#ETH

#ETH


የመስከረም አራት ሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪዎች የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔን ለመጠበቅ ተስማሙ!

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ እየደረሱ ያሉትን ችግሮችን በተመለከተ ለመጪው መስከረም አራት ሰላማዊ ሰልፍ የጠሩ መንፈሳዊ ማሕበራት ሕብረት የቤተክርስቲያኒቱን ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔን ለመጠበቅ ተስማሙ። የማሕበራቱ ተወካዮች በትናንትናው ዕለት ከአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ጋር ተነጋግረዋል።

በምክትል ከንቲባው ጽሕፈት ቤት ትናንት ከሰዓት በተደረገው ውይይት ላይ ከስምንት ማሕበራት የተውጣጡ 15 ተወካዮች መገኘታቸውን አንድ የውይይቱ ተሳታፊ ተናግረዋል። በውይይቱ ላይ ወቅታዊ የሆኑት «የአሮሚያ ቤተክህነት የማቋቋም ጥያቄ» እና «በአጠቃላይ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርቲያን ላይ እየደረሱ ያሉ መከራዎች» መነሳታቸውን በቤተክርስቲያኒቱ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ማሕበር ተወካይ አቶ ግርማ ተክሉ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ በመጪው መስከረም አራት ለማካሄድ ስለ ታቀደው ሰላማዊ ሰልፍም መወያያታቸውን እና ምክትል ከንቲባው ምላሽ መስጠታቸውን ገልጸዋል።

«በእርሳቸው በኩል የቀረበው ሀሳብ ምንድነው? ʻሰላማዊ ሰልፉን ዛሬ አድርጉም፤ አታድርጉም ብዬ አልፈቅድላችሁም፤ አልከለክላችሁምም። ነገር ግን ቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ ነው። አምናለሁ በቅዱስ ሲኖዶስ መልካም ውሳኔ ይወሰናል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ ለቀረቡት ጥያቄዎች፣ ላሉት ችግሮች ሁሉ መፍትሄ ይገኛል ብዬ አስባለሁ። ስለዚህ ከዚያ በኋላ ተገናኝተን የምንነጋርበት ቢሆን መልካም ነው» እንዳሏቿው አቶ ግርማ አስረድተዋል።

አቶ ግርማ አክለውም «[ምክትል ከንቲባው] ʻየተጠየቁ ጥቄያዎች ምላሽ ካገኙ ሰልፍ መውጣቱ ጥቅም አለው፤ ጥቅም የለውም ብለን በጋራ ቁጭ ብለን ተመልሰን፤ ተወያይተን የምንወስነው ነው የሚል አዎንታዊ የሆነ ሀሳብ ነው ያቀረቡት። በዚህም ሁላችንም ተግባብተን ነው የወጣነው» ብለዋል። ሰልፉን የጠሩት ማሕበራት ቀጣይ አካሄዳቸውን ከመወሰናቸው በፊት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የሚያሳልፈው ውሳኔን ለመጠበቅ መስማማታቸውንም የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ተወካዩ አስረድተዋል።

«የቤተክርስቲያኒቱ የበላይ አካል የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ ባሉት ጉዳዮች ላይ ዛሬ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ ትናንትና ደግሞ ከኦሮሚያ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ጋር ተወያይቷል» ያሉት አቶ ግርማ በውይይቶቹ ላይ የመፍትሄ ሀሳብ የሚቀመጥ ከሆነ ጥያቄያቸውን ዳግም እንደሚያጤኑት ተናግረዋል። «በሰላማዊ ሰልፍ ሊጠየቅ የታሰበው በቅዱስ ሲኖዶስ በኩል ለሚገባው አካል ቀርቦ ከተመለሰ፤ ቀጣዩ ነገር ʻሰላማዊ ሰልፍ ማድረጉ አግባብ ነው፤ አግባብ አይደለምʼ የሚለውን መፈተሽ ነው ማለት ነው» ብለዋል የማሕበሩ ተወካይ።

Via #DW

Report Page