Dr Abiy Ahmed

Dr Abiy Ahmed


ጠቅላይ ሚኒስትሩ TPLFን በተመለከተ ምንድነው ያሉት ?

ዶክተር ዐቢይ አህመድ ፦

" ... ከTPLF ስህተቶች 6 ነገር እንድንማር እጠይቃለሁ።

TPLF የያዘው ከፋፋይ ሀሳብ ያነሳው የሰፈር አጀንዳ የተጠናወተው ክፋት እና ጥላቻ ሌብነት ለከፍተኛ ሽንፈት ያበቁት ወደፊትም ድል በሰፈሩ እንዳይደርስ የሚያደርጉት እኩይ ባህሪዎቹ ቢሆኑም ከዚህ ሁሉ ግን ባለፈው አንድ አመት ገደማ ምናልባትም ዘለግ ብለም ሶስት አመት ገደማ ብንመለከት TPLF በትክክል ማሰብ ባለመቻሉ በህዝቡ ላይ ያደረሰውን ጫና ለማየት ስለሚያግዝ ፦

1ኛ. ለውጡ እንደመጣ የኢትዮጵያ ህዝብ ይቅርታ እንዲያሰርግልን ጠይቀን ህዝቡም በደሉን ረስቶ በዳዮቹን አቅፎ ለመኖር ሲሰናዳ ያን የለውጥ ጉዞ ተቀብሎና ደግፎ መቆም ያልቻለው TPLF የመጀመሪያውን ታሪካዊ ስህተት ስቷል። ያገኘውንም ይቅርታ እንዲያጣና ከፍተኛ ጥፋት እንዲደርስበት ሆናል።

2ኛ. ብልፅግና ሲመሰረት TPLF ከራሱ ክብር እና ስም ዘሎ ለትግራይ ህዝብ ለታገለለት ህዝብ ቢቆረቆር ኖሮ አንድ ከብልፅግና ለመውጣት ምናልባት የከፋ እንኳን እንደሆነ ለሁለት ተከፍሎ ከፊሉ ብልፅግና ጋር መቆየት ቢችል ኖሮ በርካታ ዜጎቹን መታደግ ይችል ነበር። ይህን ማድረግ ባለመቻሉ የሌብነት ጥጉ ከፍቶ እንዲታይ የጥፋቱ ጥግ ተከፍቶ እንዲታይ ማድረግ ስላስቻለ ብዙውን ነገር አበላሽቷል።

3ኛ. ምርጫ ፦ ብልፅግና በትግራይ ክልል ውስጥ ለመወዳደር ፤ ለማሸነፍ እምብዛም ዝግጁ ባለነበረበት ወቅት እራሱ TPLF በፃፈው ህገመንግስት በፌዴራል መንግስት የሚተዳደሩ አንድ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አንድ የምርጫ ቦርድ መኖር አለበት ብሎ ሲያበቃ የምርጫ ቦርድን ጥሶ የምርጫ ኮሚቴ በመሰየም ምርጫ ለማድረግ የዳዳበት ሁኔታ እጅግ ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሎታል። በጊዜው ፌዴራል መንግስት ወጪ ሸፍኖ የሚያካሂደውን ምርጫ እራሱ ወጪ ሸፍኖ የጨረቃ ምርጫ ለማድረግ ተገዷል። የዛም ሳቢያ ብዙ መዘዘ አምጥቶበታል።

4ኛ. የሰሜን ዕዝ ጥቃት ፦ የሰሜን ዕዝ ጥቃት በብዙ መንገድ ተገልጿል። በአንድ መንገድ ብቻ እንመልከተው በሺህ የሚቆጠሩ መኮንኖች ለ20 ዓመት እና ከዚያ በላይ መከላከያን ያገለገሉ ማኮንኖች በዘር በደም ብቻ አደራጅቶ ከመከላከያ ውጡ ማለት ህዝቡንም እራሱንም በእጅጉ የሚጎዳ ነገር ነበር። እያጠቃን እንኳን ቢሆን እነዛን ኃይሎች በውስጣችን አቆይቶ ቢሆን ኖሮ በ3 ሳምንት ማሸነፍ የሚቻል አልነበረም። ያ ብቻ አይደለም የወጠቱ ኃይሎች በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ያሉት ሀብት ያላቸው ይሆናሉ በዝቅተኛ ኃላፊነት ላይ ያሉት ግን ቢያንስ ለአንድ አመት ደሞዝ አልባ፣ ጡረታ አልባ ሀገር ከሀዲ እንዲሆኑና ከሚያሸንፈው ከሀገር መከላከያ ተነጥለው ከሚሸነፈው ሽፍታ ጎራ እንዲሆኑ ያስገደደ ደካማ ውሳኔ ነበር።

