#COVID19Ethiopia
ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተሰጠ ፕሬስ መግለጫ፦
በአገራችን የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተበት እለት ጀምሮ በመንግስትና በባለድርሻ አካላት በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን ትዕዛዞች፣ ክልከላዎችና መልዕክቶች እየተላለፉ ነዉ፡፡ እነዚህን መልእክቶችና ትእዛዞች ሰምቶ ለራስ በመፈጸምና ሌሎችን እንዲፈፅሙት በማድረግ በኩል በአንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሻሉ ሁኔታዎች ቢኖሩም ነገር ግን በርካታ በሚባለዉ ህብረተሰቡ ዘንድ የመዘናጋት፣ የቸልተኝነትና በሽታዉን አስመልክቶ የሚሰጡ ትእዛዛቶች ወደ ጎን በመተዉ የሚሰጡ መግለጫዎችን የመላመድና ትኩረት ያለመስጠት ሁኔታዎች እየተስተዋለ ይገኛል፡፡
በቅርቡ በመንግስት ተቋማት፣ በልማት ድርጅቶችና በግል ተቋማት ወሰጥ ያደረግነዉ ምልከታ ከቅደመ ጥንቃቄ ጋር በተያያዘ የመዘናጋት፣ ትኩረት ያለመሰጠት ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ ለማረጋገጥ ችለናል፡፡ ማህበረሰባችን በተለያዩ ቦታዎች ላይ በተለይም በግብዒት ቦታዎችና በትራንስፖርት አገልግሎት መሰጫ አካባቢ እያሳየ ያለዉ መዘናጋትና ህጎቹን ያለማክበር ጉዳይ አሳሳቢ ነዉ፡፡
ይህ የኮሮና ቫይረስ በአገራችን በተገኘበት እና የአሰቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀበት ሰሞን የነበሩ ጥንቃቄዎች ጋር ሰነጻጸር እየቀነሰ መዘናጋት እየጨመረ ሲሆን በተቃራኒዉ አሁንም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ እጅጉን አሳሳቢና ዋጋ የሚያስከፍል ጉዳይ እየሆነ ይገኛል፡፡
መንግስት በሽታዉን ለመከላከልና ስርጭቱን ለመቀነስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አዉጆ ደንብና መመሪያዎችን በማዉጣት ተግባራዊ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ከዚህ ቀደም የወጡ መመሪያ ቁጥር 1/2012 እና መመሪያ ቁጥር 2/2012 ማሻሻያዎችን የያዘ መመሪያ ቁጥር 4/2012ን አፅድቆ ስራ ላይ እንዲዉል አቅጣጫ ሰጥቷል፡፡
በዚሁ መሰረትም በመመሪያ ቁጥር 4 በኮድ 2 የቤት ተሸከርካሪዎች ተጥሎ የነበረዉ ከፊል የእንቅስቃሴ ክልከላ ፣የማሰክ አጠቃቀም ፣ በአገር አቋራጭ የህዝብ ተሸከርካሪዎች ላይ እንዲሆም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞች መግቢያና መዉጫ ስአት ላይ ማሻሻያ አድርጓል፡፡
የኮድ ሁለት የቤት ተሸከርካሪዎች ላይ መጣል ሚገባው የትራንስፖርት ሚኒስቴር በኩል የተደረገውን ጥናት መነሻ በማድረግ በከፊል በመገደብ ግለሰቦች ቤታቸዉ እንዲዉሉ በማድረግ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ታሳቢ ተድርጎ በሙሉና በጎዶሎ መለያ ቁጥር ከፊል እገዳ ተጥሎ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን ሆኖም የኮድ 2 ተሸከርካሪ ባለቤቶች በታሰበዉ መልኩ ቤታቸዉ ከመዋል ይልቅ የህዝብ ትራንስፖርት በመጠቀም እና ታርጋዎችን እየቀያየሩ የመጠቀም ሁኔታ መታየቱ እንዲሁም ተራቸዉ ባልሆነ ቀን ቤታቸዉ ከመዋል ይልቅ በሰፊዉ የመንቀሳቀስ ሁኔታ የተስተዋለ መሆኑ ክልከላዉን መልክ መቀየር አሰፈላጊ ሆኗል፡፡
በመሆኑም በአጠቃላይ በኮድ ሁለት የቤት ተሸከርካሪዎች ተጥሎ የነበረዉ ክልከላ ተነሰቶ አጠቃላይ የትራንስፖርት እንቅስቃሴውን ለመገደብ የሚያስችል አማራጭ ክልከላ እንድተገበር የሚኒስትሮች ኮሚቴ ወስኗል፡፡
የእንቅስቃሴ ገደብ መቀነሻ አሰራሮች አንዱ የሆነዉ በሀገር አቋራጭ ተሸከሪካሪዎች የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን ቁጥር መቀነስ ነው፡፡
የዋጋ ጭማሪ ማድረግ ሰዎች ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ ለመገደብ አሰተዋጽኦ እንደሚያደረግ በትራንስፖርት ሚኒስቴር የተደረገው ጥናት ያመላክታል፡፡
በዚሁ መሰረት አገር አቋራጭ የህዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪዎች መደበኛ የወንበር አቅማቸዉ ከ45(አርባ አምስት) ሰዉ በላይ የሆነ ተሸከርካሪዎች የሚያስከፍሉት የታሪፍ ጭማሪ ከመደበኛ ዋጋዉ 75% እንዲሆን የተወሰነ ሲሆን መደበኛ የወንበር ቁጥራቸዉ እስከ (45) አርባ አምስት ሰዉ የሆኑ የህዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪዎች የሚያስከፍሉት የታሪፍ ጭማሪ ደግሞ 100% መሆኑ ተወሰኗል፡፡
በተያያዘ የሚኒስትሮች ኮሚቴ በተሻሻለዉ መመሪያ መሰረት የማስክ አጠቃቀምን አስመልክቶ ከቤት ዉጭ በማንኛዉም ቦታ የአፍና አፈንጫ መሸፈኛ ማስክ ማድረግን ግዴታ እንዲሆን ወስኗል፡፡ የአፍና አፈንጫ መሸፈኛ ማሰክ በፋብሪካዎች የተሰራ ወይም ባህላዊ ጨርቅ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህን ግዴታ በማሰፈጸም ረገድ የጸጥታ መዋቅሩ ኃላፊነት እንዳለበት ተወሰኗል፡፡
በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞች የስራ መግቢያ ስአት 1፡30 እንዲሆን የተቀመጠ ሲሆን መዉጫ ስአቱም 9፡30 እንዲሆን ተደርጎ ተሸጋሽጓል፡፡ ይህም የትራንስፖርት መጨናነቅ ለመቀነስ ነው፡፡
በአጠቃላይ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሁሉም ህብረተሰብ ኃላፊነትና ግዴታ ያለበት በመሆኑ የሚታዩ መዘናጋቶችን እና ችላ ባይነትን በመቅረፍ ሁላችንም ህግና ሥርዓቱን ማክበር ግዴታ እንደሆነ በመገንዘብ መላዉ የሀገራችን ህዝብ እራሱ፣ቤተሰቡንና ሀገሩን የኮሮና ቫይረስ ከሚያስከትለው ጉዳት ለአፍታም ሳይዘናጋ ለመጠበቅ ርብርብ እንዲያደረግ ጥሪያችንን እናቀረባለን፡፡
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ
ግንቦት 19 ቀን 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