EOTC

EOTC


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ከሐምሌ 22 እስከ ሐምሌ 28 ቀን 2016 ዓ/ም ድረስ በሁሉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ገዳማት የሚፈጸመውን የምሕላ ጸሎት አስመልክቶ ከቋሚ ሲኖዶስ 

              የተሰጠ መግለጫ


‹‹ተማሕለሉ ወሰአሉ ኃበ አቡክሙ ሰማያዊ እስመ አብ ይሁበክሙ ኵሎ ዘሰአልክሙ…አባታችሁ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋልና ወደ ሰማይ አባታችሁ ለምኑ፣ ምሕላንም አውጁ›› ኢዩኤል 1፤14 ቅዱስ ያሬድ 

በሀገር አስተማማኝ ሰላም ሲጠፋ በጾም በጸሎት በመወሰን፣ምሕላን በማወጅ ልባዊ በሆነ ተማሕጽኖ ሁሉን ማድረግ ወደሚችለው አምላካችን አግዚአብሔር ምልጃን ማቅረብ የሚያስፈልግ መሆኑን ከሀገራችን ሊቃውንት መካከል የመጀመሪያ የሆነው ቅዱስ ያሬድ ከሰማያውያን ዐውደ ማህሌት ሰምቶ በቀሰመው ጣዕመ ዜማ አበክሮ ይነግረናል፡፡

በመሆኑም ውሎ ማደር፣ ወጥቶ መግባት በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች ስጋት ከሆነ ሰነባብቷልና በእውነት የሚለምኑትን ሁሉ የሚሰማ እግዚአብሔር መተላለፋችንን ይቅር እንዲለን፣ ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም፣ ለቤተ ክርስቲያናችን ፍቅር አንድነት፣ ለሕዝባችን ደኅንነት እንዲሰጥልን ከአንድነት ገዳማት ኅብረት በቀረበው ጥያቄ መነሻነት ምሕላ ማወጅ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ በሁሉም የሀገራችን ክፍልና በሌሎችም አህጉራተ ዓለም የምትገኙ መነኰሳትና መነኰሳይያት ከሐምሌ 22 እስከ ሐምሌ 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ለሰባት ተከታታይ ቀናት በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ ትውፊት መሠረት የገዳማት ኅብረቱን ጥሪ ተቀብላችሁ የምሕላ ጸሎት እንድታደርሱ፣ በጤና ችግር ምክንያት ካልሆነ በስተቀር እስከ ዕርበተ ፀሐይ በመጾም ሱባኤ እንድትይዙ፣ ቋሚ ሲኖዶስ በኅብረተ መንፈስ ቅዱስ ከአደራ ጋር ያሳስባል፡፡

ሁሉም የቤተክርስቲያናችን አገልጋዮችና ምእመናን ሀገራዊ ሰላምን፣ መረጋጋትንና ፍቅር አንድነትን ለማስፈን ጾምና ጸሎት በታወጀበት የምሕላ ሳምንት ለገዳማውያኑ ፀጥታ ሲባል ወደ ገዳማት የምታደርጉትን ጉዞ ለጊዜው እንዲቆይ አድርጋችሁ መደበኛ ሥራችሁን በያላችሁበት ቦታ እየሠራችሁ እግዚአብሔር የገዳማውያኑን ጸሎት ሰምቶ ለሀገራችንና ለሕዝባችን ምሕረትን እንዲሰጥ በኅሊና ዝግጅት፣ በሐሳብ አንድነት ሆናችሁ በጾም በጸሎት እንድተጉ ቋሚ ሲኖዶስ መንፈሳዊ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

‹‹እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ››

ሐምሌ 5 ቀን 2016 ዓ.ም.

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

Report Page