#BekeleGerba
አቶ በቀለ ገርባ ወደ ሆስፒታል ሲወሰዱ ምን ገጠማቸው ?
ትላንት የእነአቶ ጃዋር፣ የእነአቶ በቀለ ገርባ ጠበቆች በእስር ላይ የሚገኙትን ፖለቲከኞች የህክምና ጉዳይ አስመልክቶ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ችሎት አቤቱታ አቅርበው ነበር።
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎትም እነአቶ በቀለ ገርባ በግል ሀኪሞቻቸው እንዲሁም በፈለጉት የግል ህክምና ተቋም መታከም እንደሚችሉ አፅንኦት ሰጥቶ ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር።
በፍርድ ቤቱ የተሰጠው ትእዛዝ አቶ በቀለ፣ አቶ ጃዋር፣ አቶ ሃምዛ፣ አቶ ደጀኔ አ/አ ሜክሲኮ አካባቢ ላንድማርክ ጄነራል ሆስፒታል በአጃቢ አስፈላጊውን ጥበቃ ተደርጎ ህክምና እንዲወሰዱ የሚል ነው።
ነገር ግን በዛሬው ዕለት አቶ በቀለ ገርባ ላንድማርድ ጄነራል ሆስፒታል እንደሚሄዱ ከተነገራቸው እና ከማረሚያ ከወጡ በኃላ የአጃቢ መኪኖቹና እሳቸውን የያዘው አምቡላንስ ከመንገድ ላይ ወደጦር ኃይሎች ሆስፒታል እንደወሰዷቸው ልጃቸው ቦንቱ በቀለ ተናግራለች።
ቦንቱ ፥ "20 ቀን ምግብ ያልበላውን፣ የታመመውን አባቴን በኃይል በወታደሮች ተገዶ/ታፍኖ ከእርሱ፣ ከቤተሰቡ ከዶክተሮቹ እውቅና ፍቅድ ውጭ ወደማይፈልገው የወታደሮች ሆስፒታል (ጦር ኃይሎች) የገባው" ብላለች።
የተፈፀውን ድርጊት ቤተሰቡ ከአፈና ለይቶ አያየውም ስትል የምታስረዳው ቦንቱ "ማን ወደዛ እንዲወሰድ እንዳደረገው አይታወቅም፤ ማረሚያ ቤቱ ከላይ የመጣ ትእዛዝ ነው ብሎናል ፤ ይሄ ትዕዛዝ ሰጪ የበላይ አካል ከዳኛ፣ ከፍርድ ቤት፣ ከህግ በላይ የሆነ አካል እንዳለ ማሳያ ነው" ስትል ገልፃለች።
አሁን ላይ አባቴ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ አላውቅም የምትለው ቦንቱ በቀለ አባቴ ተጎድቶ የሆነ ነገር ደርሶበት ህይወቱ አደጋ ላይ ከወደቀ መንግስት ብቻ ነው ኃላፊነቱ የሚወስደው ስትል ተናግራለች።
አቶ በቀለ ወደጦግ ኃይሎች ሆስፒታል ከገቡ በኃላ በቦታው የነበሩ ጥበቃዎች ቤተሰብ ወደ ውስጥ እንዳይገባ መከልከላቸውን እና መመለሳቸውን ቦንቱ ገልፃለች።
በሌላ በኩል የእነ አቶ ጃዋር/እነ አቶ በቀለ የግል የህክምና ክትትል የሚያደርገው ክፊሉ ቡድን (የቀሩት ቃሊቲ ነበሩ) አቶ በቀለ ገርባ ላንድ ማርክ ጄነራል ሆስፒታል ይመጣሉ ብለው ለ2 ሰዓታት ሲጠብቁ ነበር።
በኃላም ሃኪሞቹ ወደጦር ኃይሎች ሆስፒታል እንደሄዱ የተሰማ ሲሆን የሃኪሞቹ ስልክ አይሰራም ነበር ሃኪሞቹ ያሉበት ሁኔታ በግልፅ አይታወቅም ነገር ግን በጦር ኃይሎች ሆስፒታል ሳይይዙ አይቀርም የሚሉ ሪፖርቶች ወጥተዋል።
የካቲት 09/2013 ዓ/ም
Tikvah-Ethiopia
@tikvaahethiopiaBOT @tikvahethiopia