ENA

ENA



አገራዊ የምክክር መድረኮች በቀጣይ ዓመት ሕዳር ወር እንደሚጀመሩ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።

የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤አገራዊ ምክክሩ የቅድመ-ዝግጅት፣ዝግጅት፣ ምክክር እንዲሁም የትግበራና ክትትል የተሰኙ አራት ምዕራፎች አሉት።

እስካሁን ባለው ሂደትም የቅድመ-ዝግጅት ሥራዎች እየተጠናቀቁ መሆኑን ተናግረዋል።

ከቅድመ-ዝግጅት ሥራዎች መካከል ዋነኛ የሆነው የእቅድ ሥራ በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ተጠናቆ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይትና ግምገማ እንደሚደረግበት ተናግረዋል።

በተያዘው ክረምት ደግሞ የዝግጅት ምዕራፎች ተጠናቀው በመጭው ዓመት ህዳር ወር ላይ የምክክር መድረኮች እንደሚጀመሩ ነው የገለጹት። 

የዝግጅት ምዕራፎችም የተሳታፊ ልየታና ሥልጠና እንዲሁም ለአገራዊ መግባባት የተሻሉ አጀንዳዎችን መለየት የሚሉ ጉዳዮችን ያካተተ እንደሆነ ገልጸዋል።

የውይይት አጀንዳ የሚቀረጸው ከታችኛው ኅብረተሰብ ክፍል ፍላጎት እንደሆነ ጠቅሰው፤ከዚህ አኳያ ገለልተኛ የሕዝብ ወኪሎች በተገቢው መልኩ ይለያሉ ነው ያሉት።

ኮሚሽኑም መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ ሚዲያ ክፍሉን እያጠናከረ መሆኑንም ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ የአገልግሎት ዘመናቸውን ያጠናቀቁ የወሰንና ማንነት እንዲሁም በዕርቀ-ሰላም ኮሚሽኖች የተጠኑ የጥናት ሰነዶችን መረከቡን አንስተዋል።

ከሰነዶችም አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን በግብዓትነት ይጠቀማል ብለዋል።

በተጨማሪ ኮሚሽኑ የራሱን ጥናት በማስጠናትም ከሌሎች ጥናቶች ላይ አዋህዶ ለምክክር እንደሚጠቀምበት ገልጸዋል።

"ምክክሩ በመንግሥትም ሆነ በሌላ የውጭ አካላት እንዲጠመዘዝና እንዲመራ አንፈቅድም"ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ከውስጥና ከውጭ ያሉ ባለሙያዎችን በማሰባሰብ ምክክሩ ግቡን እንዲመታ እንሰራለን ብለዋል።

ከገንዘብ ጋር በተያያዘም ኮሚሽኑ በገንዘብ ሚኒስቴር ሥር የትረስት ፈንድ በማስከፈት ማንኛውም ገንዘብ ድጋፍ ያደረገ የውጭ አካል ኦዲት ተደርጎ ገንዘቡ ምን ላይ እንደዋለ በግልጽ ይፋ ይደረጋል ብለዋል።

ይህ ካለማንም ጣልቃገብነት የሚከወን ምክክር ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ግንባታ አሻራ ጥሎ እንደሚያልፍም ያላቸውን እምነት ተናግረዋል። 

ለአገራዊ ምክክሩ ስኬት እንደ ስጋት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከልም በየጊዜው የሚነሱ ግጭቶች፣የዓለም አቀፉ ተለዋዋጭ ሁኔታና የሚዲያዎች የተዛባ መረጃዎች ሥርጭትን ለአብነት ጠቅሰዋል።

አገራዊ ምክክሩ በሦስት ዓመታት መጨረሻ ጠንካራ ውጤት እንደሚያመጣ ያላቸውን ተስፋ ፕሮፌሰር መስፍን ጠቁመዋል።

(ኢዜአ)


Report Page