#EPA
በተለምዶ እንቁላል ፋብሪካ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ በመኪና ገበያነት ይታወቃል። ሰሞኑን ግን “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” እንዲሉ፤ የአካባቢው የመኪና ነጋዴዎች አዲሱ የኤክሳይዝ አዋጅ ረቂቅ ለተወካዮች ምክር ቤት ከቀረበ ጀምሮ “ባልተረጋገጠ እሳቤ ምክንያት ሽያጭ ከቆመ ወራት አስቆጥረናል::” ይላሉ።
ከመሸጫዎቹ በአንዱ የአንዲት ቶዮታ ቪትስ የኋላ በር ተከፍቶ በዕቃ ማስቀመጫው ውሃ ተቀምጦበታል። አራት ወጣቶች እና ሁለት ጎልማሶች ክፍት ከተተወው የኋላ በር ፊት ለፊት ከብበው ተቀምጠው የያዙትን ውሃ እየተጎነጩ ያወራሉ። ስለገበያው ሁኔታ ሲጠየቁ ቀደም ሲል በሃዘን ስሜት ሲነጋገሩ የነበሩት ሁሉም አንድ ላይ በቁጣ ይናገራሉ:: “ገበያው ሞቷል፤ በፊት አንድ መኪና ይሸጥ ከነበረበት በ40 እና በ50 ሺህ ብር ቅናሽ ለመሸጥ ብንሞክርም እንኳን ደፍሮ የሚገዛ የለም” ይላሉ።
የመኪና አስመጪው አቶ መሃመድ አወል እንደሚናገሩት፤ መኪና ሻጭ ብዙ ቢሆንም መኪና ገዢ ጠፍቷል። ቀድሞ የመኪና ማስገቢያ ግብር ጨመረ ተብሎ ሲወራ፤ እነርሱም በመኪና ዋጋ ላይ ጨምረው ነበር። አሁን ደግሞ “አዲስ ያልተነዳ መኪና የማስገቢያ ቀረጥ ቀንሷል” መባሉ ገበያውን አበላሽቶታል። በተጨማሪ ገዢው ህዝብም ሆነ የመኪና ነጋዴው ግብሩ በምን ያህል ቀነሰ ወይም ጨመረ የሚለው በትክክል አልገባውም፤ በዚህ ሳቢያ ገበያው ተበላሽቷል።
ከራስ ደስታ ሆስፒታል የእንቁላል ፋብሪካን አደባባይ አልፈው ሲሄዱ በስተቀኝ ባለው የተንጣለለ ግቢ ውስጥና የዛፎች ጥላ ሥር ከ500 ያላነሱ መኪናዎች ተደርድረዋል። አብዛኛዎቹ ለአዲስ አበቤዎች የትራንስፖርት አገልግሎት መስጫነት የሚያገለግሉት “ስሪ ኤል” እና “ፋይፍ ኤል” የተባሉ ሚድ ባስ የቶዮታ ምርቶች ናቸው::
ሌሎቹ ወደ ክፍለ አገር በሚደረጉ ጉዞዎች ላይ በፍጥነት የሚሽከረከሩት “ሃይሩፍ” እና “ዶልፊን”፤ እንዲሁም ሌሎችም ዘመነኞቹ ብርማ ቀለም የተቀቡ መኪናዎችም ተደርድረዋል። በግቢው ውስጥ ከበር እንደገቡ ስምንት ሰዎች በሸራ የተወጠረች የጀበና ቡና ማፍያ መጠለያ ውስጥ ተቀምጠው፤ ገሚሱ የእጅ ስልኩን እየነካካ አንዳንዱ ፎቶ። አንዳንዱ ደግሞ ፌስቡክ ይመለከታል። የተወሰኑት እርስ በርሳቸው ያወራሉ።
ፂመ ሸበቶው አለሙ በቀለ (ስማቸው የተቀየረ) እንደሚናገሩት፤ 500 መኪናዎችን ይዟል ተብሎ የሚገመተው ግቢ የሚታወቀው መኪና ገዢ ሲመላለስበት ነበር። አሁን ግን እንኳን ገዢ ጠያቂ ጠፍቷል። በፊት መኪና ሲሸጥ የመኪና አስመጪው ብቻ ሳይሆን የቴክኒክ ፈታሽ፤ የመኪና ወንበር ነጋዴዎች፣ አሻሻጭ ወጣቶች እና ከሽያጩ ጋር ተያይዘው የሚመጡ የታክሲ አሽከርካሪዎች እና ረዳቶች ሳይቀሩ ስራ ያገኙ ነበር። አሁን እነዚህ ሰዎች ሁሉ ስራ አቁመዋል።
“በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ሰዎች በትራንስፖርት ችግር ይሰቃያሉ” የሚሉት የመኪና ሻጩ፤ እነርሱ ግቢ ውስጥ ያሉ 500 መኪናዎች በስራ ላይ ቢውሉ ችግሩን በማቃለል በኩል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሊኖራቸው ይችላል በማለት ይጠቁማሉ።
