ER

ER


በሶማሌላንድ ግዛት በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና በተቃዋሚ ኃይሎች መካከል የተፈጠረውን ግጭት የሸሹ ከ83 ሺሕ በላይ የሶማሌላንድ ነዋሪዎች፣ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር በመዝለቅ በሶማሌ ክልል እየሠፈሩ ነው፡፡

በአፍሪካ ቀንድ ከሶማሊያ ተነጥለው የሚገኙት ሶማሌላንድና ፑንትላንድ ግዛቶች ድንበር መካከል በምትገኘው ላስካኑድ ከተማ የተከሰተው ግጭት፣ የበርካታ የሶማሌላንድ ነዋሪዎችን ሕይወት የቀጠፈ ሲሆን፣ በርካታ ሴቶችና ሕፃናት ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ዶሎ ዞን እየገቡ መሆናቸውን የተመድ የስደተኞች ዋና ኮሚሽነር አስታወቀ።

የኮሚሽኑ ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ እስከ ቅዳሜ የካቲት 11 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ 14 ሺሕ የሚሆኑ አዳዲስ አባወራዎች (ወይም 83 ሺሕ ግለሰብ ስደተኞች) ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል። ስደተኞቹም በሶማሌ ክልል ዶሎ ዞን ውስጥ ቦህ፣ ገልሃሙርና ዳኖድ በተባሉ ሦስት ወረዳዎች ተጠልለው እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡

ዓርብ የካቲት 10 ቀን 2015 ዓ.ም. ተመድ አውጥቶት በነበረው መግለጫ አብዛኞቹ ስደተኞች ባለፈው ሳምንት ነበር ወደ ኢትዮጵያ የገቡት። በሦስቱ ወረዳዎች በ13 ቦታዎች ሠፍረው እንደሚገኙ፣ እንዲሁም የተወሰኑት በትምህርት ቤትና መሰል የሕዝብ መገልገያ ሥፍራዎች ላይ መጠለላቸውን፣ ሌሎች ደግሞ ያለ መጠለያ ሜዳ ላይ እንደሚገኙም አስረድቷል፡፡

ከሶማሌ ክልል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ቢሮ ጋር በመሆን ከ1,500 በላይ ለሆኑ በከፍተኛ ሁኔታ ለተጎዱ አባዎራዎች የተለያዩ ቁሳቁሶችና መሰል ድጋፎችን እየሰጠ እንደሚገኝ፣ ለተጨማሪ 9,000 አባዎራዎችም በቀጣይ ቀናት ድጋፉን እንደሚያደርግ ተመድ ገልጿል፡፡

የክልሉ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ቢሮ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ በሽር አራብ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የስደተኞችን ወደ ኢትዮጵያ መግባት በማረጋገጥ ከተመድ የስደተኞች ዋና ኮሚሽነር፣ ከዓለም አቀፍ ፍልሰት ድርጅት፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ጋር በመሆን የዳሰሳ ጥናት የሚያካሄድ ቡድን በማዋቀር ወደ ሥፍራው ልኮ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

የተላከው ቡድን አሁን መመለሱንና ነገር ግን ሙሉ ሪፖርት እንዳልደረሳቸው የተናገሩት አቶ በሽር፣ ‹‹ግጭቱ አሁንም የቀጠለ በመሆኑ፣ የስደተኞች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ ነው። ቡድኑ የሚያመጣው የዳሰሳ ሪፖርት ታይቶ ቁጥሩንና መሰል መረጃዎች በፌዴራል መንግሥት ደረጃ ይፋ ይሆናሉ፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡ 

የስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ መግባት ከሁለት ሳምንት በፊት መጀመሩን የገለጹት ባለሙያው፣ አካባቢው ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ከሚከሰትበት የድርቅ አደጋ ውጪ በስደተኞች እንደማይታወቅ ጠቁመው፣ ‹‹በአካባቢው ከዚህ በፊት ምንም ዓይነት ስደተኛ ስላልነበረ አሁን ያጋጠመው አልተጠበቀም ነበር፤›› ብለዋል፡፡ 

በሱማሌ ክልል ከሚመለከታቸው ኃላፊዎችና ከኢትዮጵያ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ጋር በመሆን የሕይወት አድን ድጋፎችን እየሰጠ እንደሆነ ተመድ ለሪፖርተር በላከው መረጃ ጠቅሷል። በአካባቢው የሚኖረው ማኅበረሰብ በድርቅ የተጎዳ ቢሆንም ትብብር እያደረገ እንደሆነም አስታውቋል፡፡

‹‹ግጭቱ እየተባባሰ የሚቀጥል ከሆነ ተጨማሪ በርካታ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ድንበር መምጣታቸውን ይቀጥላሉ፤›› ሲል የተመድ መረጃ ያስረዳል፡፡ 

በሶማሌላንድ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥርም እያደገ መሆኑን ተመድ ባለፈው ሳምንት አውጥቶት በነበረው ሪፖርት አስታውቆ ነበር። ሪፖርቱ በወጣበት ጊዜ 185 ሺሕ ያህል ሰዎች በሶማሌላንድ ውስጥ ሌሎች ከተሞችና ወደ ፑንትላንድ ግዛት ተሰደው እንደነበር የተጠቀሰ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ ቁጥራቸው ከፍ ሊል እንደሚችል ይገመታል ተብሏል፡፡

(ሪፖርተር ጋዜጣ)

Report Page