Dates

Dates

Crohn's & Colitis Ethiopia


የቴምር ጥቅሞች በጥቂቱ

የቴምር ፍሬ በዛ ያለና ከአብዛኞቹ ፍራፍሬዎችና አትክልቶች የበለጠ ፖሊፊኖል ይዟል። ፖሊፊኖሎች ደግሞ የሰውነትን መቆጣት ሊከላከሉ የሚችሉ አንቲኦክሲዳንት ውህዶች ናቸው።


-የቴምር ፍሬዎችን መመገብ በአንጀት ውስጥ ያለውን ጠቃሚ የባክቴሪያ እድገትን በመጨመር እና በአንጀት ካንሰር ታካሚዎች ዘንድ ፣የካንሰር ሕዋሳት መስፋፋትን በመግታት የአንጀት ጤናን ሊጨምር ይችላል። በአንጀት ውስጥ የሚገኙ ጠቃሚ ባክቴሪያዎች ደግሞ የአንጀት ጤናን በመጠበቅ እና በተለያዩ በሽታዎች እና በሽታ አምጪ ተህዋሲያን ላይ ተጽእኖ በማሳደር፤ እንደ የአንጀት ህመም፣ ተቅማጥ እና የአንጀት ካንሰርን የመከላከል ትልቅ አስተዋፆ አላቸው፡፡ 


- ቴምር በሃይል ሰጪ ንጥረ ነገር እና በካርቦሃይድሬት የበለፀገ ሲሆን በዋናነት በላይኛው የአንጀት ክፍል የሚመጠጡ ፍሩክቶስ፣ ግሉኮስ እና ሱክሮስ ይገኙበታል።ነገር ግን በአንፃራዊነት ከፍተኛ መጠን ያለው ፋይበርን (6.4-11.5%) ይይዛሉ። ስለዚህም የሆድ እቃን ጤና መጠበቅ፣የኮሌስትሮል መጠንን ማስተካከልና የተመጣጠነ ክብደትን መጠበቅ ያሉ ከፋይበር የምግብ ምንጮች የሚገኙ ጠቀሜታዎችን እናገኝበታለን፡፡


- ቴምር በተፈጥሮው የስኳር መጠን ከፍተኛ በመሆኑ ብዙ ሰዎች ለእነርሱ ጥሩ ላይሆን ይችላል ብለው ያስባሉ። ሆኖም በሰውነታችን ውስጥ የሚገኘውን የስኳር መጠን መጨመርና መቀነስን የምገልፅበት glycemic index የተባለ ልኬት አለ፤ በዚህ የልኬት መጠን ዝቅተኛ የግላሰሚክ መጠን ያላቸው ምግቦች የሰውነት የስኳር መጠንን የመዛባትና የመጨመር ባህሪ የላቸውም ስለዚህም እነዚህን መጠቀም ይመከራል፤ ቴምርም ከእነዚህ አንዱ ነው፡፡ በተጨማሪም ቴምር በተትረፈረፈ ጠቃሚ ንጥረ ነገር የተሞላ ነው፡፡


- ቴምር ከጥሩ ጣዕሙ በተጨማሪ ፕሮቲን፣ ቫይታሚን እና ማዕድኖችን ይዟል። ከዚህም ውስጥ ለአእምሮ፣ ለነርቮች፣ ለቆዳና ለተለያዩ የሰውነት ክፍሎች እድገት አስፈላጊ የሆነው ቫይታሚን B-6 ይጠቀሳል፡፡  


 - ቴምር በፖታሲየም የበለፀገ ሲሆን ይህም የልብ ጤንነትን ለመጠበቅ የሚያስፈልገን ኤሌክትሮላይት ነው። ፖታስየም በሰውነት ውስጥ ጡንቻን እና ፕሮቲኖችን ለመገንባትም ይረዳል፡፡ 


- ሰዎች ከተጣራ ስኳር ይልቅ የተፈጥሮ ስኳር መመገባቸውን ለማረጋገጥ በምግብ አሰራር ውስጥ ያሉትን ስኳር፣ ቸኮሌት ወይም ከረሜላዎች በቴምር መተካት ይችላሉ።


ቴምርን መቼ መጠቀም የለብንም?


- በተለይም እንደ የአንጀት ቁስለት ህመምና የአንጀት መቆጣት ህመም ባለባቸው ታካሚዎች ዘንድ ከፍተኛ መጠን ያለውን ምግብ ከተመገብን በሗላ በዛ ያለን ቴምር መመገብ ፤ ቴምር ከፍተኛ ፋይበርን እንደመያዙ በምግብ ቱቦ ውስጥ ለመፈጨት ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድበት ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ የሆድ መነፋትን በማስከተል በሆድ እቃ ውስጥ የመረበሽ ስሜትን ሊፈጥር ይችላል፡፡ ስለዚህም በዛ ያለን ምግብና በዛ ያለን ቴምር በአንዴ መመገብ አይመከርም፡፡


- በተጨማሪም በተለያየ ምክንያት ተቅማጥ በሚያጋጥመን ጊዜ ፤ ቴምር በውስጡ ሶርቢቶል የተባለ የስኳር አልኮል አይነት ስላለውና ይህ ደግሞ በተወሰኑ ሰዎች ላይ የሆድ እቃን ምግብን የማሳለፍ ፍጥነት በመጨመር የተቅማጥን መጠን ስለሚጨምረው የሆድ እቃችን ምግብን የመፍጨትና የማሳለፍ ሂደት እስከሚስተካከል ቴምርን ከመጠቀም ለተወሰነ ጊዜ ማቆም ይመከራል፡፡


07/03/2022

Crohn's & Colitis Ethiopia

Report Page