተመዘገበ።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ብሔራዊ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት የሚዲያ ግንኙነት ኀላፊ ኃይሉ አብርሃም ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት፣ በግድቡ መዘግየት እና ተያያዥ ችግሮች ምክንያት ህብረተሰቡ አመኔታ ማጣቱን እንደ ምክንያት ገልፀው ይህም የቦንዱን ሽያጭ አቀዛቅዞታል ብለዋል። ‹‹የህዳሴው ግድብ ግንባታ ቆመ የሚል አመለካከት በመፈጠሩ ምክንያት ሀብት ከማሰባሰብ ይልቅ ማህበረሰቡ ጋር ያለውን የመረጃ ብዥታ ማጥራት ላይ ትኩረት አድርገን ስንሠራ ቆይተናል›› ሲሉም ተናግረዋል።
በህዝቡ ውስጥ የተፈጠረውን መቀዛቀዝ ወደነበረበት ለመመለስ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች፣ የስዕል እና ቅርጻ ቅርጽ አውደ ርዕዮች፣ የሥነ ጥበብ ምሽቶች፤ ስፖርታዊ ውድድሮች እና ለሚዲያ አካላት የመስክ ጉብኝቶችን በማዘጋጀት ገንዘብ ከማሰባሰቡ ይልቅ በግድቡ ዙሪያ ብሔራዊ መግባባትን ለማምጣት እና ግድቡ ስለሚገኝበት ሁኔታ ግንዛቤ ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑንም ኃይሉ አብርሃም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በ2011 ከ1900 በላይ ኢትዮጵያውያን እና የውጭ ሀገራት ጎብኝዎች የግድቡን ግንባታ ሂደት የጎበኙ ሲሆን በ2012 ብሔራዊ መግባባቱን የሚያጎሉ እንደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሩጫ፤ የቦንድ ሳምንት እና ሌሎች የገቢ ማስገኛ መንገዶችን በመጠቀም ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብስብ ታቅዷል።
በግድቡ ስምንት የግንባታ ዓመታት ውስጥ ከ 98 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገ ሲሆን ከህዝብ ተሳትፎ 12 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሏል። 80 ከመቶ የሚሆነው የግድቡ የግንባታ ወጪ በኢትዮጵያ መንግሥት የሚሸፈን ነው። ኃይሉ አብርሃም ህብረተሰቡ ላለፉት ዓመታት ባለው አቅም ሲሳተፍ መቆየቱ የሚበረታታ መሆኑን ገልፀው፣ ህዝቡ የግድቡ ባለቤት መሆኑን ማረጋገጥ ቅድሚያ የሚሰጠው በመሆኑ ገቢው ከባለፈው ዓመት ቅናሽ ማሳየቱ በግድቡ የገቢ አቅም ላይ የሚያደረሰው ጉልህ ተፅእኖ አይኖርም ብለዋል።
በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለተከታታይ ዓመታት የአንድ ወር ደሞዛቸውን በመስጠት ቦንድ የገዙ ሠራተኞች የቦንድ ክፍያ በጊዜው ካለመከፈሉ በተጨማሪ መሥሪያ ቤቶች ሠራተኞች የገዙትን የቦንድ ኩፖን በጊዜው ተከታትለው ለሠራተኞች ባለማስረከባቸው ምክንያት በርካታ ቅሬታዎች የሚነሱ ሲሆን ለተሰበሰበው ገንዘብ ማሽቆልቆል በምክንያት እንደሚነሳ ችግሩንም ለመቅረፍ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ፋይናንስ አካላት እና መሥሪያ ቤቶች ጋር በቦንድ አሻሻጥ እና አመላለስ ዙሪያ ጽሕፈት ቤቱ ምክክር እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።
በ2012 በጀት ዓመት ከገንዘብ ማሰባሰቡ በተጨማሪ አርሶ አደሮችን እና አርብቶ አደሮችን ከብቶቻቸውን እና እህል በመስጠት እንዲሳተፉ ለማድረግ እየተሠራ ሲሆን በተጨማሪም የተፋሰስ ልማቶችን የተሻለ ለማድረግ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሮች ላይ ማህበረሰቡን ለማሳተፍ እንደሚሠራም ተገልጿል።
መንግሥት በግድቡ ግንባታ ላይ የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ባደረገው እንቅስቃሴ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከነበረበት መቀዛቀዝ በመውጣት በአሁን ወቅት ከ68 በመቶ ግንባታ አፈፃፀም ላይ እንደሚገኝ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ብሔራዊ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት መግለጫ ያሳያል።
ግድቡ በፈረንጆቹ 2024 እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቅ ሲሆን ግንባታውን በታሰበው ጊዜ ለማጠናቀቅ የእስካሁኑን ጨምሮ ከ 130 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስወጣ ይጠበቃል።
ADDISMALEDA