#ETH
ዛሬ መስከረም 4 ቀን 2012 ጠ/ሚር ዐቢይ አሕመድ ከምክትል ጠ/ሚር ደመቀ መኮንንና ከመከላከያ ሚንስትር ለማ መገርሳ ጋር በመሆን በከፋ ዞን ቦንጋ በመገኘት ከህዝብ ተወካዮች ጋር ውይይት አካሂደዋል።
ከህዝባዊ ውይይቱ በፊት በቦንጋ ስታዲየም ባደረጉት ንግግር የከፋ ህዝብ ለዘመናት ጠብቆ ያቆየውን ከተፈጥሮ ጋር ተባብሮ ተከባብሮ የመኖር፣ ራስን የማስተዳደር፣ ተቋማት ግንባታ፣ የሥራ ክፍፍል ከፍተኛ ልምምድ እንዳለው ያስታወሱት ጠ/ሚሩ በንግግር በውይይትና በምክክር ሀገር ማልማትን ለሌሎችም ልምዶችን ለማካፈል መነሳት እንዳለባቸው አንስተዋል::
አዲሱ ዓመት 2012 የፍቅር፣ የሰላም፣ የደስታና የመደመር እንዲሆን ተመኝተዋል:: በንግግራቸው ማብቂያም ከዞኑ እና ከሀገር ሽማግሌዎች የፈረስ፣ ጋሻና ጦር ስጦታ ተበርክቶላቸዋል::
ጠ/ሚር ዐቢይ አሕመድ ከከፋ ህዝብ ተወካዮች ጋር በቦንጋ ከተማ ባደረጉት ውይይት ተወካዮቹ ከክልል አወቃቀር፣ የመንገድ፣ ውሀ፣ ጤናና ቤተ መጽሀፍት የመሳሰሉ የመሰረተ ልማት፣ የሀብት አጠቃቀም፣ የሥራ አጥነት፣ የኢንቨስትመንትና ሌሎችም ጥያቄዎች አንስተዋል::
ጠ/ሚር ዐቢይ አሕመድ የተነሱ ጥያቄዎችን በምክክር አቅም በፈቀደ መጠን ለመመለስ ቃል ገብተዋል:: አቅም ያላቸው አልሚ ባለሀብቶች እንዲመጡ መሥራትና በመተባበርና በስልጣኔ የመንቀሳቀስን አስፈላጊነት በማንሳት ተፈጥሮንና ከባቢን ለመንከባከብ ያሳዩትን ቆራጥነት አድንቀዋል::
የክልል አደረጃጀት ለውጥ የሁሉም ጥያቄ መልስ አይሆንም ያሉት ጠ/ሚሩ ተያያዥነት ያላቸው አማራጭ አሰራሮች ማየት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል::
ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማጠቃለያቸው በትብብርና በመደመር በመሥራት ኢትዮጵያን ለማበልጸግ ጊዜው አሁን ነው ብለዋል::
Via #EPA