EPA

EPA


የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ፤ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎትን የ9 ወር አፈጻጸም ገምግሟል።


ኮሚቴው ከዚህ ግምገማ በፊት ማለትም ሚያዚያ 3/2016 ላይ #ድንገተኛ ምልከታ አድርጎ ነበር።


ቋሚ ኮሚቴው ምን አለ ?


- ምንም እንኳ የተጀመሩ ሥራዎች ጥሩና ተስፋ ሰጪ ቢሆኑም በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ችግሮችን እና የተገልጋይን ቅሬታ መፍታት አልተቻለም።


- ተገልጋዮች አገልግሎት ለማግኘት ብለው በሚደርስባቸው እንግልትና ስቃይ ምክንያት በተቋሙ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ቅሬታ እንደሚያቀርቡ በድንገተኛ ምልከታ መመልከት ተችሏል።


- በዋና መስሪያ ቤቱ ተገልጋይ በተቋሙ ሠራተኞች #መሰደብ፣ #መመናጨቅ እንዲሁም #መገፍተር_ጭምር የሚደርስበት በመሆኑ ተገልጋይ በሥነ ምግባር መስተናገድ አለበት።


- በአዲስ አበባ ካሳንቺስ አካባቢ የሚገኘዉ የውጪ ዜጎች አገልግሎት ተቋም የሚሰጠው አገልግሎት ኢትዮጵያን የማይመጥን፣ ምቹ ያልሆነ እና የንጽህና ጉድለት ያለው ነው። ይህ መታረም አለበት።


- ዋናው መስሪያ ቤት ለአገልግሎት ምቹ ያልሆነ፣ ሕንፃው የቆየ እና አስፈላጊዉን የማሻሻያ ጥገና ያላገኘ ነው። ሕንፃው ከተቋሙ አገልግሎት አሰጣጥ ባህሪ ጋር የማይጣጣም ስሪት ያለው ነው።


- በዋናው መስሪያ ቤት ያለው መጨናነቅ እንዲቀንስ በአዲስ አበባ ከተማ ከ5 ያላነሱ ቅርንጫፍ ጽ/ ቤቶች እንዲከፈቱ የመፍትሔ ሃሳብ ቢሰጥም አልተፈጸመም። በተለይ በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ የማስፋፋት ሥራዎች መሠራት አለበት።


- የደላላ ሰንሰለትን በመለየት ማቋረጥ ያስፈልጋል።


- አሁንም ከደላሎች ጋር የሚመሳጠሩ #ሠራተኞች በመኖራቸው ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አለበት።


- የሠራተኛ ባጅ አለመኖሩም ሊታሰብበት ይገባል።


በምክር ቤቱ የተገኙት የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ለተነሱት ጉዳዮች ምላሽ ሰጥተዋል።


ተቋሙ ረዥም እድሜ ያስቆጠሩ ችግሮች ያሉበት ነው ብለዋል። ችግሮቹን ለመቅረፍ አዲሱ አመራር በዝርዝር ችግሮቹን መለየቱን ገልጸዋል።


ተቋሙ የአደረጃጀት ችግር ያለበት በመሆኑ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆነ የራሱ አደረጃጀት እንዲኖረው ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።


የበጀት ችግሩን ጭምር የሚፈታ የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅት ተጠናቆ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ተልኳል ብለዋል።


በተቋሙ ከፍተኛ የሰው ኃይል እጥረት መኖሩን አመልክተው አሁን ላይ ከሚፈለገው የሰው ኃይል ከግማሽ በታች የሰው ኃይል መኖሩንና የሕግ ማዕቀፉ ሲጸድቅ የሰው ኃይል ክፍተቱ እንደሚሟላ ተናግረዋል።


በጊዜያዊነት ችግሩን ለመቅረፍም ሦስት መቶ የሚጠጉ ሠራተኞች በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምሩ ጠቁመዋል።


የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምቹ ቦታ ለተቋሙ መስጠቱን ተናግረው ለአገልግሎት ምቹ ተደርጎ ሥራ ይጀምራል ብለዋል።


በአዲስ አበባ በአራቱም አቅጣጫዎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ለመክፈት እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።


የሠራተኞች ዩኒፎርም ዲዛይን መጠናቀቁን ገልጸው፤ ባጅ እና የሠራተኛ መግቢያ በር ለብቻ በማድረግ ዲጂታላይዝ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል። #ኢፕድ


@tikvahethiopia

Report Page