Borana

Borana


በኦሮሚያ ክልል ቦረና 😥

በኦሮሚያ ክልል፣ ቦረና ዞን በድርቅ ሳቢያ በርካታ ወገኖቻችን ዛሬም ችግር ላይ ናቸው::

እነዚህ ወገኖች በድርቁ ምክንያት ያላቸውን ከብቶች ስላጡ እጅግ በጣም ፈታኝ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚኖሩት::

ከሰሞኑን በድርቅ ተፈናቅለው መጠለያ ካምፕ ውስጥ የነበሩ ወገኖች ቃላቸውን ለቪኦኤ ሰጥተው የነበረ ሲሆን ያሉበት ሁኔታ እጅግ በጣም አሳዛኝ ነው።

(በድብሉቅ ወረዳ የሚገኙ ተፈናቃዮች)

የ7 ልጆች እናት ወ/ሮ ጂሎ ጉራቻ ፦

" የዘንድሮው ድርቅ የነበሩንን ከብቶች እና ሁሉንም ንብረቶችን ነው ያወደመብን። ባዶ እጃችንን ስንሆን ወደዚህ መጣን ፤ እዚህ ከመጣን በኃላ በምግብ እና ውሃ እጥረት እየተቸገርን ነው። በተለይም ህፃናት ነፍሰጡር ሴቶች፣ አዛውንቶች በምግብ እጥረት እየተጎዱ ናቸው። እኛ እዚህ ከሰፈርን ከ6 ወር በላይ ሆኖናል። በመጠለያው በጣም ብዙ ቤተሰቦች ነው ያሉት። በቆይታችን አንዴ ብቻ ነው ለተወሰኑ ቤተሰቦች የምግብ ድጋፍ የተሰጠው እንጂ ምንም አላገኘንም። ስለዚህ በጣም ችግር ላይ ውስጥ ነው ያለነው። "


የ6 ልጆች አባት ዳለቻ ዲዳ ፦

" የምንጠጣው ውሃ በጣም የቆሸሸ ነው። እንስሳት ሲሞቱ ከሚጣሉበት ነው ልጆቻችን የሚቀዱልን። በዛላይ የመፀዳጃ ቦታም የለንም። እንዲሁ በበሩ ደጃፍ ነው ይህ ሁሉ በዚህ የሰፈረው ህዝብ የሚፀዳዳው ስለዚህ የበሽታ ወረርሽኝ ፍራቻ አለብን። ሌላው የመጠለያ ቦታና ላስቲክ ሰጥተውናል። ይህ ላስቲክ ብርድ የሚከላከል አይደለም። እናም በጣም ችግር ውስጥ ነን። "


የልጆች እናቷ ትዬ አደንጌ ፦

" ብርዱ በጣም አስቸጋሪ ነው። ለምግብ ፍለጋ ነው ከእሳት አጠገብ የምንነሳው። በዛ ላይ የምንለብሰው ልብስ የለንም። በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው። "

ተፈናቃዮች መንግስት እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ይድረሱልን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የድብሉቅ ወረዳ የቡሳ ጎኖፋ ፅ/ቤት ባልደረባ የሆኑት አቶ ዴበኖ ሳራ " 1410 አባወራዎች ናቸው እዚህ ሰፍረው ያሉት። እነዚህ ቤተሰቦች የነበሯቸውን ሁሉንም ከብቶች በድርቁ ምክንያት ያጡ ናቸው። የከተማ አሰተዳደሩ ቦታ ሰጥቶ እዚህ እንዲሰፍሩ ሆነዋል ነገር ግን በእስካሁን ባለው የተደረገላቸው ድጋፍ የለም። በቂ ምግብ ፣ ውሃ፣ መጠለያ፣ መፀዳጃ ቤት ልብስም የላቸውም። ብርድም እየጎዳቸው ነው። "

ወረዳው ተፈናቃዮችን ለመደገፍ አቅም የለኝም ያለ ሲሆን በመጠለያው ያሉ ወገኖች ህይወት በምግብ እጦት እንዳያልፍ የተቻለውን እየደገፈ መሆኑን ገልጾ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልግ ለዞን አመራሮች እና ለተራድኦ ድርጅቶች ማሳወቁን ገልጿል። እስካሁን ግን ምላሽም የለም።


የቦረና ዞን የቡሳ ጎኖፋ ኃላፊ አቶ ጉዮ ጨፍሪ ፦ " በዞኑ ከ17 ሺህ አባወራዎች በላይ በድርቁ ምክንያት ሙሉ ንብረታቸውን አጥተዋል።

በድብሉቅ አካባቢ ሰፍረው ስላሉት እናውቃለን። በዛ አካባቢ ከተጠለሉ ከ3 ወር በላይ ሆኗቸዋል። በዞን ደረጃ እንደግፋቸው ነበር አሁን ድብሉቅ ያሉት ከ1410 በላይ አባወራዎች ናቸው። የሚኖሩት በጣም አጣብቂኝ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ስለሆነ በዞን፣ በክልል እና በፌዴራል መንግስት ጉዳያቸው ትኩረት አግኝቶ የሚመለከተው አካል ምላሽ እንዲሰጥ ተብሏል። ሌላው ደግሞ በጤና በግልና አካባቢ ንፅህና የምግብ ድጋፍ የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አሉ። በዞን ደረጃ ከእነሱ ጋር ተመካክረን ችግራቸውን ለመፍታት እየሰራን ነው። እነዚህ ሰዎች የዛሬ ድጋፍ ብቻ ሳይሆን ዘለቄታዊ መፍትሄ ይሻሉ ምክንያቱም የነበራቸው ከብቶች አልቀውባቸዋል ወደቦታቸው መመለስ አይችሉም ስለዚህ አሁን ባሉበት በዘላቂነት ሰፍረው የስራ እድል እንዲያገኙ አዲስ ፕሮፖዛል አዘጋጅተን የተለያዩ አካላትን ድጋፍ በመጠየቅ ላይ ነን። "

በተመሳሳይ በዳሶ እና ኤልወዬ ወረዳም ተፈናቃዮች ያሉ ሲሆን ዞኑን ክፉኛ በመታው ድርቅ እስካሁን ባለው 12 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር የሚገመት የእንስሳት ሀብት ገድሏል።


(ጋዜጠኛ ገልሞ ዳዊት - VOA)

Report Page