Dr Abiy Ahmed
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማራ ክልል ፦
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በገበታ ለሀገር መርሐ ግብር የሚለማውን የጎርጎራ ፕሮጀክትን በዛሬው ዕለት አስጀምረዋል።
በስነስርዓቱ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር እንዲሁም ሌሎች የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተው ነበር።
ዶክተር አብይ ዛሬ ባደረጉት ንግግር ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክት 3 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ አሁን ላይ ከ 4 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን አውስተዋል።
ህዝቡ በስፋት በመሳተፍ ከታሰበው በላይ ገንዘብ እንዲሰበሰብ በማድረጉም ምስጋና አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው የጎርጎራ ገበታ ለሀገር ልማት ፕሮጀክትን እውን ለማድረግ አሁን ላይ በፕሮጀክቱ አካውንት 1 ቢሊዮን ብር ገቢ መደረጉን ገልፀዋል።
ፕሮጀክቱ እንዲሳካም የክልሉ መንግስት የቅርብ ክትትል እንደማይለየው ያረጋገጡት ርዕሰ መስተዳድሩ የአካባቢው ህብረተሰብና የፕሮጀክቱ ተቋራጭ በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማራ ክልል ያስጀመሩት የመንገድ ፕሮጀክት፦
ዶ/ር አብይ በአማራ ክልል ዛሬ ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚገነቡ ሁለት መንገዶች ግንባታን አስጀምረዋል።
በአማራ ክልል የሚገነባው ከዱርቤቴ - ቁንዝላ - ሻሁራ - ፍንጅት እንዲሁም ከገለጎ - መተማ ከ5 ቢሊዮን 374 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በሁለት ምዕራፍ የሚገነባውን 261 ኪሜ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ዚዢያንግ ኮሚዩኒኬሽን ኮንስትራክሽን ግሩፕ ይሠራዋል ተብሏል።
መንገዱ የአማራ ክልል 3 ዞኖችን ከማስተሳሰር ባለፈ የሀገሪቱ የገቢና ወጪ ምርት ዋና መስመር የሆነውን የመተማ ሱዳን ኮሪደርን የሚያገናኝ በመሆኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ ነው ተብሏል።
መንገዱ በሶስት ዓመታት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚደረግም ተገልጿል።
"ምግባችን ከምድራችን"
በሜጫ ወረዳ ከ3 ሺ ሄክታር መሬት በላይ የተዘራው የስንዴ ሰብል ውጤታማ መሆኑን ጠቅላይ ሚንስትር አቢይ አህመድ ገልፀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት ፥ "በአማራ ክልሏ ሜጫ ወረዳ 3 ሺህ 590 ሄክታር፣ በ15 ኩታ ገጠም እርሻዎች ላይ፣ የቆጋን መስኖ በመጠቀም ስንዴን በውጤታማነት ማብቀል ችላለች" ብለዋል።
በተመሳሳይም፣ አነስተኛ የመሬት ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች በመስኖው አማካኝነት አቮካዶን በተሳካ ሁኔታ ማምረት እንደቻሉም ገልጸዋል።
አርሶ አደሮቻችን በዚህ ከቀጠሉ "ምግባችን ከምድራችን" የሚለው ራእይ ይሳካል ነው ያሉት።
(Dr Abiy Ahmed)