Dr Debretsion G/Micahel

Dr Debretsion G/Micahel


#ድርድር 


የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት በሰላም መቋጫ ያገኝ ዘንድ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑ ይታወቃል።


ከቅርብ ጊዜ ወዲህም አንዳንድ የውጭ ሀገር ሚዲያዎች ድርድርን በተመለከተ በግልፅ ምንጫቸው የማይታወቁ መረጃዎችን ሲያሰራጩ ከርመዋል።


የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን ንግግር አለመጀመሩን ነገር ግን ለዚሁ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁሟል።


ትላንት ፓርላማ የቀረቡት ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በይፋ የታወቀ አጥኚ ኮሚቴ ተቋቁሞ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካኝነት እየተመራ መሆኑን፤ እስካሁን ውጤቱን አለማሳወቁን እና የሚደራደረው ኮሚቴም ይሄ መሆኑን ጠቁመው ነበር። ድርድር ሲጀመር መንግስት የሚደብቀው ነገር እንደሌለም ገልፀው ነበር።


ይህ የጠቅላይ ሚስትሩ ንግግር ከተሰማ ብዙም ሳይቆይ በህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል የተፃፈ ደብዳቤ ተሰራጭቷል።


ይኸው ደብዳቤ ህወሓት በኬንያ መንግስት በተጠራ ድርድር የሚሳተፍ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ለመላክ መዘጋጀቱን ይገልጻል።


ዳብዳቤው በኬንያ መንግስት የተጠራ ድርድር በናይሮቢ ስለመኖሩ ፍንጭ የሰጠ ነው።


ዶ/ር ደብረፅዮን የሰላም ድርድሮችን በማስመልከት የትግራይ ክልልን አቋምን ለማሳወቅ ደብዳቤውን የፃፉት ለአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀ መንበርና የሴናጋሉ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል፣ ለኬንያው ፕሬዝዳንት አሁሩ ኬንያታ፣ ለተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አልናህያን እና ለታንዛኒያዋ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሀሰን እንዲሁም የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝን ጨምሮ ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ነው።


በዚሁ ደብዳቤ ለምን እንደሆነ ግልጽ ባያደርጉም " ሚስጥራዊ ስምምነቶችን ለማድረግ ዝግጁ አይደለንም " ብለዋል፡፡


የአፍሪካ ህብረት ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ዝምታን መምረጡ፤ ከተቋሙ መርሆች በተቃራኒ ለመቆሙ ማሳያ ነው የሚሉም ቅሬታ አቅርበዋል፡፡


በዚህም የትግራይ ህዝብ እና የሚመሩት ድርጅት በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ያላቸውን አመኔታ ለመመለስ እንደሚቸገሩ አስታውቀዋል፡፡


ለሰላም ተጨማሪ ኪሎ ሜትሮችን ለመጓዝ ያለን ዝግጁነት የምናምንባቸው መርሆቻችን ዘንግተን እንዳልሆነ መረዳት ያስፈልጋል ያሉት ዶ/ር ደብረፅዮን የአፍሪካ ቀንድ የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ ተወካይ ኦሊሴጎን ኦባሳንጆን የተቀበልነው ለአፍሪካ ህብረት መርሆች እና ለሽማግሌዎች ባለን ክብር መሆኑ ሁሉም ሊያውቀው ይገባልም ብለዋል፡፡


" ይህ ሲባል ተወካዩ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያላቸው ቅርበት የትግራይ ህዝብ ሳያስተውለው ቀርቶ አይደለም " ሲሉም በኦባሳንጆ አዳራደሪነት ያላቸውን እምነት እምብዛም እንደሆነ ግልጽ አድርጓል፡፡


ከኦባሳንጆ በተቃራኒ ለታንዛኒያ እና ኬንያ መሪዎች ያላቸው ክብር እና ምስጋና ከፍ ያለ መሆኑን በደብዳቤያቸው ገልጸዋል፡፡


" በታንዛኒያ መንግስት እንተማመናለን እንዲሁም የታንዛኒያዋ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ለኢትዮጵያ ሰላም እያደረጉት ያለውን ጥረት እናደንቃለን”ም ብለዋል።


ዶ/ር ደብረጽዮን " የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ መርህ ላይ ተመሮኮዘና አካታች ሆነ የአደራዳሪነት ሚና " እናደንቃለን ብለዋል፡፡


በኬንያ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያት መሪነት የግጭቱ ተሳታፊ ወገኖች በናይሮቢ ለመገናኘት ለተደረሰው ስምምነት ተገዥ መሆቸውን ገልፀድ ፤ ህወሓትን የሚወክሉ ተደራዳሪዎች በቅረቡ ወደ ናይሮቢ ለመላክ መዘጋጀታቸውን አስታውቋል፡፡


" ለሚደረገው ድርድር ልዑክ ለመላክ ተዘጋጅተናል"ም ነው ያሉት ሊቀ መንበሩ፡፡ በሰላም ሂደቱ በኬንያው መንግስት መሪነት እንደ አሜሪካ ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ፣የተባበሩት መንግስታት እና የአፍሪካ ህብረት የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚያደርጉት ተሳትፎ በደስታ እንቀበላለን ሲሉ አክለዋል፡፡

(አል ዓይን )

Report Page