Daily Tip

Daily Tip

Ethiopianbusinessdaily

#የአፍርሶ_ማልማት_ኢኮኖሚ!


የከተማ መሰረተ ልማት ግንባታ ሶስት አይነት ባህሪ ሊኖረው ይችላል! (በተለይ የኢኮኖሚ፤ የማህበራዊ እና የፖለቲካዊ ማዕከል ሆነው በሚያገለግሉ ዋና ከተሞች ላይ)፡፡


አንደኛ፡- አብዛኛው የዋና ከተሞች እንደሚቆረቆሩት በልዩ ምክንያት አልያም በጥናት የረጅም ጊዜ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መሰረቶችን ከግምት ከቶ ዋና ከተማ ማዋቀር (መንገድ፤ መኖሪያ፤ የንግድ ቦታ፤ የማህበራዊ አገልግሎት ቦታ፤ ወዘተ የመጪውን ጊዜ የእድገት ፍላጎት እና የህዝብ ቁጥር ከግምት የሚከት አልያም በዘመናት ውስጥ በሂደት ቅርጹ የሚለዋወጥ ሊሆን ይችላል)፤


ሁለተኛ፡- ነባር ከተሞችን ከወቅታዊ የህዝብ ቁጥር ሁኔታ እና ከአገልግሎት ባህሪ አንጻር ማሻሻያዎችን እያደረጉ ማዋቀር (መንገዶች ሲጠቡ፤ የመኖሪያ ቤቶች እጥረት ሲኖር፤ የኢንቨስትመንት እና የንግድ የፖሊሲ ባህሪ ሲለዋወጥ፤ በተቀራራቢ ቦታ ሰፊ የደረጃ ለውጥ ሲስተዋል፤ ወዘተ በነባር ቦታዎች ላይ ማሻሻያ እያደረጉ ነባሩን ከአዲስ ይዘት ጋር እያጣጣሙ ለመሄድ መሞከር፤


ሶስተኛ፡- በብዙ ኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ምክንያቶች ነባር ከተሞችን በመተው በአዲስ ስትራቴጂካዊ ከተሞች መተካት! በዋናነት ሀገራቶች በተለይ ዋና ከተሞችን የሚለውጡት ዋና ከተማው የሀገሪቷ ማዕከላዊ/አማካይ ቦታ ባለመሆኑ እና በነባር ከተማ የተጨናነቀ አኗኗር መፈጠር ሲጀምር ሲሆን! የሚከተሉት ሀገራት ዋና ከተማ የለወጡ ናቸው….


ካዛኪስታን (ከአልማታ ወደ አስታና)፤ ማይናማር (ከያንጎን ወደ ናይፒዳው)፤ ታንዛኒያ (ከዳሬሰላም ወደ ዶዶማ)፤ ናይጄሪያ (ከሌጎስ ወደ አቡጃ)፤ ብራዚል (ከሪዮ ዲ ጄኔሮ ወደ ብራዚሊያ)፤ ፓኪስታን (ከካራቺ ወደ ኢስላማባድ)፤ ራሽያ (ከሴንት ፒተርስፐርግ ወደ ሞስኮ)፤ ግብጽን ጨምሮ አሁን ላይ አዲስ ዋና ከተማ እየገነቡ ያሉ ሀገራቶች አሉ፡፡


ሁለት ዋና ከተሞችን የአስተዳደር እና የዲፕሎማሲ መቀመጫ እና የንግድ ማዕከል አድርገው የሚጠቀሙ ሀገራቶችም አሉ (ቤኒን፤ ቦሊቪያ፤ ደቡብ አፍሪካ፤ ኔዘርላንድ፤ ማሊዢያ፤ ሲሪላንካ፤ ቺሊ፤ ሲዋዚላንድ፤ ኮትዲቫር፤ ጆርጂያ እና ሞንቲኔግሮ ናቸው፡፡


አዳዲስ ዋና ከተሞችን በእቅድ መገንባትም ሆነ ነባር ከተሞችን እያፈረሱ መገንባት ላይ የሚነሱ ጠንካራ እና ደካማ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ውጤቶች አሉ፡፡