5ኛ. ከመቐለ ስንወጣ ወጡልኝ ብሎ ከሚከተል ደጋግሞ ቢያስብ የብዙ ወጣቶችን ህይወት ከመቀጠፍ ያድን ነበር። 

6ኛ. ወደደሴ ያለው ጉዞ ቁልቁለት ሆነልኝ ብሎ ሳይዘጋጅ ሳያስብ እራሱን በበቂ ሳያደራጅ እና እድል ቢቀናው እንኳን እንዴት ሀገር እንደሚያስተዳደር ሀሳብ ሳይነድፍ እንዲሁ በእውር ድንብር መጓዙ ስላሸነፍክ ብቻ ከግብ በላይ መጓዝ ተገቢ እንዳልሆነ በእጅጉ የተማርንበት እና በመልሶ ማጥቃቱ ከአፋር እና አማራ ክልል ካወጣን በኃላ ተጨማሪውን ጉዞ አያስፈልግም ያልነው የእውር ድንብር ጉዞ ውጤቱ አደገኛ መሆኑን ከTPLF በመማር ጭምር ነው።

7ኛ. አሁን ወደ ትግራይ ክልል ዘልቀን የማንገባበት በርካታ ምክንያቶች ያሉን ቢሆንም አንገባም ብለን ከቆምን በኃላ ነገሩን በተለየ መንገድ ለማየት ጥረት እያደረግን ባለንበት በዚህ ወቅት አሁንም TPLF አላረፈም። አሁንም TPLF በግራ በቀኝ ሊነካካን ይፈልጋል። 

ለ7ኛ ስህተት የሚጓዘው TPLF በፍፁም ድል ማግኘት የማይችል እንኳን ቢሆን በወጣቶች የትግራይ ልጆች ላይ በህይወት የመቀጠፍ የመቁሰል አደጋ የሚያስከትል ስለሆነ 7ኛው ስህተቱ መስመር ስቶ ሳይሄድ መማር የሚችልበት እድል መፍጠር የራሱ ቢሆንም እንኳን እንደባላንጣ አትንኩን ፤ እረፉ ለማለት እወዳለሁ። የነካካችሁን እንደሆነ በተለመደው መንገድ የከፋ ቅጣት ይደርስባችኃልና።

ትላንት እንኳን ክስ አቋርጠን እስረኞች ይውጡ ስንል የTPLF ጀሌዎች ከፊሉ የአማራ አካውንት ከፊሉ የኦሮሞ አካውንት አስመስሎ በመክፈት እኛን ለማባላት ሳይተኙ አድረዋል። አማራ መስለው ፣ኦሮሞ መስለው ብዙ ጥረት አድርገዋል። 

በእርግጥ አማራ እና ኦሮሞ በትናንሽ ጉዳይ የመኳረፍ ባህሪ አላቸው በንግግር ሊስተካከል የሚገባ ነገር ግን ኢትዮጵያ ስትነካ ሁሉንም አጀንዳቸውን ጥለው በጋራ በአንድ ጉርጓድ ሞተው የኢትዮጵያን ነፃነት እንደሚያፀኑ ባለፉት ጥቂት ወራት ከማንም በላይ TPLF ትምህርት ወስዷል። ይህ ከንቱ ሙከራ እኛን ሊከፋፍል እና ሊያስቆመን እንደማይችል ተገንዝበው እኛን ከመነካካት እንዲቆጣቡ እና 7ኛውን ስህተት እንዳያደርጉ ለመምከር እውዳለሁ። 

የተቀረው ዓለም አይኑን እንዲገልፅ እውነትን እንዲፈልግ በባለፈው አንድ አመት በነበረው ጦርነት የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ሰላም እየፈለገና ለሰላም እጁን እየዘረጋ በተደጋጋሚ ጥቃት ያተፈፀመበትና በዓለም መድረክ ፍትህ ያጣበት መሆኑን የምናውቅ ቢሆንም አሁንም የዘረጋነውን የሰላም እጅ ባለመቀበል ትንኮሳ የማያደርገውን ኃይል ዓለም አይኑን ገልጦ እንዲያይ እውነት እንዲፈልግ ለማሳሰብ እወዳለሁ።

የትግራይ ህዝብ ባለፈው አንድ አመት በኢኮኖሚ ፣ በዲፕሎማሲ፣ በፖለቲካ እጅግ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል አሁን አይኑን መግለጥ ያለበት ጊዜ ይመስለኛል። የትግራይ ህዝብም አይኑን እንዲገልጥ አደራ ማለት ፈልጋለሁ።

የተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ፦

1ኛ እናቶች ለኢትዮጵያ አንድነት እና ሰላም ወደላይ ማንጋጠጥና ፈጣሪያችሁን መማፀን አታቋርጡ።

2ኛ ወጣቱ በተለይ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር እና በየክልል ያሉ ልዩ ኃይሎች ክንዳቸው ማበርታትና መናበብ እንዳያቋረጡ።

3ኛ ከሁሉ በላይ የድላችን ሚስጥር አንድነታችን ነውና አንድ መሆን መደመር በጋራ መቆም ለዘላቂ ድል ስለሚያበቃን ኢትዮጵያውያን ሆይ ኢትዮጵያን መታደግ የምትሹ ከሆነ አሁንም በመደመር አንድ መሆንን አበክራችሁ ፈልጉ። " 

@tikvahethiopia

Report Page