#ET

#ET


የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ ከኢዴፓ አፈንግጠው በወጡ አራት አባላት የተሰጠውን የፓርቲው ንብረቶች ያለምንም ህጋዊ መሰረት እየተጠቀመ ስለሆነ ሊመልስልን ይገባል ሲል ኢዴፓ ጥሪ አቅርቧል፤ ኢዜማ በበኩሉ በህገወጥ መንገድ የያዝሁት ምንም ንብረት የለም ብሏል፡፡

ከኢዴፓ አፈንግጠው የወጡ አራት ግለሰቦች በምርጫ ቦርድ ፍፁም ህገወጥ የሆነ ትብብር የፓርቲውን ፅህፈት ቤቶች፣ በባንክ የተቀመጠ ገንዘብ፣ መዛግብትና ማህተም ያለአግባብ በህገወጥ መንገድ እንዲረከቡ ተደርጓል ያለው ኢዴፓ ግለሰቦቹ ኢዴፓ ከግንቦት 7 ጋር እንዲዋሀድ የኢዴፓ ጠቅላላ ጉባኤ ተሰብስቦ እንደወሰነ አድርገው የሀሰት መረጃ በማቅረብ ንብረቶቹን በፓርቲዎች ውህደት ሳይሆን በግለሰቦች ስብስብ ለተቋቋመው ኢዜማ ማስረከባቸውን የኢዴፓ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከትናንት በስቲያ በሰጠው መግለጫ ጠቅሷል፡፡

ኢዜማም ያለምንም ህጋዊ መሰረት እነዚህን የኢዴፓ ንብረቶች እየተጠቀመባቸው እንደሚገኝ የጠቀሰው ማእከላዊ ኮሚቴው በዚህ የተነሳ የእለት ከእለት ስራዎችን በአግባቡ ለማከናወን መቸገሩን ገልፆ ኢዜማ ግለሰቦቹ የፈፀሙትን የማጭበርበር ወንጀል ተረድቶ ንብረቶችን እንዲመልስ ጠይቋል፡፡

‘‘ኢዴፓ ከመጀመሪውም ቢሆን አልከሰመም’’ ያለው ማእከላዊ ኮሚቴው ፓርቲው ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ምንም አይነት እገዳ እንደሌለበትና ስራውን መቀጠል እንደሚችል ከተገለፀለት በኋላ ልዩና አስቸኳይ ስብሰባ አካሂዶ የሌላ ፓርቲ አባላት ሆነው በተገኙ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ምትክ አቶ አዳነ ታደሰን የፓርቲው ፕሬዚዳንት እና ወ/ሪት ፅጌ ጥበቡን ደግሞ ም/ፕሬዚዳንት አድርጎ መሾሙን አስታውቋል፡፡

የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ ፓርቲያቸው በህገወጥ መንገድ የያዘው ምንም ንብረት አለመኖሩን ገልፀው የኢዴፓን ቢሮ እየተጠቀመ ያለው ግን የኢዴፓ ጠቅላላ ጉባኤ ፓርቲውን ለማክሰም የያዘው ቃለጉባኤ ላይ ንብረቶቹን ለማን እንደሚያስረክብ ሲገልፅ አዲስ የሚመሰረተው ፓርቲ እንዲገለገልበት መወሰኑን ተከትሎ እንደሆነ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ገልፀዋል፡፡

በዚህ መሰረት የኢዴፓ አራት አባላት ኢዜማን ሲቀላቀሉ በቃለጉባኤው መሰረት ኢዜማ የኢዴፓን ቢሮ መጠቀሙ ህገወጥ ሊያስብለው የሚችል ምንም መሰረት የለም ያሉት አቶ ናትናኤል የኢዴፓን መክሰም በተመለከተ ኢዜማ የሚያውቀው ፓርቲው መክሰሙን ሲሆን የኢዴፓ ጠቅላላ ጉባኤ ለምርጫ ቦርድ ያቀረበውን ጥያቄ ምላሽ እየጠበቁ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

#EPA

Report Page