#BGU

#BGU


በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማንዱራ ወረዳ በፀጥታ ችግር ቀያቸውን ትተው የሄዱ ሰዎችን ንብረት የፀጥታ አካላት ሲዘርፉ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ታውቋል፡፡

በክልሉ ማንዱራ ወረዳ ገነተ ማሪያም ቀበሌ እና አካባቢው ከሰሞኑ የፀጥታ ችግር ተፈጥሯል፡፡ በዚህም በቀስት እና በጥይት በታገዘ ጥቃት የሰዎች ሕይወት አልፏል፤ የአካል ጉዳትም ደርሷል፡፡ ለዘመናት በሠላም በኖሩ ኢትዮጵያውያን መካከልም ጥርጣሬና ጥላቻ እንዲፈጠር በመደረጉም የፀጥታ ችግሩ ከመሻሻል ይልቅ ስጋቶች እየጨመሩ እንደሆኑ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

በምዕራብ ዕዝ 24ኛ ክፍለ ጦር፣ ሻለቃ ሦስት፣ የ1ኛ ሻምበል አዛዥ ምክትል መቶ አለቃ መሃመድ ጀማል በአካባቢው ለማረጋጋት ሥራ መሠማራታቸውን ለአብመድ ተናግረዋል፡፡ ችግሩ የተከሰተው የተደራጁ ቡድኖች በስድስት ቀበሌዎች ተደራጅተው በሠላማዊ ነዋሪዎች ላይ እርምጃ መውሰድ በመጀመራቸው እንደሆነ ምክትል መቶ አለቃው ለአብመድ ተናግረዋል፡፡ በዚህም የሰዎች ሕይወት ማለፉንና የአካል ጉዳትም መድረሱን አረጋግጠዋል፡፡ በወቅቱ በሌላ አቅጣጫ ለግዳጅ ተሰማርተው የተዘረፉ የቤት እንስሳትን ለማስመለስ እየሠሩ እንደነበር አስታውሰው ችግሩ መከሰቱን ከሰሙ በኋላ ግን ሁኔታውን እያረጋጉ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡

ከፀጥታ ችግሩ በስተጀርባ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች የሚገኙ የክልሉ ሰዎች አሉበት ብለው እንደሚያምኑም አዛዡ ገልጸዋል፡፡ ከቀበሌ እስከ ክልል ያሉ መሪዎች ለማረጋጋት ሥራው እገዛ እንዲያደርጉ ተጠይቀው ሁኔታውን ለማረጋጋትም ሆነ ለመተባበር ቀና ምላሽ አለመስጠታቸውንም ነው በማሳያነት የተናገሩት፡፡

ስለጉዳዩ የቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሥራ ኃላፊዎችን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ባለመሳካቱ ሐሳባቸውን አላካተትንም፡፡

ይህ ዘገባ በተጠናቀረበት ጊዜም ‹‹ድኩል›› እና ‹‹ማክሰኝት›› በተባሉ ቀበሌዎች ጥቃት ለማድረስ የተደራጁ አካላት መኖራቸውን፣ በሌሎቹ ግን መረጋጋት መኖሩን ነው ምክትል መቶ አለቃ መሃመድ የነገሩን፡፡ ማንዱራ ከተማ ላይ ግን ነዋሪዎች ሙሉ በሙሉ ተፈናቅለው መሄዳቸውን እንደተመለከቱ ነው የተናገሩት፡፡ ‹‹አብዛኞቹ ወደ ቻግኒ ቀሪዎቹ ደግሞ ፓዌ እየሄዱ ነው›› ብለዋል ምክትል መቶ አለቃ መሀመድ፡፡

ቀያቸውን ትተው መሄድ እንደሌለባቸው ለማሳመን ቢሞክሩም ከተከሰተው ችግር አሳሳቢነት አንጻር ነዋሪዎቹ በስጋት አካባቢያቸውን ትተው እየሄዱ መሆናቸውን ነው ያስረዱት፡፡

የአካባቢው የፀጥታ አካላት ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በትብብር እየሠሩ ቢሆንም በማረጋጋቱ ተግባር ደስተኛ ያልሆኑ መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡

ዛሬ ሐምሌ 03 ቀን 2011ዓ.ም ደግሞ በፀጥታ ችግሩ ቀያቸውን ትተው የሄዱትን ሰዎች ንብረት አምስት የፀጥታ አካላት ለመዝረፍ ሲሞክሩ በመከላከያ አባላት እንደተያዙ ገልጸዋል፡፡ ሁለቱ ለጊዜው ሲያመልጡ ሦስቱን በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተካሄደ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡

ምንጭ፦ AMMA

@tsegabwolde @tikvahethiopia

Report Page