እንደ ኢትዮጲያ ዝቅተኛ ኢኮኖሚ ባለው ሀገር አዲስ ዋና ከተማ መገንባት (ከኢኮኖሚ አንጻር፡ የቦታ ዝግጅት እስከ የግንባታ ወጪ ቢሊየን ዶላሮችን መጠየቁ እና ከፖለቲካ አንጻር፡ የፌደራል አወቃቀር ስርዓቱ የቦታ መረጣን እና ዝግጅትን ቀላል ሂደት የሚሰጠው ባለመሆኑ) ቀላል አይሆንም! እንዲሁም ነባር ዋና ከተማ እና መንደሮችን አፍርሶ በመገንባት ሂደት ላይም ነባር ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች የሚኖራቸው Opportunity Cost ቀላል አይሆንም፡፡


#ለምሳሌ፡- በዋጋ 200ሚሊየን ብር የሚያወጣ እና በዓመት ከ200ሚሊየን ብር በላይ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቀሴ (በኪራይ፤ በክፍያ፤ በሽያጭ፤ በግዢ፤ ወዘተ) እንዲፈጠር የሚያደርግ ህንጻ ቢፈርስ በቅስፈት 400ሚሊየን ብር Negative ኢንቨስትመንት አለው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በምትኩ የሚከናወነው ፕሮጀክት ይህንን 400ሚሊየን ብር በዘላቂነት የሚመልስበት ፍጥነት የተጠና መሆን አለበት ማለት ነው! (ህንጻው በፈረሰበት ቦታ ለዓይን የሚማርክ የሰዎች ማረፊያ አረንጓዴ ቦታ ቢሰራ ይህንን አዝጋሚ የገንዘብ እንቅስቀሴ ያለበት የኢኮኖሚ ሴክተር ካጣው 400ሚሊየን ብር ጋር ለማቀራረብ ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል? ከተባለ ማህበራዊ ፋይዳው ሰፊ ግን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ጠባብ እና ጊዜ የሚወስድ ሊሆን ይችላል)፡፡


በአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ውስጥ የመንግስታት ሚና የግል ሴክተሩ በቀዳሚነት የኢኮኖሚ ፋይዳ ላይ ስለሚያተኩር ማህበራዊ ፋይዳዎች ሳይዘነጉ ተጠብቀው እንዲሄዱ ማድረግ እና የግል ሴክተሩ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው እንዲጨምር ማገዝ ነው፡፡


የአዲስ አበባ ነባር ከተሞች ከአዲስ የከተማ እድገት እሳቤ አንጻር እንዲለወጡ የመልሶ ግንባታ እንቅስቃሴ በስፋት ይስተዋላል፡፡ ይህ እያፈረሱ መገንባት አሁን ባይሆን እንኳን ወደፊት በጊዜ ሂደት ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ገፊ ምክንያቶችን ተከትሎ መደረጉ ስለማይቀር ለምን? የሚባል አይሆንም፡፡


ስለዚህ ከጠባብ ሌላ አማራጭ የሚወሰድ መፍትሄ እንደመሆኑ በመልሶ መገንባት እና ይዞታ በማሻሻል ሂደት መታሰብ ያለበት የሚፈርሱ ቦታዎች የነበራቸው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በምትካቸው ከሚሰሩት ፕሮጀክቶች ከሚጠበቅ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ጋር በአመክንዮ ማወዳደር ተገቢ ነው፡፡


በምትኩ የሚሰሩ ፕሮጀክቶች የነበሩ አዎንታዊ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን ትርፋማነት በከፍተኛ ሁኔታ መለወጥ መቻል እንዳለባቸው ማረጋገጥ ይገባል፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ የቢዝነስ እንቅስቃሴን የሚቀንስ የተጨናነቀ የትራንስፖርት እንቅስቀሴ አለ! የመንገድ ፕሮጀክቶች ፈጣን የትራንስፖርት ኮሪደርን መፍጠር ከቻሉ ቀላል ፋይዳ የለውም፡፡


የታዳጊ ሀገራት ከተሞች ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገት ለማስመዝገብ ሲያስቡ ተቀዳሚ ትኩረት ወጪ እና ተጠባቂ ፋይዳ/ገቢ ነው! በርግጥ የገጽታ ጉዳይ በሂደት የሚታሰብ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለሆነም መንደሮችን በማፍረስ ሂደት ተጠባቂ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ፋይዳ የተጠና መሆኑን እና ዝቅተኛ Opportunity Cost ያለው መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል፡፡

Report Page