ጨምረውም “እነዚህ መኪናዎች ከውጭ የገቡት ቡና ተሽጦ በተገኘ የውጭ ምንዛሪ ነው። የአገር ሃብት ናቸው። አገልግሎት መስጠት እያለባቸው ገበያ አጥተው ፀሃይ ላይ ተሰጥተው መዋላቸው ለአንድ ነጋዴ ብቻ ሳይሆን ለአገርም ኪሳራ ነው” በማለት ይናገራሉ።
በተንጣለለው ግቢ ውስጥ ከተደረደሩት መኪናዎች በስተግራ ጉብ ባለው የድንጋይ ቤት ውስጥ በጠራራ ፀሃይ ገመድ እየዘለሉ ራሳቸውን ለማዝናናት ከሚሞክሩት የመኪና ነጋዴዎች መካከል አንዱ ወጣት ሙሉጌታ አወል ነው። እርሱ እንደሚናገረው፤ በመኪና ላይ “ግብር ሊጨምርም ሆነ ሊቀንስ ነው” ተብሎ መወራት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ገበያው ተቀዛቅዟል።
ምንም እንኳን የአዋጁ አላማ ‘የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል እና አገር ለመጥቀም ነው’ ተብሎ የተገለፀ ቢሆንም፤ ገበያውን ከማቀዛቀዝ አልፎ የመኪና ነጋዴዎችን እና ከመኪና ሽያጭ ጋር ተያይዞ የሚሰሩ ሰዎችን በሙሉ ጎድቷቸዋል። ጉዳቱ በዚህ የሚያቆም ብቻ ሳይሆን ወደፊትም ይቀጥላል የሚል ስጋት አለው።
ወጣት ሙሉጌታ እንደሚናገረው፤ አዋጁ እና የግብር ማሻሻያው በደንብ ሲታይ የአገሪቱን ሁኔታ ያገናዘበ አይመስልም። አሁን ላይ የኢትዮጵያ መኪና አስመጪዎች “አዳዲስ መኪናዎች” ብለው የሚያስመጧቸው በዓለም አቀፍ ገበያ ብዙም ተፈላጊነት የሌላቸውን ነው።
እነዚህ መኪናዎች ቶሎ ከጥቅም ውጪ የሚሆኑ እና የመለዋወጫ ዕቃ እጥረት የሚያጋጥማቸው ናቸው። መኪናዎቹ ከኢትዮጵያ የመንገድ ስሪት አንፃር ቶሎ የማርጀት ዕድል የሚያጋጥማቸው ከመሆናቸውም ባሻገር የሚገዙበት ዋጋም ቀላል ባለመሆኑ ዜጎች መኪና የመግዛት አቅም አይኖራቸውም። የተገዙትም ለጥቂት ዓመት አገልግለው ይቆማሉ። ይህ ደግሞ መኪና ገዢውን ብቻ ሳይሆን አገርንም የሚያከስር ነው።“ህዝቡ ያልተረዳው አንድ ነገር አለ::
በመሰረታዊነት መኪናን እያስወደደ ያለው የኤክሳይዝ ታክስ ሳይሆን ቅድሚያ የሚከፈለው የ35 በመቶ ቀረጥ ነው።” የሚለው ወጣት ሙሉጌታ፤ መኪናውን ሌላ አገር ሄዶ መግዛት ብቻ ሳይሆን የማስጫኛ፤ የመርከብ ማጓጓዣ፤ ጅቡቲ ላይ የተቀመጠበትም ሆነ ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ የሚከፈሉ ክፍያዎች፤ ቢሮክራሲው እና አዲስ አበባ ላይ የመሸጫ ቦታ ኪራይ፤ እንዲሁም የአሻሻጭ ሰራተኛ እና ሌሎች ተደራራቢ ወጪዎች ዋጋውን የሚያንሩት መሆኑን ይናገራል።
ዝርዝር የመተግበሪያ ደንብና መመሪያ ሳይወጣለት እንዲህ ያለ ለውጥ ያመጣው የኤክሳይዝ አዋጅ በሌላ ጎኑ የነጋዴዎቹን ስራ ገድሎባቸዋልና፤ “መንግስት አዋጁን ከመውጣቱና ወሬው ከመነዛቱ በፊት በጉዳዩ ላይ የመኪና አስመጪ ነጋዴዎችን ማወያየት እና የሚናገሩትን ማዳመጥ ነበረበት። ‘ነጋዴ ጥቅሙን ብቻ የሚያይ ነው’ ብሎ መደምደም አይገባም። ነጋዴም ዜጋ ነው። መንግስትን ጨምሮ ሌሎችም ሊያስቡለት ይገባ ነበር” ይላሉ።
[አዲስ ዘመን ጋዜጣ]