#EPA

#EPA


ቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ እየተስፋፋ የመጣው የስፖርት ውርርድ (ቤቲንግ) ወጣቱን ኪሳራ ውስጥ እየጣለው ነው!

• ብሄራዊ ሎተሪ የስፖርት ውርርድ እንጂ ቁማር ስላልሆነ ፈቃድ ሰጥቻለሁ፤ እንደውም ለበርካቶች የስራ እድል ፈጥሯል ይላል

• የህግ ባለሙያዎች “ውርርድ” በሚል ሽፋን ስሙን ለውጦ የመጣው ‹‹ቁማር›› ነው፤ እየተሰጠ ያለው ፈቃድም የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉን የጣሰ ነው ብለዋል፤

‹‹...በግምት ብቻ በአጭር ጊዜ በቀላሉ ሕይወትዎን የሚቀይሩበት ታላቁ ዘዴ›› በሚል ማስታወቂያ ተስቦ ወደ ጨዋታው እንደገባ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አርባ ምንጭ ከተማ መናኸሪያ ሼል አካባቢ ነዋሪ የሆነው ወጣት አለምሰገድ ይፍሩ ያስታውሳል።

በውርርዱ እስከ 350 ሺህ ብር ማግኘት እንደሚቻል አቋማሪ ድርጅቶቹ በየሰፈሩ በተሽከርካሪ እየተዟዟሩ ሲያደርጉ የነበሩትን ቅስቀሳ በማድመጥ በ2011 ዓ.ም ማብቂያ ላይ ውርርድ ማድረግ ይጀምራል። ምንም እንኳ ቁማሩን ከጀመረ ዓመት ያልሞላ ጊዜ ቢያስቆጥርም ለዓመታት በረሀ ለበረሀ ዞሮ ላቡን አፍስሶ ያጠራቀመውን አንጡራ ሀብቱን ሲያጣ ግን የወራት ጊዜ አልፈጀበትም።

የዚህ ወጣት ታሪክ የብዙ ወጣቶች ታሪክ መሆኑ አይታበልም። ለጨዋታው ፈቃድ የሚሰጠው ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር በበኩሉ፤ የስፖርት ውርርድ ቁማር ባለመሆኑ ፈቃድ እንደተሰጠው በአስተዳደሩ የፈቃድ አሰጣጥና ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ ገዛኸኝ ይልማ ይናገራሉ።

አቶ ገዛኸኝ ይህ የስፖርት ውርርድ ሎተሪ በመሆኑ በብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ማቋቋሚያ አዋጅ 135/1999 በመመሪያ 83/2005 መሠረት የሚሰጥ የፈቃድ እንደሆነም ያስረዳሉ። በመመሪያውም ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ውርርዱን ማድረግ እንደማይችሉ ስለፀደቀ ቤቶቹ ይህንን መሠረት አድርገው ይሠራሉ ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት ይህ ጨዋታ እየተስፋፉና ገበያው እየሰፋ ሕብረተሰቡም እየተሳተፈበት በመሆኑ ለ36 ድርጅቶች ፈቃድ ተሰጥቷል ያሉት አቶ ገዛኸኝ፤ ከእነዚህ መካከል 22 የሚሆኑት በተግባር ሥራቸውን እየሠሩ ነው፤ ቀሪዎቹ ደግሞ ለሥራ የሚያስፈልጋቸውን ግብዓቶች በማሟላት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

መንግሥት ከድርጅቶቹ በአማካይ በየወሩ እስከ ስድስት ሚሊየን ብር ገቢ እንደሚያገኝ የሚናገሩት አቶ ገዛኸኝ፤ ካገኙት ትርፍ ላይ 20 በመቶ የሚሆነውን ደግሞ ሥራውን ሲጀምሩ ለተዋዋሉት በጎ አድራጎት ድርጅት ገቢ እንደሚያደርጉ ይገልፃሉ።

አቶ ገዛኸኝ በድርጅቶቹ ለአንድ ሺህ 200 ዜጎች የሥራ ዕድል እንደተፈጠረና ከጉዳቱ ጠቀሜታው እንደሚያመዝን በመግለጽ ቅሬታ አቅራቢዎቹ የሚያነሱትን ሐሳብ ውድቅ ያደርጉታል።

የህግ ባለሙያ የሕግ ባለሙያና በማንኛውም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጠበቃ አቶ ፍጹም አስራት፤ በተለምዶ ውርርድ በሚል ሽፋን ስሙን ለውጦ የመጣው ‹‹ቁማር›› ነው ይላሉ። ቁማር ማለት በአነስተኛ የገንዘብ ወጪ አንድን ያልተገባ ነገር ለማግኘት ማሰብ ነው የሚሉት ጠበቃው፤ ውርርዱ የስፖርት ጨዋታዎችን በመገመት ግምቱ ትክክለኛ ከሆነ የሚገኝ ገንዘብ ነው። ያልተገባ ክፍያ ለመውሰድ የሚደረግ ጥረት ውርርድ ወይንም ቁማር መሆኑንም ያስረዳሉ።

በኢፌዴሪ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 789 ሎተሪዎችንና ውርርዶችን የሚመለከቱ ሕጎችን መጣስ አስመልክቶ “ውርርድ ፈቃድ ኖራቸውም አልኖራቸውም ማድረግ የተከለከለ እንደሆነ ያስቀምጣል”። ለመሰብሰቢያ በተዘጋጀ ስፍራ የቁማር ጨዋታ ወይንም ውርርዶችን ወይንም በመንግሥት ክልከላ የተደረገባቸው ሌሎች የዕድል ጨዋታዎችን ከልክሏል። በዚህም ቤቲንግ ወይንም የስፖርት ውርርድ ማድረግ እንደማይቻል ሕጉ አስቀምጧል።

በሕግ አተረጓጎምም አዋጅ ደንብ ቀጥሎም መመሪያ ነው የሚሉት አቶ ፍጹም፤ የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ አዋጅ በመሆኑ ማንኛውም ይህንን የሚጣረስ መመሪያ ተገቢነትም ሆነ ተፈፃሚነት እንደማይኖረው ያስረዳሉ። ስለሆነም ፈቃድ ሰጪው አካል በምን አግባብ እንደሰጠ መመርመር ይገባዋል ሲሉ ይመክራሉ።

(ኢፕድ)

Report Page