#ETH

#ETH


እነ አቶ በረከት ስምኦን በጤና መታወክ ምክንያት እየተሰቃየን በመሆኑ የክስ መዝገባችን ተመርምሮ አስቸኳይ ፍትህ ሊሰጠን ይገባል ሲሉ ለችሎት ጥያቄ አቀረቡ ። 

በጥረት ኮርፖሬት በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት አቶ በረከት ስምኦን፣ አቶ ታደሰ ካሳና አቶ ዳንኤል ግዛው ዛሬ በአማራ ክልል ጠቅላይ ፈርድ ቤት ቀርበዋል።

በተከሰሱበት የሙስና ወንጀል መዝገቡ ተመርምሮ አስቸኳይ ውሳኔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

በተለይም አቶ በረከት እንዳሉት ቀደም ሲል የጀመራቸው የጤና መታወክ እየተባባሰ በመምጣቱ ጊዜ ሳይራዘም ፍትህ እንዲሰጣቸው አመልክተዋል።

አቶ ታደሰ ካሳ በበኩላቸው የክስ መስገቡ ሆነ ተብሎ እንዲራዘም እየተደረገ በመሆኑ ከተያዝንበት ጊዜ መርዘምና ከጤና ችግራችን አንፃር ታይቶ በአጭር ቀጠሮ እልባት እንዲሰጠን ሲሉ ጠይቀዋል።

የተከሳሾቹ ጠበቃ በበኩላቸው አለአግባብ የሆኑ ተደጋጋሚ የጊዜ ቀጠሮ በመስጠት ደንበኞቼ እየተጉላሉ ነው ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል።

በመሆኑም ጉዳዩን በመመልከት አጭር ቀጠሮ በመስጠት ለደንበኞቼ ፈጣን ፍትህ ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል ።

ችሎቱ በበኩሉ እንኳን የጤና ችግር ያለባቸውን ተከሳሾች ሌሎችንም ቢሆን በህገ መንግስቱ መሰረት በተቻለ መጠን አስቸኳይ ፍትህ የማግኘት መብት የተጠበቀ ነው ብሏል ።

በመሆኑም ከጉዳዩ ውስብስብነት አንፃር አጫጭር ቀጠሮዎችን በመስጠት ማስረጃዎችን በማሰባሰብና በመመርመር እልባት ለመስጠት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፇል ።

አሁንም ለፍርድ ቤቱ የሚቀርበውን ብዛት ያለው መዝገብ ከማየት ጎን ለጎን ለዚህ ጉዳይ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት ጥረት ይደረጋል ብሏል።

በዛሬው እለትም የዳሽን ቢራ ፋብሪካና የባህር ዳር ሞተር መገጣጠሚያን በተመለከተ ተከሳሾች ከመዝገቡ ጋር እንዲያያዝላቸው ያቀረቡትን ተጨማሪ ማስረጃ ለችሎቱ አስረክበዋል።

የቀረበውን ተጨማሪ ማስረጃ አቃቢ ህግ ተመልክቶ ለመጋቢት 4ቀን 2012 ዓም አስተያየት እንዲሰጥ ችሎቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት ተከሳሾቹ ከሁለት ቢሊዮን ብር ብር በላይ አባክናችኋል በሚል የተለያዩ ክሶች የቀረበባቸው መሆኑ ይታወቃል።

ምንጭ፦ ኢዜአ

Report Page