ESR & CRP
Crohn's & Colitis Ethiopiaየሰውነት መቆጣት ምንድን ነው?
የሰውነት መቆጣት፣ ሰውነታችን ከተለያዩ ህመምን ሊያስከትሉበት ከሚችሉ ነገሮች ራሱን የሚከላከልበት አስፈላጊ የሆነ ሂደት ነው፡፡ በዚህ ሂደት ሰውነታችን የራሱን የበሽታ የመከላከል ስርዓት በመጠቀም ከተለያዩ ጉዳቶች በራሱ ያገግማል፡፡ ለተወሰነ ጊዜ የሚቆይ የሰውነት መቆጣት ጤነኛና አስፈላጊ የሰውነት ሂደት ሲሆን ይህ ሂደት ሲዛባና ለረዥም ጊዜ ሲቆይ ግን ለሰውነት አደገኛ የሆነ ስር የሰደደን የሰውነት መቆጣት ሊያስከትል ይችላል፡፡
ESR እና CRP ምንድን ናቸው?
Erythrocyte sedimentation rate (ESR) በአማርኛው አቻ ትርጉም የቀይ ህዋሳተ ደም ዝቅጠተ መጠን እና C- reactive protein (CRP) ደግሞ የ ሲ- ምላሽ ሰጪ ፕሮቲን ፤ ከደም ናሙና ውስጥ የሰውነትን የመቆጣት መጠን የሚገልፁ ሁለት ጠቋሚ ምልክቶች ናቸው፡፡
ESR የቀይ የደም ህዋሶቻችን በላብራቶሪ የሙከራ ብልቃጥ ውስጥ በምን ያህል ፍጥነት እንደሚዘቅጡ የሚገልፅ ነው፡፡ ይህም የሚለካው በሚሊሜትር በሰዓት ሲሆን ቀጥተኛ ያልሆነ የሰውነትን የመቆጣት መጠን የሚገልፅ ነው፡፡ ምክንያቱም የሰውነት የመቆጣት መጠን ሲጨምር የቀይ የደም ህዋሶቻችን በሙከራ ብልቃጥ ውስጥ ለመዝቀጥ ረዘም ያለን ሰዓት ይወስድባቸዋል፡፡
CRP ጉበታችን ለሰውነት መቆጣት ምላሽ ለመስጠት የሚፈጥረው የፕሮቲን አይነት ነው፡፡ ስለዚህም በደም ውስጥ ያለው የ CRP መጠን የሰውነት መቆጣት ሲጨምር አብሮ ይጨምራል፡፡
በ ESR እና CRP መካከል ያለው ግንኙነት ምንድን ነው?
ስለ ESR እና CRP መረዳት የሚያስፈልገው ዋነኛ ነገር የሰውነት መቆጣት ሲጨምር ሁለቱም እንደሚጨምሩ ነው፡፡ ነገር ግን የሚጨምሩበት ፍጥነት ላይ ልዩነት አላቸው፡፡ CRP ፈጣን ሲሆን የሰውነት መቆጣቱን የቀሰቀሰው ምክንያት ሲታከም እና መፍትሄ ሲያገኝም በፍጥነት ( በአማካኝ በ ሶስት ቀናት ውስጥ) ይቀንሳል፡፡ በአንፃሩ ESR መጠኑ እንዲጨምር ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድ ሲሆን የሰውነት መቆጣቱን የቀሰቀሰው ምክንያት ከታከመ እና መፍትሄ ካገኘም በሗላ ረዘም ላለ ጊዜ ከፍ ያለ መጠንን እንደያዘ ይቆያል፡፡
የ ESR እና CRP መደበኛና ጤናማ መጠን ምን ያህል ነው?
የ ESR እና CRP መደበኛና ጤናማ መጠን እንደ እየሰው እድሜ፣ፆታ እና እንደ የጤና ሁኔታ በተለይም እንዳለብን ስር የሰደደ የህመም ደረጃ ላይ ይወሰናል፡፡ ሆኖም በጤናማ የሰውነት ሁኔታ ላይ ያሉ ሰዎች የ CRP መጠናቸው ከ 3mg/L ያነሰና ሁል ጊዜ በሚባል ደረጃ ደግሞ ከ10 mg/L ያነሰ ነው፡፡ የ ESR መጠን ደግሞ በወንዶች ከ 0-22mm/hr ሲሆን በሴቶች ደግሞ ከ 0-29mm/hr ነው፡፡
የከፍተኛ ESR እና CRP መጠን ምልክቶች ምንድን ናቸው?
ከፍተኛ የESR እና CRP መጠን በራሱ ምልክቶችን ላያስከትል ይችላል፤ ሆኖም ይህን ከፍተኛ መጠን ያስከተሉት ምክንያቶች የተለያየ ምልክትን ይሰጣሉ፡፡
በሰውነት በራሱ በሆነው የበሽታን የመከላከል ስርዓት መዛባት ምክንያት የሚከሰት የ ESR እና CRP መጠን መጨመር እንደ የሰውነት ድካም፣ የሰውነት ላይ ሽፍታዎች ወይም የመገጣጠሚያ እብጠት አይነት ምልክቶች ሲኖሩት በኢንፌክሽን ምክንያት የተከሰተ የ ESR እና CRP መጠን መጨመር ደግሞ ትኩሳትን ይጨምራል፡፡ በተጨማሪም ምልክቶችን ባጠቃይ መግለፅ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም የ ESR እና CRP መጠንን የሚጨምሩ የተለያዩ ምክንያቶች ስላሉ ነው፡፡
የ ESR እና CRP መጠን እንዲስተካከል ምን ማድረግ እችላለሁ?
በኢንፌክሽንና በተለያዩ ሰውነትን በሚጎዱ አደጋዎች ምክንያት የተከሰተ የ ESR እና CRP መጠን መጨመር እነዚሁ ኢንፌክሽኖች ተፈጥሮዓዊ በሆነው የሰውነት ራሱን በራሱ የማከም ሂደት ውስጥ ሲድኑ በራሱ ይቀንሳል፡፡ በአንፃሩ ስር በሰደደ ህመም ምክንያት የሚከሰት ከፍተኛ ESR እና CRP መጠንን ለማስተካከል፤ ይህን ላስከተሉት ስር ለሰደዱ ህመሞች የሚሰጠው ህክምና እጅግ ወሳኝ ነው፡፡
Crohn's & Colitis Ethiopia