#ETH

#ETH


በደቡብ ብሔር፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ዋና ከተማ የሆነችው የሀዋሳ ከተማ አሁን አስተማማኝ ሰላም ላይ የምትገኝ በመሆኑ ኮማንድ ፖስቱ ቢነሳም ችግር እንደማይከሰት ተገለጸ።

የሀዋሳ ከተማ ኮማንድ ፖስት ኃላፊ ኮሎኔል ተክለብርሃን ገብረመድህን እንደገለጹት፤ በደቡብ ብሔር፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አንዳንድ ከተሞች ተከስቶ በነበረው የጸጥታ አለመረጋጋት ምክንያት በሀዋሳ ከተማ የተጣለው ኮማንድ ፖስት ቢነሳም ችግር አይፈጠርም። ከተማዋ አሁን ላይ በህብረተሰቡ ከፍተኛ እገዛ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴዋ ሙሉ ለሙሉ ተመልሳለች።

እንደ ኮሎኔል ተክለብርሃን ገለጻ፤ ሀዋሳ ከተማ የተረጋጋችው በኮማንድ ፖስቱ ኃይል ሳይሆን በነዋሪው ህብረተሰብ ከፍተኛ ጥረት ነው። ኮማንድ ፖስቱ ከህብረተሰቡ ጎን በመቆም በድጋፍ ሰጪነት እየሰራ ይገኛል። ህብረተሰቡ ግን ችግር በተመለከቱባቸው አካባቢዎችና ግለሰቦችን በእራሱ እየያዘ ለህግ አካላት በማጋለጥ በየጊዜው ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። በአሁኑ ወቅትም ከተማዋ የተረጋጋች በመሆኗ የመዝናኛ ቦታዎች 24 ሰዓት አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው።

ከተማ ላይ ሠላም እንዳይመጣ ህገወጥ ተግባር ሲፈጽሙ ተገኝተዋል ተብለው የተጠረጠሩ 68 ሰዎች በኮማንድ ፖስቱ ሥር መያዛቸውን የገለጹት ኃላፊው፤ ይሁንና ከተያዙት ሰዎች መካከል የመንግስት ኃላፊዎች እንደማይገኙበት ተናግረዋል። በቀጣይም እጃቸው በጉዳዩ ውስጥ ያለባቸውን ሰዎች ለህግ ለማቅረብ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑና ሀዋሳ በአሁኑ ሰዓት ማንኛውም ግለሰብ በነጻነት የሚንቀሳቀስባት ከተማ በመሆኗ ምንም የሚያሰጋ ጉዳይ እንደሌለ ተናግረዋል።

#EPA

Report Page