EPA

EPA


በመላ አገሪቱ ከፍተኛ የደም እጥረት መከሰቱንና ያለውም የመጠባበቂያ ደም ክምችት ከአምሥት ቀናት የማይዘል መሆኑን ብሔራዊ ደም ባንክ አስታወቀ::

በብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት የደም ለጋሾች ዘርፍ አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር ተመሥገን አበጀ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ በአገሪቱ ያሉት የሁለቱ ትላልቅ ሃይማኖቶች ተከታዮች ፆም ላይ መሆናቸውን ተከትሎ በመላ አገሪቱ ከፍተኛ የደም እጥረት ተከስቷል::በአገሪቱ ያለውም የመጠባበቂያ ደም ክምችት ከአምሥት ቀናት የማይበልጥ ነው::

በአገር ደረጃ ሲታይ ከፆም በፊት በዚህ ዓመት የነበረው የደም ክምችት አመርቂ የሆነበት ዓመት ነበር ብሎ መውሰድ ይቻላል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ የዐቢይ እና ረመዷን አፁዋማት ከገቡ በኋላ የመደበኛ ደም ለጋሾችም ሆነ ሌሎች ለጋሾች ቁጥር ማሽቆልቆሉን ተናግረዋል::

ይህም የደም ክምችት ላይ ከፍተኛ እጥረት እንደፈጠረ አመልክተው፤ በተለይ እንደ ፕላትሌት የደም ተዋፅዖ እና ‘ኦ’ የደም ዓይነት ክምችቶች እጥረት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ብለዋል::

ፕላትሌት የሚባለው የደም ተዋፅዖ ለካንሰር ታማሚዎችና የደም መፍሰስ ችግር ላለባቸው ታካሚዎች የሚሰጥ የደም ዓይነት መሆኑንና ያለው ክምችት ለአንድ ቀን ብቻ ሲሆን ‘ዖ’ የተባለው የደም ዓይነትም በዛ ቢባል ለሁለት ቀናት የሚሆን ክምችት መኖሩን አመልክተዋል::

በአዲስ አበባ ያለውን የደም ፍላጎት እንደ አብነት ወስደው ያስረዱት ዶክተር ተመሥገን ፕላትሌት የሚባለው የደም ተዋፅዖ ብቻ ከ200 ዩኒት በላይ በቀን እንደሚያስፈልግ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል::

የሌሎች የደም ዓይነቶች በአሁኑ ጊዜ ያለውም የደም ክምችት መጠን ዝቅተኛና ለአምሥት ቀናት መጠባበቂያ እንደሆነና ለድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ሊሆን የሚችል እንደሆነ በአፅንዖት ገልፀዋል::

ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ብቻ ከ350 እስከ 400 ዩኒት ደም በየቀኑ ይሰበሰብ እንደነበር አስታውሰው፤ የተለዩ ደም የመሰብሰብ መርሐ ግብሮች ሲኖሩ ደግሞ እስከ አንድ ሺህ ዩኒት እና ከዚያ በላይ መሰብሰብ ይቻል ነበር፤ አሁን የለጋሾች ቁጥር ከግማሽ በታች መሆኑን ጠቅሰዋል::

በአገሪቱ ያሉ የመደበኛ ደም ለጋሾች ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑ ለክምችቱ መቀነስ ተጨማሪ ምክንያት መሆኑን ገልጸው፤ እንደ አገር ሲታይ ከአጠቃላይ የደም ለጋሾች ቁጥር መደበኛ የደም ለጋሾች ቁጥር ከ5 እስከ 8 በመቶ ብቻ መሆናቸውን አስረድተዋል::

የአዳዲስ ደም ለጋሽ ቁጥር የመጨመር አዝማሚያ በየጊዜው ቢታይም የመደበኛ ደም ለጋሾች ቁጥር ግን መሻሻል እንዳላሰየ አመልክተው፤ ካሁን በፊት በተናጠል፣ በቡድን እና በተቋማት ሲደረግ የነበረውን የደም ልገሳ ፕሮግራሞች ተጠናክሮ እንዲቀጥል ዶክተር ተመሥገን ጥሪያአቸውን አስተላልፈዋል::

በፆም ወቅት በተገቢው መጠን ደምን ሊተካ የሚችል ፈሳሽ በመውሰድ መለገስ እንደሚቻልና ምንም ዓይነት ጉዳት እንደሌለው ዶክተር ተመሥገን ገልፀዋል::

በሰሞነ ሕማማት እና አፁዋማት ላይ ያለው ማኅበረሰብ ደም በመለገስ በዓሉን ቢያከብረው ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል ብለዋል::

ደም ባንኮች በማንኛውም ሰዓት ክፍት ስለሆኑ ደም ለጋሾች በፈለጉት ሰዓት ሄደው ደም መስጠት እንደሚችሉና አሁን በሕዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ እየተከበረ ያለውን ሰሞነ ሕማማትን ደም በመለገስ ለበጎ ነገር ተጠቀሙበት ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል::

መጪዎቹን በዓላት ስናከብር በሞትና በሕይወት መካከል ሆነው የእኛን ደም የሚፈልጉትን ሳንረሳ ይሁንም ብለዋል::

(የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)


Report Page