DW

DW


ዛሬ ያስቻለው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሶስተኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ቀሲስ በላይ መኮንን በተጠረጠሩበት «ከባድ የሙስና ወንጀል» ላይ የተከሳሾች ጠበቆች መቃወሚያን አድምጧል። በችሎቱ አንደኛ ተከሳሽ ቀሲስ በላይ እንዲሁም ሁለተኛ እና ሶስተኛ ተከሳሾች ቀርበዋል፡፡ አራተኛ እና አምስተኛ ተከሳሾች ግን ዛሬም ስላልቀረቡ ፖሊስ ያቅርብ ነው የተባለው፡፡

ሶስቱ ተከሳሾች እና ጠበቆቻቸው በቀረቡበት የክስ መነበብን ተከትሎ ጠበቆች መቃወሚያቸውን ካቀረቡ በኋላ የደንበኞቻቸው የዋስትና መብት ተጠብቀው ጉዳያቸውን ከውጪ እንዲከታተሉ በሚል አጥብቀው ተከራክረዋልም፡፡

በተለይም በጠበቆች በኩል የቀረበው የአቃቤህግ የክስ መቃወሚያን በማስመልከት አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ ከጠበቆቻቸው አንዱ አቶ ዮናታን ዘውዴ፤ ዋናው የክሱ ጭብት ተቃውሞ ከቀረበባቸው ነጥቦች መሆኑን አስረድተዋል

ጠበቆቻቸው አክለውም ቀሲስ በላይ ላይ የተመሰረተው ክሱ አስቀድሞውም የዋስትና መብታቸው እንዲነፈግ ተብሎ “ተገቢ ባልሆነ አንቀጽ” ተመሰረተ ሲሉም ተከራክረዋል፡፡ እሳቸው የቤተክህነት ዋና ስራ አስከያጅ ሆነው ሳሉ የመንግስት ሰራተኛ በማስመሰል የተመሰረተባቸው ክስ ከዚህ አኳያ ተቀባይነት የለውም ሲሉም ጠበቆች ተከራክረዋል፡፡ ቀሲስ በላይ መንግስት ባሁን ወቅት አዲስ አበባ ውስጥ የሚሰራው የኮሪደር ልማቱ አስተባባሪ እንደነበሩም አስታውሰው በምርመራ ወቅትም ያደረጉት ትብብር በአዎንታዊነት ታይቶ የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅ ጠይቀዋል፡፡

ቀሲስ በላይ ለችሎቱ ያቀረቡት አስተያየት

ቀሲስ በላይም በችሎቱ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ ጠበቆቹ እንዳሉት ሁሉ “ፖሊስ ይዞኝ ሳይሆን እራሴ ነው የሄድኩት” ብለዋል፡፡ “ብዙ የሀገር ጉዳይ በእጄ ስላሉ ጥፋ ብባል እንኳ የምጠፋ ስላልሆንኩ” በጤናዬ ላይ በደረሰው እክል እና በቤተሰቦቼ ላይ በደረሰው ችግር ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብት ይጠብቅልኝ ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በዚህም የብዙ ልጆች አሳዳጊና የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን ጠቅሰው የዋስትና መብቱ እንዲጠበቅላቸው ጠይቀዋል፡፡

ጠበቃቸው አቶ ዮናታን አክለው በሰጡን ማብራሪያም፤ ቀሲስ በላይ የሀይማኖት ተቋም ሰራተኛ እንጂ የመንግስት ሰራተኛ ባለመሆናቸው ሊጠየቁ የሚገባው በወንጅል ህግ እንጂ በጸረ-ሙስና ህግ መሆን አይገባም ነበር፡፡

“አቃቤ ህግ ወንጀሉ በመንግስት ልማት ደርጅት ላይ ከተፈጸመ በጸረ-ሙስና ህግ ያስጠይቃል ብልም፤ እኛ ግን በማንኛውም አካል ለሚፈጸም የማታለል ድርጊት በወንጀል ህጉ መሰረት መጠየቅ አለባቸው ብለን ስንከራከር አሁን ያተኮርነው የዋስትና መብታቸውን ማስጠበቅ ላይ ነው” ያሉት ጠበቃ ዮናታን ወንጀሉ መፈጸም አለመፈጸሙ ገና ወደ ፍሬ ጉዳይ ስገባ የሚታይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

አቃቤ ህግ በበኩሉ ክሱ የተመሰረተው “በከባድ የአታላነት የሙስና ወንጀል” በመሆኑና ቅጣቱም ከ10 ኣመት በላይ ስለሚያስፈርድ የዋስትና መብቱ ልጠበቅላቸው አይገባም በማለት ተከራክሯል፡፡ በርግጥ በተጠርጣሪ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ያረጋገጠው የአቃቤ ህግ ክርክር ሆኖም ግን ክሱ በተመሰረተበት የሙስና ወንጅል አዋጅ አንቀጽ መሰረት በመንግስት የልማት ድርጅቱ ላይ ሊደርስ የነበረው ጉዳት ወይም በተጠርጣሪዎች ሊገኝ የነበረው ያልተገባ ጥቅም እንደ ጉዳት (ጥቅም) ሊታይ ስለሚችል ዋስትና ያስከለክላል ሲል ሞግቷልም፡፡ 

የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ

ግራ-ቀኙን የተመለከተው ችሎቱም ተከሳሾች አሁንም በፖሊስ ጣቢያ እንዲቆዩ፣ አቃቤ ሀግ የጠበቆች መቃወሚያ ላይ መልስ እንዲሰጥ እና ዛሬ የክስ መቃወሚያ ያላቀረቡት ሶስተኛ ተከሳሽ የክስ መቃወሚያ እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ በመስጠት፤ በዋስትናው ጥያቄ እና በክስ መቃወሚያው ላይ ብይን ለመስጠት ለዛሬ ሳምንት ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ሊቀ ዐዕላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን በሚዚያ ወር መጀመሪያ የአፍሪካ ኅብረት ግቢ ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ በአካል በመቅረብ "ከኅብረቱ የክፍያ ሰነድ ጋር ተመሳስለው የተዘጋጁ" በተባሉ ሀሰተኛ ሰነዶች በመጠቀ ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ከህብረቱ የባንክ ሒሳብ ወደ ሌላ ሒሳብ ለማዘዋወር ሲሞክሩ ተገኝተዋል በሚል በፖሊስ መያዛቸው የሚታወስ ነው። 

ሥዩም ጌቱ

እሸቴ በቀለ

ዶቼ ቨለ

Report Page